Site icon ETHIO12.COM

የ”አማራ ሃይሎች ትግል” የመሪዎች ማንነት ጉዳይ ከወዲሁ ውዝግብ ማስተናገድ ጀመረ፤ አንዳርጋቸው ጽጌ “የሻዕቢያ አጀንዳ አስፈጻሚ”

አቶ አንዳርጋቸው የሞት ፍርድ ከሚጠባበቁበት እስር ቤት ወጥተው ከቤተሰቦቻቸውና ፍትህ ወዳ ዜጎች ጋር በተገናኙበት ወቅት የተነሱት ምስል ነው። ይህን ምስል የሚያስታውሱ ስለምን አቶ አንዳርጋቸው በተደጋጋሚ ከሚዋኙበት የትጥቅ ትግል ራሳቸውን አይቅቡም? የሳቸው ቤተሰቦችና ልጆች " አባታችንን ለቀቁልን፣ አስለቅቁልን" እያሉ ሲጮሁ እንደነበረው ሁሉ ሌሎች ህጻናት ቤተሰብ አልባ የሚሆኑበት ትግል ውስጥ ስለምን ይሳተፋሉ? አርጁ አይበቃቸውም ሲሉ ብዙዎች ያዝኑባቸዋል።

ጠብመንጃ ካነሱት መካከል ከመንግስት ጋር ለመነጋገርና በሰላም ወደ መደበኛ ህይወት ለመመለስ ፍላጎት ያላቸው መኖራቸው ታውቋል፤ “አመጹ የያዝነውን ያሳጣናል” የሚሉ ሃይሎች ባደረጉት ጥረት በሰላማዊ ንግግር ችግሩን ለመቅረፍ የተጀመረው እንቅስቅሴ መስመር እየያዘ መምጣቱ ” መሪ እኔ ነኝ” ለሚለው አለመግባባት ዋና ምክንያት እንደሆነ እየተነገረ ነው።

“መነሻችንን አማራ መዳረሻችንን ኢትዮጵያ አድርገን የአማራ ህዝባዊ ግንባር መስርተናል” ሲል ታጋይ እስክንድር ነጋ ይፋ ላደረገው ድርጅት ወይም ፋኖ ለሚባለው ትግል መሪ ለመሆን ከወዲሁ የሚዲያ ዘመቻና ቡድን የማበጀት፣ እንዲሁም ለመሪነት ወደፊት እየመጡ ላሉት እውቅና የመስተትና የመከልከል ቅስቀሳ እየተካሄደ ነው። አቶ አንዳርጋቸው የሻዕቢያ አጀንዳ አስፈጻሚ እንደሆኑ በመግለጽ የሚተቿቸው በዝተዋል።

የተለያዩ ከተሞችን ተቆጣጥሮ የነበረውና በአማራ ክልል የራሱን መዋቅር ዘርግቶ ክልሉን ለመረከብ ቋፍ እንደደረሰ ሲነገርለት የነበረው እንቅስቃሴ አሁን ላይ መልኩን ቀይሯል። ትግሉን እንደሚመሩ የሚናገሩ ” ሆን ብለን ነው ከተሞችን የለቀቅነው” በሚል ቢያስታውቁም፣ አሁን ላይ እንደሚሰማው ከሆነ በገጠር ሳይቀር ፈርሶ የነበረው የመንግስት መዋቅር ዳግም እየተዋቀረ መሆኑንን ነው።

መሬት ላይ ያለው ጦርነት “መነሻችንን አማራ መዳረሻችንን ኢትዮጵያ” ለሚለው ከውጭ በሻለቃ ዳዊት፣ በአገር ቤት በእስክንድር ነጋ ለሚመራው የአማራ ህዝባዊ ግንባር ምን ያህል ድል እንዳስገኘ በግልጽ የሚወጡ መረጃዎች የሉም። ባለፈው ሳምንት ” ቅጽበታዊ የፋኖ አንጸባራቂ ድል ይደገማል” በሚል በሁለት የዲሲ ነዋሪዎች ባለቤትነት በሚመራው የመረጃ ቲቪ ተገልጾ ነበር። ይሁን እንጂ እስካሁን ኦፕሬሽኑ ስላስገኘው ድልም ይሁን የተለየ ዜና ይኸው በሻዕቢያ የሚደገፍ ነው የሚባለው መረጃ ቲቪ ያለው ነገር የለም። ይልቁኑም እነ አንዳርጋቸው ጽጌን ” ወዴት ጠጋ ጠጋ” አይነት ነቀፌታ የያዘ መረጃ በዚሁ ሚዲያ የሚሳተፉ እያቀረቡ ነው።

