በስዊዲን የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች በፈጠሩት ግጭት ጉዳት ደረሰ፤ ከመቶ በላይ ታስረዋል

በስዊድኗ መዲና ስቶክሆልም በኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል ላይ በተከሰተ ግጭት ከ50 በላይ ሰዎች መጎዳታቸውን አሶሲዬትድ ፕሬስ (ኤፒ) ዘገበ። የስዊድን ፖሊስ ቃል አቀባይ ዳንኤል ዊክዳሀል እንዳሉት ከክስተቱ ጋር በተያያዘ ከ100 እስከ 200 የሚሆኑ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ኤፒ የአገሪቱን መገናኛ ብዙኃን ጠቅሶ እንደዘገበው በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል በተከሰተው ግጭት በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል።

ፌስቲቫሉ እንዳይካሄድ የተቃወሙ አንድ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ፌስቲቫሉ ስፍራ በኃይል በመግባት ድንኳኖች እና ተሽከርካሪዎችን በእሳት አያይዘዋል።

ፌስቲቫሉን በኃይል ለመበተን ከተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች የመጡ ናቸው የተባሉት ተቃዋሚዎች ድንጋይ እና ዱላ በመጠቀም የፖሊስ ፍተሻ ጣቢያዎችን በኃይል አልፈዋል ሲል ‘ኤክስፕረሰን’ የተባለ የአገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።

ግጭቱን ተከትሎ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች መኪኖች ሲነዱ እና ደንኳኖች ፈራርሰው አሳይተዋል።

ስዊድን በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ትውልደ ኤርትራውያን መኖሪያ ነች። የፌስቲቫሉ አዘጋጆች ሥነ ሥርዓቱ የኤርትራን ባሕል መዘከር ነው ቢሉም ተቃዋሚዎች ግን ለአምባገነኑ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈርቂ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ነው ይላሉ።

በአውሮፓ ከተሞች በሚካሄዱ የኤርትራውያን የባሕል ፌስቲቫል ላይ ግጭቶች ሲከሰቱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም. በጀርመኗ ጊሰን ከተማ በኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል ላይ በተፈጠው ሁከት በርካታ የጀርመን ፖሊስ አባላት ላይ እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።

የጀርመን ፖለቲከኞችን እና ባለሥልጣናትን ባስቆጣው ሁከት ተሳታፊ ናቸው በተባሉ በመቶዎች በሚቆጠሩ ኤርትራውያን ላይ የወንጀል ክስ መመስረቱ ተገልጾ ነበር።

በዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ደግሞ ፌስቲቫሉ እንዳይካሄደ ተቃዋሚዎች ባቀረቡት ጥያቄ ከቀናት በፊት ዝግጅቱ እንዲሰረዝ ተደርጓል።

ቢቢሲ

See also  የማዳበሪያ ያለህ በሚባልበት አማራ ክልል 400 ኩንታል ማዳበሪያ በህገወጥ መንገድ ሲሰራጭ ተያዘ

Leave a Reply