Site icon ETHIO12.COM

በሰሜን ሸዋ ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው ከእገታ የተለቀቁት አባት የቀናት ሰቆቃና ምስክርነት፤ “ነጻ ልናውጣችሁ ነው” አጋቾች

“ይህ ከእናንተ የምንወስደው ገንዘብ ለትግል ይውላል” ብለው አጋቾቹ ለታገቱት አቶ ደቻሳ ነግረዋቸዋል። “አንዳንድ ጊዜ ልክ እንደ ጓደኛቸው ያዋሩኛል። ዓላማችን ይህ ነው፣ ያ ነው እያሉ ነግረው ለሕዝብ ነጻነት እንደሚታገሉም ያወራሉ። የገንዘብ ጉዳይ ሲያነሱ ግን በጣም ነው የሚያስፈራሩት።” ቢቢሲ በግልጽ ማይናገርም ስማቸው ለድህንነታቸው ሲባል የተቀየረው አቶ ደቻሳ ኦሮሞ ናቸው። ጥቅሱ ለቢቢሲ ከሰጡት እማኘት የተወሰደ ነው። እያገቱ ገንዝብ በመዝረፍ የፖለቲካ ትግልና ነጻ አውጪነት!! ሙሉውን ከስር ያንብቡ

በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ደገም፣ ኩዩ፣ ያያ ጉለሌ፣ ሂደቡ አቦቴ፣ ወረ ጃርሶ እና ደራ ወረዳዎች ታጣቂዎች የሚንቀሳቀሱባቸው ሲሆኑ በተለያየ ጊዜ ሰዎች እየታገቱ ገንዘብ አንዲከፍሉ ይጠየቃሉ።ይህ ጉዳይ በእነዚህ ወረዳዎች በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ያለ እና ከሁለት ዓመት በላይ ያስቆጠረ ነዋሪዎችን ያሳሰበ ጉዳይ ነው።

አቶ ደቻሳ*፣ ስማቸው ለደኅነንታቸው ሲባል የተቀየረ፣ አንድ ሌሊት ከቤታቸው በታጣቂዎች ተወስደው መታገታቸውን ይናገራሉ።

በታጣቂዎች ታግተው በቆዩባቸው አስር ቀናት ያሳለፉትን ሁኔታ እና እንዴት በሕይወት እንደተረፉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ደቻሳ ታጣቂዎች ከሚንቀሳቀሱባቸው ወረዳዎች በአንዱ ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን፣ በግል ሥራ ላይ የተሰማሩ ናቸው።

በገዢው ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ውስጥም ተሳትፎ እንደሌላቸው ይናገራሉ።

“እኔ የራሴን ሥራ ሰርቼ ቤተሰቤን የማስተዳድር ሰው ነኝ። እዚህ የምኖርበት አካባቢ ላይ ሰዎች በታጣቂዎች ታግተው ገንዘብ እንደሚጠየቁ እሰማ ነበር። ነገር ግን እኔ ሰላማዊ ሰው ነኝ። ፖለቲካዊ ተሳትፎ ስለሌለኝ አይነኩኝም ስለምል ተረጋግቼ ነበር የምኖረው” ይላሉ።

እኚህ ግለሰብ የሚኖሩበት ከተማ ውስጥ የሚገኙ እና ንብረት ያፈሩ ሰዎች የታጣቂዎች ሁኔታ ስለሚያሰጋቸው እየሸሹ ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል።

አቶ ደቻሳ ግን በሥራ ሁኔታቸው ምክንያት በቀያቸው መቆየት እና መኖርን መርጠው ነበር።

“የሆነ ሰው ተወሰደ፣ ይህን ያህል ገንዘብ ተጠየቀ። እከሌ ይህን ያህል ገንዘብ ከፈለ። እከሌ ደግሞ የሚከፍለው ገንዘብ ስለሌለው ተገደለ የሚሉ ወሬዎችን እንሰማለን” ይላሉ።

ታጣቂዎቹ የመጡበት ሌሊት

አቶ ደቻሳ የታገቱት ከወራት በፊት ነበር።

በየቀኑ ታጣቂዎች ሰው ያግታሉ ለሚል ወሬ ጆሯቸው አዲስ አይደለም። ይኹን አንጂ እርሳቸው ላይ ይደርሳል ብለው አስበው እንደማያውቁ ይናገራሉ።

