Site icon ETHIO12.COM

የአቶ ተስፋዬ ጌታቸው፣የዶ/ር አምባቸው መኮነን፣ አቶ ምግባሩ ከበደ እና አቶ እዘዝ ዋሴ አጭር የህይወት ታሪክ

አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ከአባታቸው ከአቶ ጌታቸው ተማች፣ ከእናታቸው ከወ/ሮ ይታሹ ጥጋቡ የካቲት 21 ቀን 1962 ዓ.ም በቀድሞው ጐንደር ክፍለ ሃገር፤ ጋይንት አውራጃ በአሁኑ የደ/ጐንደር አስተዳደር ዞን ስማዳ ወረዳ ልዩ ስሙ አጅ ቀበሌ እንደተወለዱ የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

አቶ ተስፋየ የ1ኛ ደረጃ ትምህርቻቸውን በአጅ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የመለስተኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በታገል ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቀዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርታቸውንም በኢትዮጵያ ሲቨል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በመከታተል በልማት አስተዳደር (Development Administration) የመጀመሪያ ዲግሪ፤ አሜሪካ አገር ካሊፎሪኒያ ከሚኘው የአዙዛ ፖሳፊክ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በተቋም አመራር (Organizational Leadership) በከፍተኛ ማዕረግ መመረቃቸውን ከህይዎት ታሪካቸው ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

አቶ ተስፋዬ ጌታቸው የቀድሞውን የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴንን) የአሁኑ ብአዴንን ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ በመቀላቀል በትጥቅ ትግሉ ወሳኝ የሆነ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎችም አገልግለዋል፡፡

ከነዚህም ውስጥ ዋና ዋናዎቹ፤
– ከ1982 -1984 ዓ.ም በክፍለ ህዝብነት፤
– ከ1985-1987 ዓ.ም በዋግ ኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የአበርገሌ ወረዳ አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ፤
-ከ1988- 199ዐ ዓ.ም የደቡብ ጐንደር አስተዳደር ዞን የአቅም ግንባታ ኃላፊ፤
– ከ199ዐ-1994 ዓ.ም የደቡብ ጐንደር አስተዳደር ዞን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የማህበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ፤
– ከ1994-1996 ዓ.ም የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የህዝብ ተሳትፎና አደረጃጀት ቢሮ የህዝብ አደረጃጀት ጉዳይ ኤክስፐርት፣
– ከ1996-1998 ዓ.ም የብአዴን ኦዲት ኮሚሽን ጽ/ቤት ኃላፊ፤
– ከ1998 -2ዐዐ3 ዓ.ም በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የጥቃቅን፣ አነስተኛ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ ስራዎች ማስፋፊያ ኤጀንሲ ኃላፊ፤
– ከ2ዐዐ3-2ዐዐ6 ዓ.ም በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የንግድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ፤
– ከ2ዐዐ6-2ዐዐ8 ዓ.ም በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የንግድ ቢሮ ኃላፊ፤
– ከ2ዐዐ8-2ዐ1ዐ ዓ.ም ድረስ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በምክትል ርዕሠ መስተዳድር ማዕረግ የንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ፤
– ከሚያዚያ 2ዐ1ዐ ዓ.ም ጀምሮ ህይዎታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በምክትል ርዕሠ መስተዳደር ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ የህዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት አማካሪና የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ.ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ከመንግስት ኃላፊነት በተጨማሪ፡-
– ከ 1999 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት 11 ዓመታት የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፣
– ከ 2007 ዓ.ም ጀምሮ የብአዴን እና የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የኢህአዴግ ምክር ቤት አባል በመሆን በከፍተኛ የድርጅት ኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ ጌታቸው የክልሉን ህዝብ የዘመናት የኢንዱስትሪ ልማት ጥያቄ ለመመለስ የክልሉን ተወላጅ ባለሃብቶችና የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በማስተባበር ከፍተኛ ተስፋ የሚጣልበትን የአባይ ኢንዱስትሪያል አክሲዮን ማህበር እንዲቋቋም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ መስራታቸውም በህይዎት ታሪካቸው ተመልክቷል፡፡

