Site icon ETHIO12.COM

“የአማራ ህዝብ ማንነቱንም ፤ ነጻነቱንም ማስመለስ ችሏል” ኮሎኔል ደመቀ

ኮሎኔል ደመቀን ጠቅሶ የክልሉ ሚዲያ እንዳለው አማራ ማንነቱንም ፤ ነጻነቱንም ማስመለስ ችሏል። ያስመለሰው ነጻነትና ማንነቱ ደግሞ ቀደም ሲል በሃይል የተነጠቀውን ነው። ባህይል የተነጠቀውን ማንነቱን በሃይል ማስመለሱን ያመለከቱት ኮሎኔል ደመቀ ጉዳዩ ተፈጥሯዊ መብትን የማስመለስ ነው።

ሰሞኑንን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ በህግ አግባብ በህዝብ ፍላጎት ለአንዴና መቸረሻ ጊዜ የህግ እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ፣ ከዛ ውጭ ያለው የሃይል አካሄድ እንደማይጠቅምና መንግስትም እንደማይፈልገው በግልጽ ማስታወቃቸው ይታወሳል። የአማራ ክልልም በተመሳሳይ በህግና ህግ የህዝብን ፍላጎት ተነተርሶ እልባት እንዲሰጠው እንደሚሰራ አስታውቆ ነበር።

ከትግራይ ቲቪ ይህን ተከትሎ ባሰራጨው ዜና በህገ መንግስቱ መሰረት ቀልቃይት ጠገዴና ሌሎች አሁን አማራ ክልል አሁን ያስተዳደራቸው ያሉ አካባቢዎችን መረከብ እንደሚፈልግ፣ ይህ ካልሆነ ግጭት እንደሚነሳ፣ የፕሪቶሪያው ስምምነትም ይህን እንደሚያካትት ጠቅሶ ሰፊ ቃለ መጠይቅ አቅርቧል። ቃለ መጠየቁ ሲጠቃለለ የህዝብ ፍላጎት የሚባል ነገር ሳይነሳ ትህነግ ባዘጋጀውና የአማራ ክልል ቀደም ሲል አልተሳተፍኩበትም ባለው ህገመንግስት መሰረት አሁን ነጻ ወጡ የተባሉትን አካባቢዎች እንዲመለሱ የሚጠይቅ ነው።

ለዚህ ጥያቄ ይመስላል ኮሎኔል ደመቀ “ባለፈው ሥርዓት የአማራ ሕዝብ ማንነቱ ተጨፍልቆ፤ ነጻነቱን ተነጥቆ ቆይቷል” ያሉት “ከበርካታ ዓመታት ውጣ ውረድ በኋላ በቅርቡ የአማራ ህዝብ ማንነቱንም ፤ ነጻነቱንም ማስመለስ ችሏል” ሲሉ ከህዝብ ፍላጎት ውጪ የሚሆን ምንም ጉዳይ እንደማይኖር ያመለከቱት። “ነጻነት አስጠብቆ እና ማንነቱን ጠብቆ ለመዝለቅ ከምንጊዜውም በላይ በሰከነ እና በበሰለ መንገድ መጓዝን ይጠይቃል” ሲሉም የስሜትን ጉዞ ጎጂነት ጠቁመዋል።

“ነጻነት ተፈጥሯዊ መብት ነው፤ የተነጠቅነውም ያስመለስነውም ተፈጥሯዊ መብታችንን ነው” ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ከነጻነት ማግስት ለመልማት እና ለማደግ መሥራት ደግሞ ሌላው ተፈጥሯዊ ግዴታችን መኾን አለበት ብለዋል፡፡ ዞኑ በሙሉ አቅሙ እና ትኩረቱ ልማት ላይ መኾኑን አመልክተዋል። አሚኮ ይህን አስመልክቶ የዘገበውን ከስር ያንብቡ።

ከሐምሌ 5 እስከ ጥቅምት 24 በሁለት የተለያዩ ዓመታት ያየናቸው ሁለት ዓበይት ክስተቶች የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ትግል እና ድል ፈር ያስያዙ አጋጣሚዎች ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄን በሰከነ እና በሰለጠነ መንገድ መመለስ ያልቻሉ የዓለም አምባገነን መንግሥታት ያዩትን ውርደት በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ትናንት የነበሩ አምባገነኖችም አይተዋል፡፡