የ360 ዩቲዩብ ተናጋሪዎች አንዳርጋቸው ጽጌ “አርፈው የጥሞና ጊዜ ቢወስዱ ይሻላሸዋል” ሲሉ አላግጠውባቸዋል። ከመሳይ መኮንን ጋር ያደረጉትን ውይይት አንተርሰው 360ዎች “ይቅርታ ማድረግ ጥሩ ነው። ግን የአማራ መሪ ነኝ ማለት አይቻልም” ሲሉ “ቅሌታም በለዋቸዋል። “አደናግራቸው” ሲሉ አቶ አንዳርጋቸውን የዘነጠሉት የ360 ተቺዎች ” መሳይን ተወው” ሲሉ አበሻቅጠውታል። የብልጽግና ገረድ እንደሆነበር ጠቁመው አንድ ላይ በመስፈር የአማራ ትግል ውስጥ ስፍራ የለሽ እንደሆኑ ገልጸዋል።

እነ መሳይና ሌሎች የ1997 ዓም የቅንጅት ወቅት የህዝብ ትግልና ድምጽ “ነፍሰ ገዳይ” በሚል የሚተቹት የሚዲያ ሰዎች ” ጋዜጠኞች” “መሪ ነን” ባይሉም፣ አማራ ክልል ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ የግላቸው በማድረግ ልክ የግንቦት ሰባትን እንቅስቃሴ ሲመሩ እንደነበር ለመምራት ሙከራ እያደረጉ ሰንብተዋል።

የትግራይ ሕዝብ ነጽ አውጪ ግንባር ወረራ በፈጸመበት ወቅት የኢትዮጵያን ሳይሆን የሻዕቢያን አጀንዳ ይዘው መከላከያን አጅበው እንደነበር አሁን ላይ መረጃ የወጣባቸው የእነ መሳይ ቡድን ከእነ አቶ አንዳርጋቸው ጋር መግጠማቸው ቀደም ሲል የህ የሚዲያ ሃይል ከሻዕቢያ ጋር ገጥሟል ሲባል የነበረውን መረጃው አጠናክሮታል። ጉዳዩን የሚከታተሉ እንደሚሉት አቶ አንዳርጋቸው የሻዕቢያ የስለላ መዋቅር አባል በመሆናቸው እሳቸውን ወደፊት የማምጣት ዓላማ የሻዕቢያ አጀንዳ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም።

እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት አቶ አንዳርጋቸው ከመሳይ መኮንን ጋር ሲወያዩ የሚያቀርቡት መረጃ ሙሉ በሙሉ የሻዕቢያ የስለላ መረጃ ነው። ትህነግን የሚተካ ሃይል ሻእቢያ አደራጅቶ ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር አስተሳስሮ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ይንቀሳቀስ እንደነበር የገለጹት ክፍሎች፣ መንግስት ሻዕቢያ የሚመራውና እንዳሻው የሚነዳው ሃይል ትግራይን እንዲመራ ፍላጎት ስላልነበረው አቶ አንዳርጋቸው በይፋ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን መንግስት ወደ መቃወም ማምራታቸውን ገልጸዋል።

ሻእቢያ ትግራይ ላይ እሱ ያደራጃቸውን ሃይሎች ለመትከል ከጫፍ ደርሶ በነበረበት ወቅት፣ መንግስት የፈረሰውን ደህንነት፣ መከላከይና የጸጥታ አቅም በሚገባ አደራጅቶ ስለነበር ከለከለ። አሁን ጊዜው ባለመሆኑ ለመግለጽ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ጠቅሰው እነዚሁ ወገኖች እንደሚሉት ሻእቢያ እስከ አፋር ዘልቆ የሚፈልገውን መንግስት ለመትከል መዋቅር ዘርግቶ ነበር።

