ETHIO12.COM

ገና እንኮራለን!!የኢትዮጵያ ዋላዎች በቡዳቴስት ማራቶን ታላቅነታቸውን አስመሰከሩ፤”እግሬ አበጠ፣ መሮጥም መተንፈስም አቃተኝ”

በሃንጋሪ የከተሙት የኢትዮጵያ የሴቶች ማራቶን ተወዳዳሪዎች እንደ ዋላ እየተስፈነጠሩ ዓለም የኢትዮጵያን ጀግንነት እንዲያከብር አድርገዋል። ኢትዮጵያ አሸንፋለች። ድሉ በኢትዮጵያ ታሪክ በማራቶን ወርቅና ብር በማሸነፍ የተገኘ ሪኮርድም ሆኗል። ገና እንኮራለን።

ይህን ድል ለማጣጣም “እግሬ አበጠ፣ መሮጥም መተንፈስም አቃተኝ” ያለውን የይስማው ድሉን የአስር ሺህ ሜርት ውድድር ገጠመኝ እንይ። ይስማው ከጎጃም ገጠር የተገኘ አዲስ አትሌት ነው። ይስማው ገና አስራ ስምንት ዓመቱ ነው። በታላላቅ ውድድር ምንም ልምድ የለውም። ኢትዮጵያ ሻምፒዮና አስር ሺህ ሮጦ ሁለተኛ ወጣ። ተመልሶ ጎጃም ሄደ። ከዛ ሲጠራ ስፔይን ማላጋ ሄዶ ማጣሪያ ሲደረግ ሶስተኛ ወጣ።

1 / 8

አሰልጣኝ ሁሴን ሽቦን ካሉበት በስልክ ስናነጋግራቸው ” ይህ ልጅ አስራ ስምንት ዓመቱ ነው። እመኑኝ ትልቅ አትሌት ይሆናል” በማለት ነው የገለጹልን። ሁሴን ሽቦ ይስማው “እግሬ አበጠ፣ መሮጥም መተንፈስም አቃተኝ …” ብሎ ከውድድሩ በሁውላ ስለገጠመው ሲያስረዳቸው እጅግ ማዘናቸው አመልክተው ” ወደፊት ትልቅ አትሌት ትሆናለህ። አይዞህ” በማለት እንዳበረታቱት ገልጸዋል።

በርካቶችን ያሳዘነው የመደረብ ጉዳይ በኢትዮጵያ ሩጫ ታሪክ የተለመደ ባሆንም ልጅ ሙቀቱን መቆጣጠር አቅቶት እግሩ አብጦ መተንፈስ ባለመቻሉ የተከሰተና ገና ታዳጊ መሆኑንን ከግምት ማስገባት አግባብ እንደሆነ አሰልጣኙ አመልክተው ግርምታቸውንም አክለዋል። ” ይገርማል” አሉ ሁሴን ሽቦ ” በልምምድ፣ ላይ የነበረው ብቃት አስገራሚ ነበር። ልምምድ ላይ የሚሰጠውን ሁሉ የሚተገብር አጓጊ አትሌት ነበር። ያጋጥማል ስፖርት ነው” በማለት ይስማው “አይዞህ ሊባልና ሊደገፍ ይገባዋል። እርግጠኛ ነኝ ነገ ያስጨፍረናል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ይህን መሰሉን ተመልካች የማይረዳውን የውድድር ሰንካ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት እንዲቻል ሚዲያዎች ትልቅ አስተዋጾ እንዳላቸው የቡዳቴስትን ዓለም ሻምፒዮና የሚከታተለው አርነ ማግኑስ ለኢትዮ 12 እንዳለው ” አትሌቲክስ ገመድ ልትበጥስ ሰኮንዶች ሲቀሩህ ድንገት ቀጥ የምትልበት ስፖርት ነው” ሲል ውጤት በሚበላሽባቸው ስፖርተኞች ላይ ብዙ ሃጢአት ማብዛት አግባብ እንዳልሆነ ያመልክታል። እሱ እንደሰማው ኢትዮጵያ የተከተለችው የምርጫ ሂደት የተሻለ ሰዓት በመሆኑ የተሻለሰ ሰዓት ስላለው ተመረጠ። አልተሳካለትም። ሙቀቱ ዲሃይድሬት ያደረገው ይመስላል ብሏል።

አርነ ቀነኒሳ በቀለ ኬንያ በተካሄደ ውድድር ሙቀቱ ዲሃይድሬት አድርጎት ወይም ውሃ ከሰውነቱ አልቆ ውድድር ሳያልቅ ያለቀ መስሎት እንዳቆመ፣ ሲጠየቅ ሙቀቱ ማሰብ እስኪያቆም ድረስ አውኮት እንደነበር ያስታውሳል። እናም በአስር ሺህ ሜትር ተደረበ የተባለው አትሌት ውድድሩን መጨረሱ በራሱ አስገራሚ ሆኖበታል። አርነ እንደሚለው ገና ስሜቱ ሲሰማው ማቋረጥ ነበረበት። ምክንያቱም ለህይወቱም አደገኛ ሊሆን ይሽላልና። ይህን ድካም በማሰብ ወደ ዛሬው የማራቶን ድል እናምራ።

