ETHIO12.COM

“አማራ የሆኑ በቁጥጥር ስር እየዋሉ ወደ አጎራባች ክልሎች እንዲጋዙ ተደረገ” በሚል የሃሰት ዜና ተሰራጨ

“የአማራ ተወላጆችን ሀገራዊ ሁኔታውን ለመቆጣጠር አስከሚቻል ድረስ በቁጥጥር ስር በማዋል ከከተማ ውጪ በአጎራባች ክልሎች በተዘጋጀ ቦታ እንዲቆዩ እየተደረገ ነው” በሚል በማህበራዊ ትስስር ገጾች በተጭበረበረ ደብዳቤ ታግዞ እየተሰራጫ ያለው መረጃ ፍጹም ሀሰት መሆኑን ተረጋገጠ። የተሰራጨው ደብዳቤ ፎርጅድ ነው።

ሀሰተኛ መረጃው “በተጨማሪም ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታን ይመለከታል” በሚል “የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአደባባይ ሃይማኖታዊ በዓላት እስኪከበሩ ድረስ ከአባላት እስከ ማስተባበሪያ ኃላፊ ያሉ የአማራ ተወላጆችን ሀገራዊ ሁኔታውን ለመቆጣጠር አስከሚቻል ድረስ በቁጥጥር ስር በማዋል ከከተማ ውጪ በአጎራባች ክልሎች በተዘጋጀ ቦታ እንዲቆዩ” የታዘዘ አስመስሎ ዘግቧል።

ይህን ያረጋገጠው ኢፕድ ደብዳቤዎች ፍጹም ስህተት መሆናቸውን ያረጋገጠው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ነው። ኮሚሽነሩ በማህበራዊ ትሰስር ገጾች እየተሰራጨ ያለው መረጃ ፍጹም ውሸት መሆኑን በመጥቀስ ህብረተሠቡ ከዚህ ዓይነት ውዥንብር ራሱን እንዲጠብቅ መክረዋል፡፡

መጪውን የጥምቀት በዓል ተከትሎ ከሃይማኖት አባቶች ጀምሮ እየተሰማ ያለው መግለጫና አካሄድ ህዝብን ሰላም እንደነሳ በተለያዩ አውዶች እየተገለጸ ሰንብቷል። መንፈሳዊ አውድ ላይ መስቀል ይዘው በአደባባይ ዕልቂት የሚያውጁ “አባቶች” መታየታቸው እጅግ እያነጋገረ ባለበት ወቅት ብሄር መርጦ ማጎሪያ ለማስቀመጥ መመሪያ እንደተሰጠ ተደርጎ የተሰራጨውን ደብዳቤ አስመልክቶ አዲስ አበባ ፖሊስ ያወጣውን መግለጫ ከስር ያንብቡ።

ወቅት እና አጋጣሚዎችን እየጠበቁ ሃሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ህዝቡን ለማሸበር እና የፖሊስ ሰራዊቱን ለመከፋፈል የሚደረጉ ሃላፊነት የጎደላቸውን እንቅስቃሴዎች እንደማይታገስ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ

ከተማችን አዲስ አበባን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ግጭት ጠማቂ ሃይሎች በተለያዩ ጊዜያት ያደረጓቸው ሙከራዎች በፀጥታ ሃይሉ እና በሰላም ወዳዱ የከተማችን ነዋሪ መክሸፋቸው ይታወቃል፡፡

በዚህ በኩል አልሳካ ያላቸው እነዚህ ፀረ ሰላም ሃይሎች እና የእነሱን አጀንዳ የሚያራግቡ አካላት ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የፖሊስን መልካም ገፅታ ጥላሸት ለመቀባት እና ሰራዊቱን ለመከፋፈል ሃሰተኛ መረጃዎችን በመለጠፍ የበሬ ወለደ ወሬ ሲያሰራጩ መቆየታቸውም ይታወሳል፡፡

አሁን ደግሞ ወቅትና አጋጣሚዎችን ተጠቅመው የሚፈልጉትን አጀንዳ ለማሳካት በለመዱበት መንገድ ሃሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ጀምረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ በአንድ ብሔር ተወላጆች የፖሊስ አመራርና አባላት ላይ ብቻ ያተኮረ እርምጃዎችን ሊወስድ እንዳሰበ የሚገልፅ ይዘት ያለው ሃሰተኛ ደብዳቤ ልዩ ልዩ ህገ-ወጥ ቴክኒኮችን በመጠቀም በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ ሲያዘዋወሩ ተስተውሏል፡፡