አቶ ተስፋዬ ጌታቸው በክልሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲቋቋሙ፤ በየአካባቢው የኢንዱስትሪ መንደሮች እንዲመሰረቱ እና በአጠቃላይ የገጠር ኢንዱስትራላይዜሽን እንዲስፋፋም አስተዋጽኦ ማበርከታቸውም በህይዎት ታሪካቸው ተመልክቷል፡፡

በቅርቡም ባጋጠማቸው የጤና መታወክ ለህክምና ክትትል አሜሪካን አገር ወደሚገኘው ጆርጅ ዋሺንግተን ሆስፒታል በመሄድ በመንግስት፤ በቤተሰቦቻቸውና በጓደኞቻቸው ድጋፍ በህክምና እየተረዱ በነበረበት ወቅት በድንገት ሀምሌ 18 ቀን 2ዐ1ዐ ዓ.ም በተወለዱ በ48 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ ጌታቸው ባለትዳርና የሶስት ወንዶች እና የአንድ ሴት ልጅ አባት ነበሩ፡፡
የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅትም በአቶ ተስፋዬ ጌታቸው ድንገተኛ ሞት የተሰማውን ሃዘን ይገልፃል፡፡ ለቤተሰቦቻቸው፤ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ፣ ለስራ ባልደረቦቻቸው፣ ለጓደኞቻቸው እና ለክልሉ ህዝብ መፅናናትን ይመኛል፡፡

ዶ/ር አምባቸው መኮንን ከአባታቸው ከአቶ መኮንን ሲሳይ እና ከእናታቸው ወ/ሮ አማን እንደብልሃቱ በቀድሞው ጋይንት አውራጃ በአሁኑ የደቡብ ጎንደር ዞን ታች ጋይንት ወረዳ ልዩ ስሙ አቄቶ ኪዳነማርያም ቀበሌ ተወለዱ፡፡

እድሜያቸው ለትምህርት እንንደሰረ አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአቄቶ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፣ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በታጠቅ ለስራ መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በንፋስ መውጫ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እየተከታተሉ ባሉበት ወቅት በወቅቱ የነበረውን ስርዐት ጭቆና በመቃወም ወደትግል በመግባት ትምህርታቸውን ከሰላምና መረጋጋት በኋላ አጠናቀዋል፡፡

ዶ/ር አምባቸው መኮንን የከፍተኛ ትምህርታቸውን በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በምጣኔ ሀብት ሳይንስ ኢኮኖሚክስ፣ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በሁለት ከፍተኛ የውጪ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ማለትም በደቡብ ኮርያ ‘’ስኩል ኦፍ ፐብሊክ ፖሊሲ ኤንድ ማኔጅመንት’’ እና በእንግሊዝ ሀገር ‘’ኬንት ዩኒቨርሲቲ በማስተርስ ኦፍ ሳይንስ ኢን ኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኤንድ ኢኮኖሚክ ዴቬሎፕመንት’’ እጅግ በከፍተኛ ውጤት ተመርቀዋል፡፡ የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በእንግሊዝ ሀገር ኬንት ዩኒቨርሲቲ በምጣኔ ሀብት ሳይንስ በከፍተኛ ማዕረግ አጠናቀዋል፡፡

ዶ/ር አምባቸው መኮንን በትምህርት ክትትላቸው ፈጣን ተማሪ የነበሩ ሲሆን ትምህርታቸውን በተከታተሉባቸው ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተሸላሚና ተወዳዳሪ ነበሩ፡፡

ዶ/ር አምባቸው መኮንን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ በነበረበት ወቅት በወቅቱ የነበረውን ጭቆና በመቃወምና የህዝባዊ ትግሉ አካል በመሆን በለጋ እድሜያቸው የቀድሞውን የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ኢህዴን/ የአሁኑን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ በመቀላቀል ለትጥቅ ትግሉ ወሳኝ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡

በሽግግር መንግስቱ ወቅትና ህዝባዊ መንግስት ከተመሰረተ በኋላ በድርጅትና በመንግስት የተሰጧቸውን ሀላፊነቶች በቁርጠኝነትና በታማኝነት አገልግለዋል፡፡

ዶ/ር አምባቸው መኮንን ባለፉት 29 አመታት ከክፍለ ህዝብነት እስከ ከፍተኛ የመንግስትና የህዝብ ሀላፊነት ያለመታከት አመራር ሰጥተዋል፡፡

ከ1982-1988 ዓ.ም በደቡብ ጎንደር ዞን ታች ጋይንትና ፋርጣ ወረዳዎች፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማበርና ሀገረማርያም ከሰም ወረዳዎች በክፍለ ህዝብነት በመስራት ህዝቡን በማደራጀትና ለመብትና ጥቅሞቹ እንዲታገል አድርገዋል፡፡

ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት አመታት የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግስት ስራ አመራር ተቋም ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል፡፡

በወቅቱ ፈታኝ የነበረውን የክልሉን መንግስት የመፈፀም አቅም ለመገንባትና የፈፃሚ አካላትን አቅም ለማሳደግ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ብቃት ከፍ ለማድረግ ጉልህ አመራር ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር አምባቸው መኮንን በደቡብ ኮርያና እንግሊዝ የማስተርስ እና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከተከታተሉ በኋላ አቅማቸውን ይበልጥ በማሻሻል ከክልል እስከ ፌደራል መንግስት የሀላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል፡፡

በ1993 ዓ.ም ከደቡብ ኮርያ እንደተመለሱ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ንግድ ቢሮ ም/ቢሮ ሀላፊ በመሆን የክልሉ ንግድ ስርዐት ዘመናዊነትን እንዲላበስ በማስቻል ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል፡፡

ከ1994-1995 ዓ.ም የቀድሞው ብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅ/ቤት ሀላፊ በመሆን ወቅቱ የሚጠይቀውን አመራር ሰጥተዋል፡፡ ለአንድ አመት ያህልም የጥረት ኮርፖሬት ም/ስራ አስፈፃሚ በመሆን አመራር ሰጥተዋል፡

ከ1996-1998 ዓ.ም የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሀላፊ በመሆን በክልሉ የተጀመረውን የንግድ ሪፎርም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ክልሉ ለኢንቨስትመንት ምቹ እንዲሆን አመራር ሰጥተዋል፡፡

የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በምጣኔ ሀብት ሳይንስ አጠናቀው ከተመለሱ በኋላም ከ2003-2005 ዓ.ም የአማራ መልሶ መቋቋም ልማት ድርጅት /አመልድ/ ዋና ዳይሬክተር በመሆን የግብርና ስራ ፣ምግብ ዋስትና፣ የተፈጥሮ ሀብት እና መሰል ስራዎችን ሰርተዋል፡፡

ከ2006-2008 ዓ.ም በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ ሆነው አመራር ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር አምባቸው መኮንን የክልሉን ከተማ ልማት ቢሮ በመሩበት ወቅት ዛሬ በአማራ ክልል ከተሞች ተሞክሮ የሚወሰድባቸው በማህበራት የተደራጁ እና የየከተማውን ፕላን ጠብቀው የለሙ መኖሪያ ቤቶች እውን እንዲሆኑ በማድረግ አሻራቸውን አሳልፈዋል፡፡

ዶ/ር አምባቸው መኮንን ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በኢፌዲሪ የከተማ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር እና በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚንስትሩ የመሰረተ ልማት አማካሪ በመሆን የሚወዷትን ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን በቅንነትና በታማኝነት አገልግለዋል፡፡

ከየካቲት 29/2011 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉን ህዝብ ጥያቄ በመቀበል የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በመሰየም ህዝባቸውን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡

ዶ/ር አምባቸው መኮንን የታች ጋይንት ወረዳ ህዝብን በመወከል የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ም/ቤት አባል እንዲሁም የአማራን ህዝብ በመወከል የኤፌዲሪ ፌዴሬሽን ም/ቤት አባል አባል በመሆን የተጣለባውን ህዝባዊ አደራ በብቃት ተወጥተዋል፡፡

