Site icon ETHIO12.COM

በጀርመን የኤርትራ መንግስት ደጋፊና ተቃዋሚዎች ተጋጭተው 26 ፖሊሶች ጉዳት ደረሰባቸው፤ መቶ ኤርትራውያን ታሰሩ

በጀርመኗ ጊሰን ከተማ በኤርትራውያን የባሕል ፌስቲቫል ላይ በተከሰተ ግጭት 26 የጀርመን ፖሊስ አባላት ጉዳት እንደደረሰባቸው የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

የአገሪቱ ፖሊስ በጊሰን ከተማ የተዘጋጀውን የባሕል ፌስቲቫል ለማወክ የወጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያንን ለመበተን ዱላ እና ዐይን የሚያቀጥል ፈሳሽ ረጭቷል፤ ሄሊኮተፕር ጭምር በአካባቢው አሰማርቶ ነበር።

ፖሊስ በግጭቱ ተሳታፊ ናቸው ያላቸውን ከ100 የማያንሱ ኤርትራውያንን እና ትውልደ ኤርትራውያንን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ጨምሮ ገልጿል።

ሁከቱ የተፈጠረው በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች የተዘጋጀ ነው የተባለውን ዝግጅት ለማወክ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች ፌስቲቫሉ ወደሚዘጋጅበት ቦታ በኃይል ለመግባት ጥረት ማድረጋቸውን ተከትሎ ስለመሆኑ የጀርመን መገናኛ ብዙኃን በስፋት ዘግበዋል።

የባሕል ፌስቲቫሉ መዘጋጀቱን በመቃወም አደባባይ የወጡ፤ ፌስቲቫሉ ለኤርትራ መንግሥት ፕሮፖጋንዳ የተዘጋጀ ነው ይላሉ።

የጀርመን ፖሊስ ትናንት ቅዳሜ ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም. የተከሰተው ግጭት ለሰዓታት መቆየቱን እና 26 የፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጿል።

አሶሺዬትድ ፕሬስ የጀርመን ፖሊስን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ሁከቱን ለመቆጣጠር 1 ሺህ የፖሊስ አባላት፣ ሄሊኮፕተር እና ውሃ በከፍተኛ ኃይል የሚረጭ አድማ በታኝ መኪና ተሰማርቶ ነበር።

የከተማዋ አስተዳዳሪዎች በሁከቱ ወቅት የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ መሐል የከተማ ክፍል ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

በጀርመኗ ከተማ የተከሰተውን ግጭት የሚያሳዩ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተጋሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች፣ በአብዛኛው ወጣት የሆኑ ኤርትራውያን ድንጋይ ወደ ፖሊስ ሲወረውሩ እና በከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል ውስጥ ፖሊስ ሲያባርራቸው ታይተዋል።

ፖሊስም ተቃዋሚዎቹ በሕግ አስከባሪ ኃይል አባላት ላይ ጠርሙስ፣ ድንጋይ እና የጭስ ቦምብ መወርወራቸውን፣ ተሸከርካሪዎችን ማውደማቸውን እና ፌስቲቫሉ የሚካሄድበትን ስፍራ የመከለያ አጥር ማፍረሳቸውን አስታውቋል።

ፖሊስ ጨምሮ እንደገለጸው ተቃዋሚዎቹ ወደ ፌስቲቫሉ ስፍራ ተሳታፊዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ በነበረ አውቶብስ ላይ ድንጋይ ወርውረዋል።

የጀርመን ዜና አገልግሎት በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከንጋት 11፡30 ጀምሮ ፌስቲቫሉ ወደሚካሄድበት ቦታ በኃይል ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ከነበሩ ከ100 በላይ ሰዎች መከልከላቸውን ዘግቧል።

ከአንድ ዓመት በፊት በተመሳሳይ ከዚህ ፌስቲቫሉ መካሄድ ጋር በተያያዘ ሁከት ተፈጥሮ በርካታ ሰዎች ተጎድተው ነበር።

የጀርመን ዜና ወኪል ዲፒኤ ከአንድ ዓመት በፊት በነበረው ሁከት 100 የፌስቲቫል አዘጋጆች እና ጎብኚዎች ላይ ጉዳት ደርሶ እንደነበር ዘግቧል።

ይህን ተከትሎ ሊከሰት ይችላል የተባለን ተመሳሳይ ሁከት ለመከላከል ፌስቲቫሉ ዘንድሮ እንዳይካሄድ የከተማዋ ባለሥልጣናት እና ፖሊስ ከልክለው የነበረ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤት ግን ፌስቲቫሉ መከልከል የለበትም በሚል ተካሂዶ ዳግም ግጭት ተከስቷል።

በሁከቱ ምንክንያት ከፍንራንክፈርት በስተሰሜን በምትገኘው እና የ84 ሺህ ሕዝብ መኖሪያ በሆነችው ጊሰን ከተማ የትራፊክ እንቀስቃሴ ተገድቦ ቆይቷል።

ፌስቲቫሉ ከአርብ ሰኔ 30 እስከ እሁድ ሐምሌ 2/2015 ዓ.ም. ድረስ እንዲካሄድ የተዘጋጀው የኤርትራውያን ማዕከላዊ ምክር ቤት በተባለ እና ለኤርትራ መንግሥት ቅርብ ነው በተባለ አካል ነው።

በቅርብ ዓመታት ጀርመን ከፍተኛ ቁጥር ላለቸው ኤርትራውያን ስደተኞች ጥገኝነት የሰጠች ሲሆን፣ ይህም በአውሮፓ ኅብረት ካሉ አፍሪካውያን ማኅብረሰቦች ኤርትራውያኑን ከቀዳሚዎቹ ተርታ አስልፏቸዋል።

በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኤርትራ መንግሥት በዜጎቹ ላይ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጽም ይገልጻሉ።

በዚህም ምክንያት በኤርትራ ያለውን የፖለቲካ እና የእምነት ነጻነት ጭቆና እንዲሁም የጊዜ ገደብ የሌለውን አስገዳጅ የብሔራዊ አገልግሎት በመሸሽ በርካቶች ኤርትራውያን አገር ጥለው ይሰደዳሉ።

ቢቢሲ አማርኛ

Exit mobile version