ETHIO12.COM

በአማራ ክልል ኮማንድ ፓስቶች የማጽዳት ስራ መጀመራቸው ይፋ ሆነ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ረብሻው እየተቀዛቀዘ ነው

“ችግር የሚያባብሱና ስምሪት የሚሰጡ ኃይሎች” በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆኑን መንግስት አስታውቋል። “ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው፤ ጉዳዩን የሚያባብሱ ስምሪት የሚሰጡ ኃይሎችን በቁጥጥር ሥር ምዋላቸውን የመንግሥት ኮምዩንኬንሽ አገልግሎት ኃላፊው ለገሰ ቱሉ ናቸው የተናገሩት። የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው ” ዘራፊ” ያሉት ቡድን በአስቸኳይ በቁጥጥር ስር ውሎ ክልሉ ወደ ነበረበት ሰላማዊ እንቅስቃሴ ባስቸኳይ እንደሚገባ ገልጸዋል። አሁን ወቅቱ የወደብ ባለቤት የሚኮንበት እንደሆነም ተመልክቷል።

በተለያዩ ቦታዎች “በጎንደር፣ ባህርዳር ከተማ አቅራቢያ፣ ደብረብርሃን ከተማ ዙሪያና የተለያዩ አካባቢዎች የተኩስ ድምጽ ይሰማል” ከሚለው የተደጋገመ ተባራሪ ወሬ በቀር የተጠቀሱት ከተማዎች አሁን ድረስ አስተዳደራቸው እንዳለ ነው። በአንዳንድ ገጠራማና አነስተኛ ከተሞች መዋቅር የማፍረስ ስራና አዲስ አደረጃጀት የመሰየም እንቅስቃሴ መኖሩ ግን መንግስትም አምኗል። ከዚሁ የተኩስ ድምጽ መሰማት ጋር ተያይዞ በመስል ይፋ የሆነው ዘርፋና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ የተፈጸመ ዘረፋ ነው። ከጎንደር 60 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ዳባት አጠገብ ገደብጌ ነጋዴዎች ተዘርፈዋል። ብቸና በተመሳሳይ ዝርፊያና ንብረት ማውደም ተፈጽሟል። ማርቆስ የጅምላ ዝርፊያ ተፈጽሟል።ሌሎችም አካባቢዎች በስፋት ዝርፊያ መፈጸሙ ተሰምቷል። ለዚህ ይመስላል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በግልጽ ቋንቋ ” ዘራፊ ሃይል” ያሉት። ይህ ሃይል የመንግስትን መዋቅር የማፍረስ ስራ የሰራባቸው አካባቢዎች እንዳሉ አመልክተው ባስቸኳይ ሁሉም ጉዳይ መልክ እንደሚይዝ አመልክተዋል።

ቀደም ሲል በደብረ ኤሊያስ ስላሴ ገዳም መሽገው የነበሩ ከሁለት መቶ በላይ ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን ተከትሎ የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል “ባልደራስ በሚል ሽፋን ተንቀሳቅሶ እንዳልተሳካለት ሲያውቅ፤ መንግሥትን በኃይል ለመጣል በማቀድ የአማራ ሕዝባዊ ግንባር የተባለ አደረጃጀት በመፍጠር ሽመልስ ስማቸው፣ ሰውመሆን ወረታውና መንበሩ ካሴ ከተባሉ ግብረዓበሮቹ እንዲሁም ከሌሎች ጥቂት የክልሉ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር በመቀናጀትና በህቡዕ በመንቀሳቀስ  ታጣቂዎችን ሲመለምል፣ ሲያደራጅና ስምሪት ሲሰጥ ነበር” ሲል እስክንድር ነጋን መወንጀሉ አይዘነጋም። ግንባሩን በውጭ አገር ሆነው የሚመሩት ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ እንደሆኑ እስክንድር የግንባሩን መቋቋም ይፋ ሲያደርግ ማስታወቁ አይዘነጋም። ግብረሃይሉ ሁለቱ  በፈጠሩት ትስስር በክልሉ የትጥቅ ትግል በማድረግ ሕዝቡን ወደማያባራ ጦርነት ለማስገባት ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውንም አስታውቆ ይህ ሳይሆን ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ጥሪም አቅርቦ ነበር።

