Site icon ETHIO12.COM

ትህነግና ሻዕቢያ በዱባይ መገናኘታቸው ተሰማ፤ አሜሪካ የፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ አተኩራለች

– አማራና ኦሮሚያ ክልል ሰላም እንዲሰፍን በሚል አሜሪካ ከአውሮፓ ህብረት ጋር እየመከረች መሆኑ ተገለጸ

– በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ጦርነት በውይይት ለመፍታት የተለያዩ አካላት እየተንቀሳቀሱ ነው

የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አስተዳደር እንዳቋቋመው የሚነገርለት ቡድን አቶ ጌታቸውና ሌተናል ጻድቃን የሚመሩት ቡድን አካል ከሆነ የትህነግ አካላት ጋር በዱባይ ተገናኝተው መምከራቸው ተሰማ። አሜሪካ በኦሮሚያና በአማራ ክልል ሰላም እንዲወርድ በሚል ከአውሮፓ ህብረት ጋር መላ እንደምትፈልግ አስታወቀች። የፕሪቶሪያውን ስምምነት ትግበራ እንደሚገመግሙ አመልክተዋል። ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን “ያገኘነውን እንዳናጣ” ሲሉ እርጋታን የተማጸኑበት መልዕክታቸው አሁን ላይ ትርጉም እያገኘ ነው።

የኢትዮ12 መረጃ አቀባዮች እንዳሉት የኤርትራ ሃይሎችና የትህግራይ ነጻ አውጪ ግንባር አንድ ክፍል የተገናኙት አብረው ሊሰሩ የሚችሉበትን መንገድ ለማፈላለግ ነው። ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አገዛዝ ግንኙነት እንደሌላቸው ተደርጎ ሽፋን የሚሰጣቸውና በውጭ አገር የሚኖሩ የሻዕቢያ ወገኖች የተገናኙት ከጀነራል ጻድቃንና አቶ ጌታቸው ጋር ግንኙነት ካላቸው የትህነግ ሃይሎች ጋር መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

እነዚህ አካላት በንግግራቸው ኢትዮጵያ አፋር ድረስ ዘልቀው በመያዝ፣ በሰሜን ወልቃይትና ጠገዴን በማካተት ፣ ትግራይን ከኤርትራ ደጋማ አካባቢዎች ጋር በመዋሃድ አንድ ታላቅ አገር ለመገንባት ቀደም ሲል የተያዘውን ዕቅድ ተግባራዊ የሚደረግበትን አግባብ ተነጋግረዋል። ይህ አሳብ በፍጥነት እንዲከናወን የታሰበው ኢትዮጵያ እየገነባች ያለው ሰራዊት በኤርትራ ላይ ከፈጠረው ስጋት አንጻር ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ አማራ ክልል ውስጥ እንዲነሳ የተደረገው ጦርነት በተፈለገው መንገድ ካልተጠናቀቀ ኢትዮጵያ አሰብን ለመውሰድ በገሃድ ዘመቻና እርምጃዎችን ልትወስድ እንደምትችል ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

“የአሰብን ወደብ ለኤርትራ ሰጥተን በሁዋላ ጊዜው ሲደረስ ከኤርትራ ላይ ለመውሰድ ይቀላል” በሚል አቶ መለስ በወሰኑት መሰረት የአሰብን ወደብ ያለ አግባብ የውሰደችው ኤርትራ፣ ከውስጥም ሆነ ከውጭ በአገዛዙ ላይ የሚነሳው ቅሬታ በመበርከቱ ኢትዮጵያ ሃይል እንኳን ብትጠቀም የሚመክት ሃይል እንደማይኖር መረጃውን የነገሩን አመልክተዋል። ስለሆነም ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትሆን ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን “ነጻ ነን፤ ከፐሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ግንኙነት የለንም” የሚሉ ሃይሎችና ትህነግ ምክር መጀመራቸው ተመልክቷል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ስምምነት ፈጥረው ድንበር ሲከፈት በሶስት ወራ ውስጥ ብቻ አምስት መቶ ሺህ የሚጠጉ የኤርትራ ተወላጆች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን፣ በአሁኑ ሰዓት አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የኤርትራ ተወላጆች አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በሰላም እየኖሩ መሆኑንን የሚገልጹት የዜናው ባለቤቶች፣ የትግራይ ሃይሎች መከላከያን ተቀላቅለው ወደ ኤርትራ ካቀኑ የኢሳያስ አገዛዝ እድሜው የቀናት ስለሚሆን ቅድሚያ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በማሰብ ይህን ግንኙነት እንደጀመሩ አመልክተዋል።

