Site icon ETHIO12.COM

ዐቃቤ ህግ በቀድሞ የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የክስ መዝገብ ሌሎች ድርጅቶችን አካቶ ለመቅረብ ጠየቀ

ዐቃቤ ህግ በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ባቀረበባቸው የቀድሞ የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትር ጫላ ዋታ( ዶ/ር) መዝገብ ዝርዝር ላይ ተጨማሪ ሌሎች ድርጅቶችን በክሱ ላይ አካቶ ለመቅረብ ፍርድ ቤቱን ጠየቀ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ዐቃቤህግ ሌሎች በክሱ ያልተካተቱ ድርጅቶችን አካቶ ለማቅረብ ያቀረበው የክስ ዝርዝር ማሻሻያ ጥያቄን ለመጠባበቅ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በነበረ ቀጠሮ ዐቃቤህግ የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀደሞ ፕሬዚዳንትር ጫላ ዋታ (ዶ/ር) ጨምሮ 15 ተከሳሾች ላይ ከ 195 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ማድረስ በሚል አራት ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቶ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

ክሱ ተመስርቶባቸው ከነበሩ ተከሳሾች መካከል የቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀደሞ ፕሬዚዳንት ጫላ ዋታ(ዶ/ር )፣ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ታምሩ ኦኖሌ፣ የዩንቨርሲቲው የአስተዳደር እና የተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ሮባ ደንቢ(ዶ/ር ) ፣ በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ተቋማዊ ልማት ም/ፕሬዚዳንት ኢንጂነር አብርሐም ባያብል ይገኙበታል።

ይሁንና የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤህግ በክስ ዝርዝሩ ላይ ከተከሳሾቹ በተጨማሪ የወንጀል ተሳትፎ ያላቸው ሌሎች ድርጅቶችን አካትቼ ክሴን አሻሽዬ ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

በዚህም መሰረት ችሎቱ ዐቃቤህግ ሌሎች በክሱ ያልተካተቱ ድርጅቶችን አካቶ ለማቅረብ ያቀረበው የክስ ዝርዝር ማሻሻያ ጥያቄን ለመጠባበቅ ለሀምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

እንደ አጠቃላይ በ15 ተከሳሾች ላይ በግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በተከሳሾቹ ላይ ቀርቦባቸው የነበረው የክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው በሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በቀጥታ ግዢ እንዲፈጸም ውሳኔ በማስተላለፍ ከሌሎች ተከሳሾች ከስራ ተቋራጮች ያለአግባብ ካለ ግልፅ ጨረታ የግዢ በመፈጸም በመንግስት ላይ 195 ሚሊየን 52 ሺህ 812 ብር ከ81 ሳንቲም ጉዳት አድርሰዋል በማለት ነበር ዓቃቤ ህግ በዋና በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ ያቀረበባቸው።

በታሪክ አዱኛ – fana

Exit mobile version