“ሥራ ውዬ ነበር የገባሁት። ከቤተሰቦቼ ጋር አገር አማን ብለን በር ዘጋግተን ተኛን። እኩለ ሌሊት ላይ፣ ሰዓቱን በደንብ አላስታውሰውም፣ አጥሩን እንዴት አልፈው አንደገቡ አላውቅም፤ በሬ በኃይል ይንኳኳ ጀመር። ትፈለጋለህ ክፈት አሉኝ።”

ለአቶ ደቻሳ እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ በርቀት ሲሰሙት የነበረው የእገታ ወሬ ደጃፋቸው ድረስ እየዳኽ መምጣቱን የሚያረዳ ነበር።

“ትጥቅ ያላቸው ናቸው። በሩ እንደተከፈተ ወደ ቤቱ ተግተልትለው ገቡ። ‘ተነስ እንሂድ’ አሉኝ። ይህንን ጉዳይ ስለማውቀው እየታገትኩ እንደሆነ ገባኝ። ምንም ሳላንገራግር ተከትያቸው መሄድ ጀመርኩኝ።”

አቶ ደቻሳ አጋቾቻቸው በቁጥር ከሃያ እንደሚበልጡ ያስታውሳሉ። ስልካቸውን ቤት እንደገቡ እንደተቀበሏቸው ይናገራሉ።

በእኩለ ሌሊት በማያውቁት መንገድ ከታጠቁ አጋቾቻቸው ጋር አብረው ሲጓዙ አደሩ።

“እየተጓዝን ነጋ። እስከዛሬ ድረስ ቦታው የት እንደሆነ አላስታውስም። እኔን መካከል አድርገው በግራ እና በቀኝ፣ በሰልፍ ነበር የሚጓዙት። ደከመኝ ስላቸው እረፍ ይሉኛል፤ ከዚህ ውጪ ግን ዝም ብሎ ብቻ መጓዝ ነበር” ይላሉ።

ከነጋ በኋላ ታጣቂዎች በስፋት የሚንቀሳቀሱበት ቆላ አካባቢ ደረሱ።

“እዚያ በረሃ [ቆላ] ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሁኔታውን ስለሚያውቁት ቢያዩህም ምንም አይመስላቸውም። እነርሱ ይዘውኝ ሲሄዱ እያዩ ዝም ብለው ነበር የሚያልፉት” ይላሉ።

የታጋቹ ማረፍያ የአርሶ አደር ጎጆ

አቶ ደቻሳ እንደሚሉት ታጣቂዎቹ ሌሊት ከቤታቸው አውጥተው ከወሰዷቸው በኋላ፣ ረዥም ጉዞ በማድረግ ማረፊያቸው ደረሱ።

እዚያ ከደረሱም በኋላ አንድ አርሶ አደር ቤት ውስጥ አስቀምጠዋቸው ጥበቃ መደቡባቸው።

“እንደደረስን አንድ የአርሶ አደር ቤት ውስጥ አስገቡኝ። ከዚያም አጠገቤ ቁጭ ብለው ይጠብቁኝ ነበር።”

እዚያ በደረሱበት በመጀመሪያው ቀን ምን አጥፍተው እንደታገቱ ሊያብራሩላቸው ይሞክሩ ጀመር።

“እዚያው እንደደርስኩኝ ምንድን ነው ጥፋቴ ስል ጠየቅኳቸው። ጥፋትህ ይሄ፣ ይሄ ነው እያሉ ዘርዝረው ነገሩኝ። እነርሱ ጥፋት ነው የሚሉት ነገር ምን ያህል እውነት ነው የሚለው ለራሴ ጥያቄ ነው። አይ ይህ ጥፋቴ አይደለም ብሎ በመከራከር የሚቀየር ነገር ስለሌለ ያለው አማራጭ መቀበል ብቻ ነው።”

“ከዚያ በኋላ ከጥፋቴ ጋር የሚመጣጠን ያሉትን፣ ይህን ያህል ገንዘብ ትከፍላለህ ብለው ውሳኔያቸውን ነገሩኝ” ይላሉ አቶ ደቻሳ።

“የያዙት ሰው ኖሮት የማያውቀውን ከፍተኛ ገንዘብ እንዲከፍል ይወስናሉ፤ በልመና እና በለቅሶ የተወሰነ ሊቀንሱ ይችላሉ። ከዚያ በኋላ ለቤተሰብ ለመደወል ስልክ ይሰጣሉ። ስለዚህ ለቤተሰብ የምትለቀቅበትን የገንዘብ መጠን እንዲፈልጉ ትነግራለህ” ይላሉ።