አሁን የተጀመረውና መሳይ መኮንን “የፋኖዎች ህብረት” ያለው እንቅስቃሴ ወለጋ ድረስ ዘልቆ የአማራን መሬት እንደሚያስመልስ መሪው ሻለቃ ዳዊት በይፋ ቀደም ሲል የብሄራዊ ቲያትር ተወዛዋዥ ከነበረውና አሁን “የፖለቲካ ተንታኝ፤ የአማራ ትግል መሪ” ከሆነው አበበ በለው ጋር በመረጃ ቴሌቪዥን መናገራቸው ይታውሳል።

መሠረቱን ምዕራብ ጎጃም ቡሬና አባይ በረሃ አካባቢ አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው ግለሰቡ የሃይማኖት ሽፍንና እንደ ከለላ ለመጠቀም ከሌሎች የቡድኑ ታጣቂዎች  ጋር ወደ ምሥራቅ ጎጃም ዞን  ደብረ ኤልያስ ወረዳ በማቅናት  ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ በሥላሴ ገዳም አካባቢ ምሽግ ቆፍረው መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል በህቡዕ ሲያሴሩ እንደነበር ያመለከተው የግብረ ኃይሉ መግለጫ፤ በተለይ የገዳሙ አስተዳዳሪ የሆኑትን አባ ኤልሳን ለዚህ ሕገወጥ ተግባር ሲጠቀሙ እንደነበር ጠቅሷል፡፡ አስተዳዳሪውም ከሃይማኖቱ አስተምህሮ ውጭ በገዳሙ ውስጥ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ እንዲደረግ ከመፍቀድ ባሻገር ከሌሎች መነኮሳት ጋር በማበርና የጦር መሣሪያ ጭምር በማንገብ ከጽንፈኛ ቡድኑ አባላት ጋር  ተሰማርተው እንደነበር ኦፕሬሽኑ ካለቀ በሁዋላ ግብረሃይሉ በምስልና በምስክር ይፋ ማድረጉን የሚያስታውሱ አሁንም ዋና ምሽግ በተመሳሳይ ገዳማት እንደሆኑ ይገልጻሉ። ለዚህም ይመስላል እንቅስቃሴው በሃይማኖት ሽፋን የሚመራና ሌሎችን የሚያገል እንደሆነ የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች ስጋት እንደገባቸው የሚናገሩት። እዚህ ላይ ያንብቡ

ክልሎች በተለይም ” የጋላ ወራሪ” እየተባለ የሚጠራውን ኦሮሚያን ጨምሮ ምንም ሳይተነፍሱ በዝምታ እየተከታተሉት ያለው የአማራ ክልል አሁናዊ ቀውስ በሰላም እንዲቋጭ አብዛኛው ህዝብና አካሄዱ የገባቸው እየወተወቱ ነው። ከዚህ ቀውስ ጀርባ ያሉት መሪዎችና ተዋጊዎቹን አሰልጥነው፣ አስታጠቀውና ዕቅድ አውጥተው ያሰማሩት ሃይሎችን ማንነት ጠንቀቀው የሚረዱ እንደሚሉት ይህ ግጭት ማንንም አይረቅምም። በተለይም ለአማራ ህዝብ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው።

 ፊትለፊት የሚነገረውና ከጀርባ የሚሴረው ፍጹም የተለያየ እንደሆነ ሰክኖ ማስብ እንደሚያስፈልግ የሚያሳሰቡ የአማራ ህዝብ በስም ተለይቶ የደረሰበትን በደል አሁን በተያዘው ማንገድ ማረም አይቻልም። ሆነ ብለው ለማጋደል አልመው በሚሰሩ ተላላኪዎች ሴራ፣ በተወሰኑ ነፍጥ አንጋች ተቀጣሪዎች ጥፋት አንድን አቃፊና ከሁሉም ጋር የተዋለደ አቃፊ ህዝብ “ጋላ፣ ወራሪ፣ ፈላሽ” በሚል በአደባባይ በአገር ውስጥና በዓለም ዙሪያ መፈክር ለጥፎና መፈክር አያሰማ የሚፈርጅ ትግል በምን የፖለቲካና የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል ለበርካቶች ግራ ነው።