ትውልዱ ከሀገር እና ሕዝብ በላይ የኾነ ፍጹም ምድራዊ ኃይል እንደሌለ በዚያች ተዓምራዊት ሌሊት በተግባር አይቷል፡፡ ግፈኞች የግፍ ቁናቸው ሞልቶ የሚያፈሰውን መከራ እና ሞት መቀበል ጀምረዋል፡፡ ሐቅን እስከ ህቅታ የያዙ እውነተኛ የሕዝብ ልጆች ደግሞ ለአይቀሬው ድል የሞት ሽረት ትግል አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም እውነት እስከ ንጋት ድረስ ሳትጠበቅ ሕዝብ አሸናፊ የኾነበትን የድል ብስራት ዜና ሐምሌ 5 ምሽት ላይ ሰማ፡፡

በኢትዮጵያ ዘመናዊም ኾነ ጥንታዊ የሀገረ-መንግሥት ምስረታ ታሪክ የአማራ ሕዝብ ታላቅ አበርክቶ አለው ያሉን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኅላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የታላቅ አበርክቶው መገለጫ ራሱን በንቃት ከመጠበቁ እና የሌሎችንም አጥብቆ ከማክበሩ ይመነጫል ይላሉ፡፡ በየዘመኑ ያለፈው ሥርዓተ መንግሥት ሁሉ ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ከሕዝብ ተጠቃሚነት አንጻር ሲታይ በርካታ ክፍተቶች ነበሩበት የሚሉት ኮሎኔል ደመቀ ባለፈው ሥርዓት ከነበረው ዝቅጠት የከፋ ክስተት የታየበት ጊዜ ግን አልነበረም ይላሉ፡፡

ባለፈው ሥርዓት የአማራ ሕዝብ ማንነቱ ተጨፍልቆ፤ ነጻነቱን ተነጥቆ ቆይቷል ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ከበርካታ ዓመታት ውጣ ውረድ በኋላ በቅርቡ ማንነቱንም ፤ ነጻነቱንም ማስመለስ ችሏል ነው ያሉት፡፡ ያስመለሰውን ነጻነት አስጠብቆ እና ማንነቱን ጠብቆ ለመዝለቅ ከምንጊዜውም በላይ በሰከነ እና በበሰለ መንገድ መጓዝን ይጠይቃል ብለዋል፡፡ “ነጻነት ተፈጥሯዊ መብት ነው፤ የተነጠቅነውም ያስመለስነውም ተፈጥሯዊ መብታችንን ነው” ያሉት ኮሎኔል ደመቀ ከነጻነት ማግስት ለመልማት እና ለማደግ መሥራት ደግሞ ሌላው ተፈጥሯዊ ግዴታችን መኾን አለበት ብለዋል፡፡ ዞኑ በሙሉ አቅሙ እና ትኩረቱ ልማት ላይ መኾኑን በማንሳት፡፡

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ እና አሥተዳደር ከነጻነት ማግስት ጀምሮ በሰላም ማስጠበቅ እና በልማት ሞዴል አካባቢ ኾኗል ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና አንጻራዊ መረጋጋት ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አንዱ ነው ያሉት ኮሎኔል ደመቀ የተገኘው ሰላም የሕዝቡ እና አሥተዳደሩ መናበብ እና መደጋገፍ የፈጠረው ጥምረት ውጤት ነው ብለዋል፡፡

ሕዝቡ ላለፉት ዓመታት ለማንነቱ እና ለነጻነቱ ዋጋ የከፈለ ሕዝብ በመኾኑ ያገኘውን ድል ለማጽናት በቁርጠኝነት እየሰራ መኾኑን ያነሱት ኮሎኔል ደመቀ የአማራ ሕዝብ ካለፈው መማር፣ አንድ መኾን እና ለዓላማ መጽናት ግድ የሚልበት ወቅት ላይ መኾኑን አንስተዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ትግል ከውስጥ ወደ ውጭ የሚያይ መኾን ይኖርበታል ያሉት መምሪያ ኅላፊው ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር ለነገ የማይባል የአማራ ሕዝብ የቤት ሥራ እንደኾነም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

Exit mobile version