በዛሬው ዕለት ስለተደረገው የሴቶች ማራቶን ውድድር እግረመንገዳቸውን የተሰማቸውን ስሜት የገለጹት ሁሴን ሽቦ፣ “ድንቅ ነው፤ አዲስ ታሪክ ነው፤ በጠዋቱ ሁለት ሜዳሊያና ታሪክ ተመዝግቧል” ብለዋል። ኢትዮጵያን አትሌቶቻችን አንደኛ እና ሁለተኛ በመሆን ተከታትለው የገቡበት የማራቶን ውድድር አገራቸውን ለሚወዱ ሁሉ የሰንበት ስጦታ ሆኖላቸዋል። እርግማንና ጸብ የሚዘራበት ማህበራዊ ሚዲያ በጠዋቱ በኢትዮጵያ ባንድሪና የደስታ ሃረጎች ደምቋል።። አትሌት አማኔ በሪሶ የወርቅ፣ ጎይተቶም ገብረስላሴ የብር ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አበርክተዋል።

ፋጡማ ሮባ በ1996 አታላንታ ኦሊምፒክ ላይ ለአፍሪካና ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የማራቶን ድል ስታበስር ድሉ ታሪክም ሆኖ ነበር። የኦሜድላ ልጅ ሻምበል ፋጡማ ሮባ የታሪክ አሻራዋ ዛሬ በቡዳፔስት በአዲስ ታሪክ ታጅቦ መጉላቱ ነገ ለሚደረገው የወንዶች ውድድር የስነልቦና ስንቅ እንደሚሆን ሁሴን ሽቦ ነገረውናል።

የዛሬው ማለዳ ውድድር እንደወትሮው ከፍተኛ ሙቀት አልነበረውም። የዓየር ንብረት መረጃ እንደሚያመለክተው ውድድሩ ሲካሄድ ከ22 እስከ 28 ዲግሪ ሴሊሸስ የሚደርስ ነበር ሙቀቱ። ውድድሩ ሊጠናቀቅ አካባቢ ሙቀቱ ከመሸመሩ ውጪ አስቸጋሪ የሚባል አልነበረም።


Fatuma Roba is an Ethiopian long-distance runner, best known for being the first African woman to win a gold medal in the women’s Olympic marathon race at the Atlanta 1996 Summer Olympics and for winning three successive Boston Marathons


በአራት ድንቅ የርቀቱ ከዋክብት ኢትዮጵያውያን ግሩም የቡድን ስራ የደመቀው ፉክክር የቁጥር የበላይነቱና ትብብሩ ትልቅ የስነልቦና የበላይነት አላብሷቸዋል። ለሁለት ሰአታት ቡድኑን ከፊት በመምራት ፀሀይ ገመቹ ትልቅ ሚና ተጫውታለች። እሷ ትልቁን ስራ ጨርሳ አቋርጣ ስትወጣም አሸናፊዋ አማኔ በሪሶና የአምናዋ ቻምፒዮን ጎተይቶም እንዲሁም ያለምዘርፍ የኋላው ውድድሩን ተቆጣጥረው ወደፊት ገፍተዋል። ውድድሩ በአረንጓዴ ጎርፍ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሲቀረው ግን ያለምዘርፍ የነሐስ ሜዳሊያ ለማጥለቅ የቻለችውን ሁሉ ጥረት አድርጋ አልተሳካላትም። ያምሆኖ የወርቅና የብር ሜዳሊያውን አማኔና ጎተይቶም በሚደንቅ ብቃት አጥልቀውታል።

ይህ በርቀቱ በታሪክ ለኢትዮጵያ ሶስተኛው ወርቅ ሲሆን በሴቶች ወርቅና ብር ሲመዘገብም የመጀመሪያ ነው። የአምና ቻምፒዮኗ ጎተይቶም ዳግም ቻምፒዮን በመሆን የኤድና ኪፕላጋትን ታሪክ የመጋራት እድል ቢኖራትም የብር ሜዳሊያ ማጥለቋ በራሱ በተከታታይ ቻምፒዮናዎች ወርቅና ብር በማጥለቅ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት አድርጓታል።

የብር ሜዳሊያው በራሱም በቻምፒዮናው ታሪክ ኢትዮጵያ በሴቶች ማራቶን ያስመዘገበችው የመጀመሪያ ነው።

ውድድሩ እጅግ ጥቂት እስኪቀረው ድረስ የታገለችው ያለምዘርፍ የነሐስ ሜዳሊያውን ብታጠልቅ ኖሮ ኢትዮጵያውያን እኤአ 2011 ዴጉ ላይ ኬንያውያን ከአንድ እስከ ሶስት በማጠናቀቅ የሰሩትን ታሪክ መጋራት ይችሉ ነበር። ያምሆኖ አሁን ያስመዘገቡት ውጤት ለአትሌቶቹም ለኢትዮጵያም እጅግ የደመቀ ወደፊት በታሪክ ሊረሳ የማይችል ነው።

Exit mobile version