የአማራ ወጣቶችን ወደ አስመራ አግዞ ሲያስለጥን የቆየው ሻዕቢያ ከትግራይ ክልል ከያዝቸው አካባቢዎች እንዲወጣ ከሰላም ስምምነቱ በሁዋላ በመንግስት መጠየቁ ለአማራ ክልል ድንገተኛ ጦርነት በፍጥነት መነሳት ዋና ምክንያት እንደሆነ የሚገልጹ ወገኖች፣ አቶ አንዳርጋቸው አሁን በይፋ የአማራውን ትግል ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረቡት ከዚሁ የሻዕቢያ ፍላጎት አንጻር መሆኑን ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሳይፈተሹ እየወጡ ይገቡ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ትህነግ ወደ ትግራይ ሲሸሽ የስለላውን መዋቅርና ሙሉ የጸጥታ መረብ ይዞ በመሄዱ አዲስ አበባ ገብተው ከነበሩ የሻዕቢያ የስለላ ሰዎች ጋር አብረው ይሰሩ እንደነበር የሚያውቁ ገልጸዋል። ኦሮሞ እንደሆኑ በራሳቸው መጽሃፍ ጽፈው ለውጡን ሲያሞካሹ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ” ካልተለቀቁ በስተቀር ስራዬን እለቃለሁ” በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ህይወታቸውን ያተረፉላቸው አቶ አንዳርጋቸው ከሻዕቢያ ጋር ያላቸው ቁርኝት ከመንግስት ጋር እንዳላስማማቸው በቂ መረጃዎች እያደር እንደሚወጡ ገልጸዋል።

እነ መሳይም ሆኑ ሌሎች የዩቲዩብ ሚዲያዎች 360 እና መረጃ ቲቪ እንዲሁም የጀርመኑ ዘመድኩን እያነሱባቸው ላለው ተቃውሞና ” የባንዳነት” ፍረጃ እስካሁን ያሉት ነገር የለም። ትህነግ አማራ ክልልን በወረር ወቅት “አያገባንም” በሚል መንግስት ጦርነቱን ለመቀልበስ ከህዝብ ጋር ያደረገውን ርብርብ ሲያንቋሽሹ የነበሩት የ360 ፊት አውራሪዎች የአማራ ክልል ብቸኛ ወኪል አድርገው ራሳቸውን የሾሙበት አግባብም ለብዙዎች ግልጽ አይደለም።

ይልቁኑም አሁን ላይ የሚሰማ ” አማራን ካለበት ችግር የሚያወጡ ጠቢብ ፖለቲከኞች እንዴት ጠፉ” የሚለው ጥያቄ ነው። የአማራ ክልል ፖለቲካ እጅግ ስሜታዊ፣ ሌሎች የህብረትሰብ ክፍሎችን የሚያገል፣ ኦሮሞን በጅምላ የሚፈርጅና በየክልሉ ተበትነው ለሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ስጋት እንደሆነ የሚጠቅሱ ” አማራ ክልልን በሰከነ ፖለቲካ የሚመሩና የሚያታግሉ መጥፋታቸው ክልሉን ማንም ዳንሰኛና አሸብሻቢ፣ እዚህ ግባ የሚባል እውቀት የሌላቸው፣ የቆሸሸ የጀርባ ታሪክ ያላቸው፣ ሳያጣሩ በሚለፈለፉ አክቲቪስቶች እንዲመራ አድርጎታል” ሲሉ ሃዘናቸውን ይገልጻሉ።

የአማራን ፖለቲካ በሰላማዊ አግባብ ለማበጀት፣ በአማራ ህዝብ ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃትና ግፍ ለማስቆም ሁሉም ህዝብ የሚሳተፍበት ትግል እንዲደረግ አስበው እየተንቀሳቀሱ ያሉትን ሃብታሙ አያሌው ” ይህ ሁሉ መስዋዕትነት ከተከፈለ በሁዋላ ከብልጽግና ኦሮሙማ ጋር ለመደረደር የምትንቀሳቀሱና እንዳራድራለን የምትሉ ባለሃብቶች አቁሙ” በሚል ንብረታቸው ችግር ውስጥ እንደሚገባ ስም ጠቅሶ ማሳሰቢያ መስጠቱን በማመልከት ክልሉ ለማረጋጋት ጥረት የሚያደርጉ ወገኖች እንዴት ማስፈራሪያ እንደሚቀርብባቸው አሳይተዋል።


Exit mobile version