ዶ/ር አምባቸው መኮንን ከመንግስት ሀላፊነታቸው በተጨማሪ ላለፉት አመታት የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ የኢህአዴግ ም/ቤት አባልና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአዴፓ ምክትል ሊቀመንበር በመሆን በከፍተኛ የድርጅት ሀላፊነት ሰርተዋል፡፡

ዶ/ር አምባቸው መኮንን የልማት ድርጅቶችን ማለትም የአመልድ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የሰሩ ሲሆን ከፌደራል ተቋማትም የኢትዮጵያ ምድር ባቡር፣ የኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ መብራት ሀይልን በቦርድ አባልነት እንዲሁም የጎንደር ዩኒቨርሲቲና የደብረታቦር ብረታብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽንን በቦርድ ሰብሳቢነት መርተዋል፡፡

በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሌሎች የትግል ጓዶቻቸው ጋር በመሆን በከፍተኛ ትግልና ቁርጠኝነት አመራር ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር አምባቸው መኮንን በአሁኑ ወቅት በሀገራችንና ክልላችን እየተካሄደ ባለው የለውጥ እንቅስቃሴ ከትግል ጓዶቻቸውና ከህዝቡ ጋር በመሆን የሀገሪቱንና የክልሉን ህዝቦች ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የዜጎች ሰብዐዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲከበር የታገሉ የህዝብ ልጅ ናቸው፡፡

ዶ/ር አምባቸው መኮንን ባለፉት አመታት በገጠሙ የፖለቲካ ብልሽቶች ምክንያት ያጋጠሙ የሰብዐዊ መብት ጥሰቶች እንዲታረሙ በፅናትና በከፍተኛ ህዝባዊ ስሜት ከትግል አጋሮቻቸው ጋር በመሆን በርካቶች ከእስር እንዲፈቱ ታግለዋል፡፡

ዶ/ር አምባቸው መኮንን ሰው አፍቃሪና ሀገርና ህዝባቸውን የሚያስቀድሙ የጠንካራ ስብዕና ባለቤት ነበሩ፡፡ የህዝቡን የለውጥ ፍላጎትና ጥሪ ተቀብለው ከነበሩበት ሀላፊነት የክልሉን ህዝብ ለማገልገል ከየካቲት 29/2011 ዓ.ም ጀምሮ በርዕሰ መስተዳድርነት ተሰይመው በሀገሪቱን በክልሉ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ሌትከቀን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

ዶ/ር አምባቸው መኮንን ቅዳሜ ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በክልሉ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ፅ/ቤት የርዕሰ መስተዳድር ም/ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ስብሰባ በነበሩበት በደረሰ ጥቃት ከሌሎች ሁለት የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በጥይት ተመተው በተወለዱ በ48 አመታቸው ተሰውተዋል፡፡ ዶ/ር አምባቸው መኮንን ባለትዳርና የአራት ሴቶችና የአንድ ወንድ ልጅ አባትም ነበሩ፡፡

የ አቶ ምግባሩ ከበደ የህይወት ታሪክ ባጭሩ!
አቶ ምግባሩ ከበደ በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ወረዳ ወፍ አርክስ ቀበሌ በ1966 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ የወረዳ እና ዞን ዐቃቢ ሕግ ባለሙያነት ደግሞ የሥራ ሕይወታቸው መጀመሪያ ነው፡፡
በኋላም የምሥራቅ ጎጃም ዞን አቅም ግንባታ መምሪያ ኃላፊ፣ የደብረ ማርቆስ ከተማ ከንቲባ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ፣ የአዴፓ የገጠር ፖለቲካና አደረጃጀት አማካሪ፣ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የርዕሰ መስተዳደሩ አማካሪ እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደረጃ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኃላፊ በመሆን ሕይወታው እስካለፈበት ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሕዝባቸውን አገልግለዋል፡፡
አቶ ምግባሩ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 አካባቢ በአማራ ክልል በተካውደ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በታጣቂዎች ተመትተው በሕክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ረፋድ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
አቶ ምግባሩ ከበደ በሕይወት የሦስት ወንድ እና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ፡፡ ለመላው ቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለትግል አጋሮቻቸው መጽናናትን እንመኛለን፡፡
አቶ ምግባሩ ከበደ አብረዋቸው በጥቃቱ ከተሰውት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንንና ከርዕሰ መስተዳድሩ የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴ ጋር ሰኔ 19 ቀን 2011ዓ.ም በባሕር ዳር ዓባይ ማዶ ገብርኤል ሥርዓተ ቀብራቸው ተ ፈጸማል፡፡

