Site icon ETHIO12.COM

መንግስት ለማንኛውም ሰላማዊ ውይይት ዝግጁ መሆኑን ገለጸ፤ አገራዊ እርቅ ኮሚሽንን መርዳት እድልን መጠቀም ነው

መንግስት ለማንኛውም ሰላማዊ ውይይት ሁሌም ዝግጁ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

መንግስት ለማንኛውም ሰላማዊ ውይይት ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

የምክር ቤቱ ስብሰባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 28/2016 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር መሰረት በማድረግ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ፤ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶች ብዙ ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም በየጫካው ታጥቃችሁ የምትንቀሳቀሱ አካላት ሁሉ ወደ ሰላም አማራጭ መምጣት አለባችሁ በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

በሰፈር ከመነዳት በማቆም በምክንያት መጓዝ ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት ለማንኛውም ሰላማዊ ውይይት ሁሌም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ለሚነሱ ሁሉም ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አዳጋች ቢሆንም በመነጋገር በሂደት እየፈቱ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።

“የኛ መሻት ሁሉ ጊዜም ሰላም ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምንናገረው አብዝተን የምንተጋው ሰላምን ለማስፈን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

መንግስት የሚነሱ ግጭቶችን የመከላከል ስራ ብቻ መስራቱን ጠቅሰው እስካሁን ለማጥቃት አንድም ሙከራ አላደረገም ብለዋል፡፡

በመሆኑም ማንኛውንም ጥያቄ በሰላም ከመፍታት ባለፈ የሃይል አማራጭ ፋይዳ የሌለው ወደ ውጤትም የማይወስድ በመሆኑ የታጠቁ ሃይሎች የሚያደርጉትን የጥፋት እንቅስቃሴ በማቆም በሃሳብ መነጋገርን ብቻ አማራጭ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያዊያን በሰላም፣ በፍቅር፣ በትብብር በመኖር የጋራ ሀገር ለመገንባት መስራት አለብን ሲሉም አስገንዝበዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ባደረጉት ንግግር በሀይል ፍላጎትን ማስፈጸም ጊዜያዊ ድል እንጂ በዘላቂነት ሀገር እንደማያስቀጥል መግለፃቸው ይታወሳል።

የሰለጠነ ስርዓተ መንግስት በመነጋገር፣ በመመካከር፣ በመወያየት፣ በመከራከር እንዲሁም ሰጥቶ በመቀበል መርህ መገንባት እንደሚገባም እንዲሁ

አገራዊ የንግግር ኮሚሽን

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የሚበጅ ስራ እንዲያከናውን ሁላችንም ልንደግፈው ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን በተመለከተ ከምክር ቤቱ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለኢትዮጵያ የሚበጅ ስራ እንዲያከናውን ሁላችንም ልንደግፈው ይገባል ብለዋል።

እድሉን መጠቀም አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ እድል ከባከነ መሰል እድሎችን ለማግኘት በርካታ ዓመታትን ሊፈጅብን ይችላል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው በ1953 ዓ.ም ለውጥን የመጠቀም እድል አግኝተን አምልጦናል፤ በ1966 እንዲሁም በ1983 ዓ.ም ድጋሚ እድል አግኝተን አልተጠቀምንበትም ብለዋል፡፡

በመሆኑም አሁን አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሚሰጠንን እድል በተገቢው መልኩ መጠቀም አለብን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ትምህርትን በተመለከተ

የትምህርት ሥራ በተሟላ መልኩ ካልተስተካከለ በነጠላ ተግባር የሚሳካ አይደለም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

የትምህርት ሥራ በተሟላ መልኩ ካልተስተካከለ በነጠላ ተግባር የሚሳካ አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናገሩ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

የምክር ቤቱ ስብሰባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 28/2016 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር መሰረት በማድረግ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ በአገሪቱ የነበረው የትምህርት ሥርዓት ዘርፈ ብዙ ስብራት ስለነበረበት የትምህርት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት የለውጥ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ላለፉት ሰላሳ ዓመታት የጥራት ጉዳይ እየወረደ በመምጣቱና ብዙ ስብራት ስለታየበት ለውጥ ለማምጣት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

የትምህርት ሥርዓቱን ለማዳከም መስነፍና ጥቂት ጥረት ብቻውን በቂ ሲሆን ለማቃናት ግን ብዙ ድካምና ትጋት ይጠይቃል ብለዋል።

የትምህርት ፍኖተ ካርታ ሰባት ምሰሶዎችን በመያዝ ወደ ተግባር መግባቱን በመናገር ለዚህም መንግሥት ሰፋፊ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

በተለይም የፈተና ሥርዓቱን መቀየር፣ የምገባ ሥርዓትና የትምህርት ጥራትን ማሳደግ በፍኖተ ካርታው መካተታቸውን ጠቅሰዋል።

ይህን ተከትሎ ባለፉት አምስት ዓመታት አንድም ዩኒቨርሲቲ ሆነ ቅርንጫፍ ካምፓሶች አለመከፈታቸውን ነው የገለጹት።

በአንፃሩ በመላ አገሪቱ 18 ሺህ የሚጠጉ መዋዕለ ሕፃናትንና 1 ሺህ 400 የሙያና ቴክኒክ ኮሌጆች መከፈታቸውን ተናግረዋል።

የትምህርት ሥራ በተሟላ መልኩ ካልተስተካከለ በነጠላ ተግባር የሚሳካ አይደለም ብለዋል።

የፈተና ሥርዓቱ ቁጥጥር ስለበዛበት ውጤቱ ዝቅ ማለቱን በማንሳት ነገር ግን የማለፊያ ነጥቡን ከ50 በመቶ ዝቅ በማድረግና የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ተፈታኞች ዩኒቨርሲቲ እንዲቀላቀሉ መደረጉን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የፈተና ስርዓቱን ማሻሻል ለዘመናት የተሻገረውን የትምህርት ስብራት ለማስተካከል እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) 6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ከሕዝብ ተወካዮች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትምህርት ጉዳይን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያም ኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ስብራት ዘመናትን መሻገሩን አንስተው ይህን ለማስተካከል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የፈተና ስርዓቱን ማሻሻል አንዱ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ50 በላይ ያመጡ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲገቡ ቢደረግም ድጋሚ የማካካሻ ፈተና ወስደው የሚያልፉት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚቀላቀሉበት አሰራር ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።

በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ ያለውን ስብራት ማስተካከል ካልቻልን ልጆቻችን በህይወት ፈተና እንዲወድቁ እናደርጋቸዋለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትብብር የተሻለ የትምህርት ስርዓት እንዲኖር መስራት አለብን ብለዋል።


Exit mobile version