ቤተሰቦችህን በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ብር እንደሚያስፈልግህ ካስታወቁ በኋላ፣ ቤተሰብ ይህንን ብር በብድር ለማግኘት ላይ ታች ይላሉ።

“ይህ ገንዘብ ትልቅ ነው። እኔ ራሴ በእጄ ያለኝ አይደለም። ከተለያየ ቦታ እየጠየቀ እየሰበሰበ ያለው ቤተሰብ ነው። የዚያን ጊዜ ሲያስጨንቀኝ የነበረው ይህ ገንዘብ ካልተገኘ መገደሌ ነው የሚለው ነበር።”

አቶ ደቻሳ ከታጣቂዎች ጋር ያሳለፉት 10 ቀናት በጭንቀት እና በሃሳብ የተሞሉ እንደነበር ያስታውሳሉ።

“ትልቁ ሃሳብ ገንዘቡ ባይገኝስ. . .የሚለው ነው። ሌላው ጭንቀት ደግሞ እነርሱ እጅ ላይ እያለሁ ከመንግሥት ታጣቂዎች ጋር ተኩስ ቢከፈት መሞቴ ነው የሚለው ያስጨንቀኝ ነበር። እሞታለሁ አንጂ ከዚያ ወጥቼ እኖራለሁ የሚለው ለአንድም ሰከንድ በአእምሮዬ ውል ብሎ አያውቅም” ይላሉ።

ቀን በገፋ ቁጥር እና የተባለው ገንዘብ ሳይሞላ በዘገየ ቁጥር ማስፈራርያው እና የመሞት ጭንቀቱ እየገዘፈ መጣ።

“ደውል ይላሉ። የተወሰነብህን በጊዜው ካላደረስክ እንግዲህ ያንተው ችግር ነው በማለት ያስፈራራሉ። ጊዜ በጨመረ ቁጥር ቤተሰብም ጋር እየደወሉ ማስፈራራቱ እየባሰ መጣ።”

ያሳረፏቸው ቦታ የአርሶ አደር ቤት ስለሆነ አርሶ አደሮች እየመጡ ያነጋግሯቸው እንደነበር እና “አያስቡ ይወጣሉ” እያሉ ያጽኗኗቸዋል።

የተጠየቀውን ገንዘብ ማድረስ እና ፈተናው

ታጣቂዎቹ የጠየቁት ገንዘብ በጥሬ ብር እንዲሰጣቸው ነው የጠየቁት። አቶ ደቻሳ እንዲከፍሉ የተጠየቁት በመቶ ሺህዎች ስለሚቆጠር ተሸክሞ ለመሄድ ፈተና ሆነ።

እነዚህ ታጣቂዎች ባሉበት እና ሰዎችን በሚያግቱበት አካባቢዎች ገንዘብ አግኝቶ መክፈል ብቻ ሳይሆን፣ ከተለያዩ ሰዎች በብድር የተገኘን ገንዘብ ሰብስቦ አጋቾቹ ጋር በማድረስ የታገተውን ሰው ማስለቀቅ ሌላው ፈተና ነው።

አቶ ደቻሳ እንደሚሉት ታጣቂዎቹ ያሉበት ቦታ በጣም ሩቅ እና በእግር ረዥም ጉዞ የሚያስኬድ ነው።

መንገዱ የደኅንነት ስጋት ያለበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ብዙ ሰው የሚያውቀው አለመሆኑ ሌላው ችግር ነው።

“አንድ ሰው ታገተ በሚባልበት ጊዜ፣ የመንግሥት ሚሊሻዎች ደግሞ ገንዘብ የሚያደርሰውን ይጠብቃሉ። ለጠላት ሊሰጡት ያሉት ገንዘብ በሚል በቁጥጥር ስር ይውላል። የሚያደርሰውም ሰው ይታሰራል። በዚህ መካከል በታጣቂዎቹ እጅ ያለው ሰው ይገደላል።”

ስለዚህ የቤተሰቡ አባል የታገተበት ሰው፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠረውን ገንዘብ ለታጣቂዎች ከማድረሱ በፊት መንገዱ ተጠንቶ በከፍተኛ ምሥጢር ታጣቂዎች ጋር በማድረስ ነው ታጋቹን የሚያስለቅቁት።