የአቶ እዘዝ ዋሴ የህይወት ታሪክ

አቶ እዘዝ ዋሴ ከአባታቸው ዋሴ መንግስቱ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ የውብዳር ቢወጣ በ1957 ዓ.ም በቀድሞ ጎንደር ክፍለ ሃገር በደብረታቦር አውራጃ ፤በአሁኑ ደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ በስኳ በርጉት ቀበሌ ተወለዱ ።የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውንም በተወለዱበት አካባቢ የቅዳሜ ገበያ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፤የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመካነ እየሱስ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።

አቶ እዘዝ ዋሴ የመደበኛ ትምህርታቸውን ከማጠናቀቃቸው በፊት በወቅቱ የነበረውን የደርግ አገዛዝ በመቃወም ትምህርታቸውን አቋርጠው ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ ከመሰል ጓደኞቻቸው ጋር ህዝባዊ ትግሉን ዳር እንዲደርስ የበኩላቸውን አበርክተዋል፡፡ በሽግግሩ ወቅት በክፍለ ህዝብነት በሰሩበት በእስቴ ወረዳ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በቁርጠኝነትና በታማኝነት በመወጣት በወቅቱ ደፍርሶ የነበረውን የአካባቢውን ሰላም በማረጋጋት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

የሃገራችን ሰላም ተረጋግቶ መደበኛውን ሥራ መስራት ሲጀመር ከዚህ በፊት አቋርጠውት የነበረውን ትምህርታቸውን በመቀጠል እስከ ማስትሬት ዲግሪ በመማር የእውቀት ድረስ ትምህርታቸውን በመከታተል የእውቀት አድማሳቸውን አስፍተዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ ማኔጅመንትና የማስተርስ ዲግሪያቸውን ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አጥንተው ተመርቀዋል።

አቶ እዘዝ በደቡብ ጎንደር አስተዳደር እስቴ ወረዳ በልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተው፤ በነበራቸው የህዝብ ተቀባይነት ከ1998 እስከ 2002 ዓ.ም የእስቴ ወረዳን ህዝብ ወክለው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በአባልነት አገልግለዋል።አቶ እዘዝ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም ቀን ከለሊት የሚተጉ፤ ችግር ነው ብለው ያመኑበትን ነገር ያለምንም ፍርሃት ፊት ለፊት የሚታገሉ የቁርጥ ቀን ከአማራ ህዝብ አብራክ የወጡ የህዝብ ልጅ ነበሩ።

ከምርጫ 2002 ማግስት የክልሉን ህዝብና አካባቢውን ለማገልገል በነበራቸው ቁርጠኝነት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመልሰው ከ2003 ዓ.ም እስከ 04 ዓ.ም የደቡብ ጎንደር አስተዳደር ዞን የብአዴን ጽህፈት ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል ።ከ2004 እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ በመሆን አገልግለዋል። በዚህ ወቅት የዞኑን ህዝብ የሰላም የልማትና የዴሞክራሲ ተጠቃሚ ለማድረግ የሰራቸው ስራዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ በተለይ መላ የዞኑን ህዝብ በማነቃነቅ የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ ፤የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራና በሌሎች ስራዎች የዞኑ አፈጻጸም እየተሻለና ዞኑን ተሸላሚ በማድረግ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ የቻሉ የህዝብ ልጅ ናቸው ።