ትግራይ ክልል ገብተው የነበሩ የአማራ ግዛቶችን አስመልክቶ በውይይቱ ላይ ዝርዝር አቋም ባይያዛም፣ የትግራይ ሃይሎች ከኤርትራ ወገን የቀረበላቸውን የአብሮነት ቅድመ ሁኔታ ከተቀበሉ በኤርትራ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግ እንደሚችል ቃል መገባቱ ታውቋል። ስማቸውን ሳይጠቅሱ መረጃውን ያቀበሉን ሚስጢር አዋቂዎች፣ አሁን ላይ ባለው ወደብ የማግኘት አቋም፣ ሻዕቢያ እያሰለጠነ በአማራ በኩል የሚልከው ሃይል ከኢትዮጵያ በኩል በፈጠረው ብስጭት ፣ በጦርነቱ ሳቢያ የያዘውን የኢትዮጵያን መሬት ሙሉ በሙሉ ለቆ እንዲወጣ መጠየቁ አንድ ላይ ተዳምሮ ሻዕቢያ “ሳልቀድም ልቅደም” በሚል ከትህነግ ፍላጎት ጋር ለመግባባት የማይችል ንግግር ተጀምሯል። ከኢርትራ በኩል ያሉት ክፍሎች የሻእቢያ የውጭ ክንፍ እንደሆኑ መረጃ እንዳለም አመልክተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሀመር ከነሐሴ 13 ጀምሮ እስከ 19/2015 ድረስ ወደ አውሮፓ እንደሚያቀኑ፣ በጉዟቸውም ከአውሮፓ ሕብረ አገራት ጋር በኢትዮጵያ ወቅትዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ይፋ አድርጓል።

ማይክ ሀመር በስዊድን ስቶኮልም እና በቤልጂየም ብራስልስ በሚኖራቸው ቆይታ፤ በአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ እና ሱዳን ተዎካዮች ጋር ተገናኝተው እንደሚነጋገሩ መረጃው አመልክቷል። በስቶኮም ዓለም አቀፍ የውሃ ተቋም በተዘጋጀው የዓለም የውሃ ሳምንት መድረክ ላይ ሲሳተፉ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ እንደሚመክሩ በመረጃው ተጠቁሟል። የአባይ ጉዳይ አስመልክቶ ዝርዝር የተባለ ነገር የለም።

በቤልጂየም ብራስልስ በሚኖራቸዉ ቆይታ፤ ከአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ ተዎካዮች ጋር ተገናኝተው ኅብረቱ እና አሜሪካ በኢትዮጵያ በአማራ እና በኦሮምያ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በሚቻልበትና ሰላማዊ ሰዎችን በመጠበቅ ዙሪያ ይወያያሉ ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በተጨማሪም በፕሪቶሪያ የተፈረመዉ የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በሚደረግበት ሁኔታ ከህብረቱ አገራት ጋር እንደሞነጋገሩ መረጃው አመልክቷል። ይሁን እንጂ ዝርዝር አጀንዳዎችን አልጠቀሰም። በተደጋጋሚ አሜሪካ የፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም አስታካ የምታነሳው ሁሉም ነገር ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት የሚል እንደሆነ ይታወቃል። የትግራይ አዲሱ መሪ አቶ ጌታቸውም ይህንኑ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማል። አሁን ላይ በአማራ ክልል የተነሳው ጦርነትና ” መከላከያ ከክልሉ ይውጣ” የሚለው መፈክር ” የያዝነውን እንዳያሳጣን” ሲሉ እርጋታ የጠየቁትን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ንግግር የሚያስታውስ ሆኗል። ከዚህ ጎን ለጎን ፍትሕ እና ተጠያቂነትን በማስፈን ዙሪያም ከኢትዮጵያ አመራሮች ጋር እንደሚወያዩ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ በመግለጫው ገልጿል። መንግስት የፍትህ ሚኒስቴር ያዘጋጀውን ሰነድ በማዘጋጀት ለተጠያቂነቱና ፍትህን የማስፈኑንን ስራ መጀመሩን ማስታወቁ አይዘነጋም።

አሜሪካ የአማራ ሃይሎች እያለች ከትግራይ ምዕራባዊ ግዛት እንዲወጡ በተደጋጋሚ ስትጠይቅ መቆየቷ ይታወሳል። አሁን ላይ ሃመር ከመንግስት ሃይሎች ጋር ይህንኑ አስመልክተው እንደሚወያዩ ከመገለጹ ውጪ ዝርዝር የተባለ ነገር የለም።

በሌላ ዜና የኢትዮጵያ ብሄራዊ የንግግር ኮሚሽንን ጨምሮ ለጊዜው ስማቸው ይፋ ያልሆኑ አካላት በአማራ ክልል የተነሳውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት እንዲቻል መንቀስቀሳቸው ሰሞኑንን ተሰምቷል። ከታጣቂዎቹም መካከል የተወሰኑት እርቅ አድርገው መግባት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። የክልሉ መንግስትም ሆነ የፌደራሉ ይህ ነው ብለው በግልጽ ዝርዝር ጉዳይ ባያስቀምጡም ለሰላምና ድርድር በራቸው ክፍት መሆኑን ሲያስታውቁ ነበር። በመንግስትና መሳሪያ ባነገቡት ሃይሎች መካከል እርቅ እንዲወርድ ህዝብም ፍላጎቱ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ተሰምቷል።


Via addismaleda

Exit mobile version