ይህ ክልሎች ሁሉ በጥንቃቄ የሚመለከቱት የአማራ ክልል ጉዳይ ሁሉም በጋራ ያደረጁትን መከላከያ ሰራዊትን “ወራሪና አሸባሪ” በሚል ፈርጆ መነሳቱ ካስከተለው ቅሬታ በዘለለ ትናንት ለትህነግ ጋር በነበረው ጦርነት የከፈለውን መሰዋዕትነት የካደ መሆኑ በርካቶችን ” ምክንያቱ ምንድን ነው? መከላከያን የሚጠላና እንዲፈርስ የሚሰራ ሃይል ከየት የመጣ ነው? የመከላከያ መፍረስ አጀንዳስ የማን ነው? የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ምን ያስተምረናል? እነማን ተባብረው መከላከያን፣ አየር ሃይልን፣ ባህር ሃይልን አፈርሱት? ዛሬስ እነማን ናቸው ከዚህ ተጋር ጀርባ ያሉት? ኢትዮጵያ የወደብ ጉዳይ ስታነሳ ለምን ይህ ጦርነት እንዲጀመር ሆነ? ” የሚሉ ጥያቄዎችን የሚያነሱ አሁንም ጥንቃቄ እንደሚያሽ ይመክራሉ።

የአማራ ህዝብ ” አራት ኪሎ ግባ” የሚል የእነ አቶ ክርስቲያን ቅስቀሳ ሌሎች ክልሎችን ምን እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል? የሚለው ጉዳይ፣ “መጀመሪያ አማራ ክልል ቀጥሎ ኢትዮጵያ” የሚለው የእስክንድር ነጋ የአደባባይ መግለጫ፣ በአንድ የፌደራል ስርዓት በምትመራ አገር እንዴት ሊተገበር እንደሚችል ግራ የገባቸው አሁንም እርጋታን ይማጸናሉ።

መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የአማራን ክልል ጸጥታ ለማስከበር ክልሉን በአራት ኮማንድ ፖስት ከፍሏል። በቅርቡም ክልሉን ወደቀድሞ ሰላሙ እንደሚመልስም አስታውቋል። የአስተዳደር መዋቅሩ የተጠለፈና ሁለት ቦታ በሚንቀሳቀሱ አካላት የተበረዘ በመሆኑ ማጥራት እንደተጀመረም አመልክቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ጽህፈት ቤቱን ጨምሮ አራት መምሪያዎችን ማደራጀቱንና የአማራ ክልልም በአራት ኮማንድ ፓስቶች ስር መከፈሉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዋና ሰብሳቢው አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ።

አቶ ተመሥገን ዛሬ በሠጡት ማብራሪያ መሠረትም፤ በአማራ ክልል የተቋቋመው ኮማንድ ፓስት አንደኛው የምዕራብ አማራ ኮማንድ ፓስት ሲሆን፤ ምስራቅ ጎጃምን፣ ምእራብ ጎጃምን፣ ደብረማርቆስ ከተማን እና የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞንን እንዲሁም የባህርዳር ከተማ አስተዳደርን የሚይዝ ነው። የኮማንድ ፓስቱን መቀመጫ ራሡ ኮማንድ ፓስቱ የሚወስን ይሆናል ብለዋል።

ሁለተኛው ኮማንድ ፓስት በቀድሞ አጠራሩ ሰሜን ጎንደር ይባል የነበረው የአሁኑ የሠሜን ምዕረብ አማራ ኮማንድ ፓስት ሲሆን ይሄ ደግሞ፤ ሰሜን ምዕራብ ማዕከላዊ ጎንደር ከተማን ደቡብ ጎንደርን ደብረታቦር ከተማን የያዘ ነው።

ሶስተኛው የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፓስት ሲሆን፤ ደብረብርሃን ከተማን ሰሜን ሸዋን እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞንን ያካለለ መሆኑን አቶ ተመስገን አስታውቀዋል።

የምሥራቅ አማራ ኮማንድ ፓስት አራተኛው ኮማንድ ፓስት ሲሆን፤ የደቡብ ወሎን የደሴ ከተማን ኮምቦልቻን የሰሜን ወሎን ወልዲያ ከተማን እና የዋግኸምራ ብሔረሰብ ዞንን ያካለለ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተለያዩ አካላት ተውጣጠው የተካተቱበት ኮማንድ ፓስቱ በዛሬው ስብሰባው የጠቅላይ መምሪያ ዕዙን እቅድ ተመልክቶ ማጽደቁን አቶ ተመስገን ተናግረዋል።

በቀጣይ ቀናት የኦፕሬሽን ሥራዎች የፓርቲና የመንግሥት መዋቅሮችን የማጠናከር ሥራዎች እንደሚከናወኑ፤ ህግና ሥርዓት የማስከበሩ ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

ሐምሌ 30 ቀን 2015 ዓ.ም

Exit mobile version