አቶ እዘዝ ዋሴ ደፋርና ጀግና ነበሩ ።ታማኝ ታጋይም ነበሩ ።ለአላማቸው ጽኑ ታጋይ ነበሩ ።የትግል ጓደኞቻቸውን መቼም የማይረሱ ከወደቁበት ፈልገው የሚያነሱ የዓላማ ሰው ነበሩ ለሚያምኑበት አላማ ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ ቆራጥ የህዝብ ልጅ ነበሩ። ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደርና አጋጥሞ የነበረው አለመረጋጋት ወደ ሰላም ለመመለስ የሚወዷቸውን ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ወደ አካባቢው በመሄድ

ተልኳቸውን ከሥራ ባልደረባቸው ከገነቡት ከአቶ ምግባሩ ከበደ ጋር በመሆን በብቃት የተወጡና በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ አክብሮት የተቸራቸው እንቁ ሰው ነበሩ ።

አቶ እዘዝ አሁን በክልላችንና በሃገራችን ለታየው ለውጥ ከትግል ጓዶቻቸው ጋር በመሆን ፊት ለፊት የሚሰማቸውን በአደባባይ የታገሉ ፤ለውጡ መሬት እንዲነካ በየመሃሉ የሚያጋጥሙ እንቅፋቶች መልክ እንዲይዙ ከትግል ጓዶቻቸው ጋር በመሆን ታግለዋል። ከ2009 እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የአስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው እንዲያገለግሉ በኃላፊነት በታማኝነት፣በቆራጥነትና በጀግንነት መርተዋል ።መሪ ድርጅቱ አዴፓ ታሪካዊ የሆነውን የ12 ኛውን መደበኛ ጉባዔ ካካሄደ በኋላ የአዴፓን ማዕከላዊ ጽህፈት ቤትን በጠንካራና በቁርጠኛ የአማራ ልጆች እንዲመራ በማሰብ ከጥቅምት 2011 ዓ.ም ጀምሮ መስዋዕትነት እስከ ከፈሉበት ድረስ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አዴፓ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊና የርዕሰ መስተዳድሩ የአደረጃጀት አማካሪ በመሆን በተለመደው ህዝባዊ ባህሪያቸው ለአማራና ለኢትዮጵያ ህዝቦች ጥቅም መረጋገጥ ታግለዋል።

አቶ እዘዝ ዋሴ ለስራቸው እጅግ ታታሪ ከመሆናቸው የተነሳ ሙሉ ጊዜያቸውን ለስራ የሚያውሉ በመሆኑ ጠዋት ለስራ ሲወጡ የተኙ ልጆቻቸው ማታ ከስራ አምሽተው ሲመለሱ ተኝተው ስለሚያገኟቸው ለልጆቻቸው ራሱ ሙሉ ጊዜ ሳይሰጡ መስዋዕት የሆኑ አባት ነበሩ። አቶ እዘዝ በአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ተመድበው በክልሉና በሃገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል ያለምንም እረፍት ሌት ተቀን እየሰሩ ባሉበት በክልሉና በሃገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ባሉበት የክልሉን መንግሥት በሃይል ለማስወገድ ፣ክልሉንና የሃገራችንን ኢትዮጵያ የከፋ አደጋ ለመጣል ታስቦ የተቀነባበረውና ተሞክሮ በከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሴራ ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ በክልሉ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት የመስተዳድሩ ምክር ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ስብሰባ ላይ በነበሩበት በተደረገ ጥቃት ከሌሎች ሁለት ባልደረቦቻቸው ከዶክተር አምባቸው መኮንንና አቶ ምግባሩ ከበደ ጋር በጥይት ተመትተው በ48 ዓመታቸው ተሰውተዋል። አቶ እዘዝ ዋሴ ባለትዳርና የሁለት ሴቶችና የሦስት ወንድ ልጆች አባት ነበሩ።

ባሕር ዳር፡ሐምሌ 19/2010 ዓ/ም(አብመድ)

Exit mobile version