አንዳንዴ ደግሞ የሚከፈልበት ቀን ካለፈ ታጣቂዎቹ ያገቱትን ሰው ይገድሉታል።

ይህም ሌሎች ሰዎች በመፍራት ሌላ ጊዜ የተጠየቁትን በጊዜ እንዲያደርሱ ለማድረግ በሚል እንደሆነ አቶ ደቻሳ ይናገራሉ።

በእርሳቸው ላይ ግን በአስር ቀናት ቆይታ ውስጥ ገንዘቡን በፍጥነት እንዲያደርሱ ከማስጨነቅ በስተቀር ምንም የደረሰባቸው እንግልት የለም።

እነዚህ ታጣቂዎች ራሳቸውን የኦሮሞ ጦር ሠራዊት ብለው እንደሚጠሩ የሚናገሩት አቶ ደቻሳ፣ “ይህ ከእናንተ የምንወስደው ገንዘብ ለትግል ይውላል” እንዳሏቸው ይገልጻሉ።

“አንዳንድ ጊዜ ልክ እንደ ጓደኛቸው ያዋሩኛል። አላማቸው ይህ ነው፣ ያ ነው እያሉ ነግረው ለሕዝብ ነጻነት እንደሚታገሉም ያወራሉ። የገንዘብ ጉዳይ ሲያነሱ ግን በጣም ነው የሚያስፈራሩት።”

አቶ ደቻሳ በአስር ቀናት ቆይታቸው የተለያዩ የአርሶ አደር ቤቶች ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉንም አክለው ተናግረዋል።

ከአጋቾቻቸው በቆዩባቸው አስር ቀናት ሁሉ በአካባቢው ምንም የተኩስ ልውውጥ ድምጽ ሰምተው እንደማያውቁም ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ከአጋቾቻቸው እጅ ከወጡ በኋላ

የአቶ ደቻሳ ቤተሰቦች የተጠየቁትን ገንዘብ የሚያበድራቸው ሰው ከአንድ ሳምንት በላይ ለሚሆን ጊዜ ፈልገው በማግኘት ለታጣቂዎቹ በመክፈል በአስረኛው ቀን ተለቀቁ።

“እነዚያው ያገቱኝ ሰዎች ናቸው ገንዘቡ ደርሶናል አሁን መሄድ ትችላለህ ያሉኝ። ማመን አልቻልኩም፤ በሕይወት ተርፌ እወጣለሁ የሚል ሃሳብ ፈጽሞ አልነበረኝም። ከዚያም መንገድ የማታወቅ ከሆነ ሰው እንሰጥሃለን ብለው አንድ ሰው መደቡልኝ” ይላሉ።

ቀኑን ሙሉ ሲሄዱ ውለው ማታ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተገናኙ።

“እኔ ብቻ ሳልሆን ቤተሰቦቼ ከእኔ በላይ ነበር የተጨንቀው። ገንዘቡን ማግኘት ብቻ ሳይሆን ገንዘቡን ታጣቂዎቹ ከተቀበሉ በኋላ ቢገሉትስ የሚል ትልቅ ጭንቀት ነበራቸው። ወደ ቤት የተመለስኩ ቀን ልክ ዳግም እንደተወለድኩ እና የመኖር ዕድል እንደተሰጠኝ ነበር የሆነው” ይላሉ።

አቶ ደቻሳ እገታው ከተፈጸመባቸው እና ለቀናት በሰቆቃ ውስጥ ከቆዩ ከወራት በኋላ አሁንም ከጭንቀት እንዳልወጡ ይናገራሉ።

“መጀመሪያ እንኳን ተረፍኩ የሚል ነበር ደስታዬ። አሁን ደግሞ የተበደርኩተን ገንዘብ ከየት አምጥቼ ነው የምከፍለው? በሚል ትልቅ ጭንቀት ውስጥ ነው ያለሁት። በተጨማሪም እዚያ ያሳለፍኳቸው ምሽቶች አሁን ድረስ በፊቴ እየመጡ ያስጨንቁኛል። በጣም ነው የሚረብሸው።”

በበሰሜን ሸዋ ወረዳዎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች፣ ራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብለው ቢጠሩም ቡድኑ ግን ታጣቂዎቻቸው በእንዲህ ዓይነቱ ማኅበረሰብን በሚጎዳ ተግባር ላይ እንደማይሳተፉ ይናገራሉ።

_______

*ለታጋቹ እና ለቤተሰባቸው ደኅንነት ሲባል ስማቸው የተቀየረ ሲሆን፣ ማንነታውን ለመለየት የሚያስችሉ ጠቋሚ ዝርዝር ሁኔታዎችን ከመግለጽ ተቆጥበናል። BBC Amharic


Exit mobile version