እውነታውን መላው የተቋማችን አመራርና አባላትም ሆኑ የከተማችን ነዋሪዎች የሚያውቁት በመሆኑ ለተሰራጨው ሃሰተኛ መረጃ ቦታ ባለመስጠት ሁከት እና ግጭት ለመፍጠር እንዲህ አይነቱን ህገ ወጥ ተግባር የሚፈፅሙ ግለሰቦችን እና ቡድኖችን በማጋለጥ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ተቀናጅተው መስራታቸውን ይቀጥላሉ፡፡

ሰላም ወዳዱ የከተማችን ነዋሪ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሰላምን ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚከናወኑ ተግባራትን በማገዝ ተባባሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ፖሊስ ጥሪውን እያሥተላለፈ የአዲስ አበባ ፖሊስ በአንድ ብሔር ተወላጅ በሆኑ የፖሊስ አመራርና አባላት ላይ ብቻ ያተኮረ እርምጃዎችን ሊወስድ እንዳሰበ ተደርጎ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ ሲያዘዋወር የተስተዋለው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በሌላ የፖሊስ ዜና=

አልሳካ ያላቸው እነዚህ ፀረ ሰላም ሃይሎች እና የእነሱን አጀንዳ የሚያራግቡ አካላት ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የፖሊስን መልካም ገፅታ ጥላሸት ለመቀባት እና ሰራዊቱን ለመከፋፈል ሃሰተኛ መረጃዎችን በመለጠፍ የበሬ ወለደ ወሬ ሲያሰራጩ መቆየታቸውም ይታወሳል፡፡
አሁን ደግሞ ወቅትና አጋጣሚዎችን ተጠቅመው የሚፈልጉትን አጀንዳ ለማሳካት በለመዱበት መንገድ ሃሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ጀምረዋል

የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ላለፉት ተከታታይ ሳምንታት ባካሄዱት ኦፕሬሽን እና በመደበኛ የፀጥታ ስራዎች ዙሪያ የነዋሪዎችን አስተያየት ለማሰባሰብ ከህዝብ ጋር ሲካሄድ የቆየው የውይይት መድረክ ተጠናቋል፡፡

ጥር 3 እና 4 ቀን 2016 ዓ/ም በቦሌ፣ በቂርቆስ፣ በኮልፌ ቀራንዮ እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች ውይይቶቹ መካሄዳቸው የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ጥር 5 ቀን 2016 ዓ/ም በቀሪዎቹ ሰባት ክፍለ ከተሞች ውይይት ተደርጓል፡፡ በአዲስ ከተማ፣ በየካ፣ በአራዳ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ፣ በለሚ ኩራ፣ በልደታ እና በጉለሌ ክፍለ ከተሞች በተካሄዱት ህዝባዊ መድረኮች የየክፍለ ከተሞቹ ፖሊስ መምሪያ ሃላፊዎች በተሰሩ ስራዎች ዙሪያ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

በየክፍለ ከተሞቹ በምስል ተደግፎ የቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ፖሊስ ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ያከናወናቸው ተግባራት በቅንጅት መስራት የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ አይነተኛ መፍትሄ መሆኑን እንደሚያመላክቱ ተናግረዋል፡፡

በተለይም ከባድ ወንጀሎችን ፈፅመው ተሰውረው የቆዩ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ በተደረገው ክትትል በቁጥጥር ስር መዋላቸው ማንም ሰው ወንጀል ፈፅሞ ከህግ ማምለጥ እንደማይችል ማሳያ መሆኑንም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል፡፡ ከህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ሞተር ብስክሌትን በመጠቀም ከሚፈፀም የቅሚያ ወንጀል፣ ከተሽከርካሪ እና ከተሽከርካሪ ዕቃዎች ስርቆት እንዲሁም ከሌሎች ልዩ ልዩ ወንጀሎች ጋር ተያይዞ ወንጀል ፈፃሚዎቹን ብቻ ሳይሆን በወንጀል የተገኙ ንብረቶችን የሚቀበሉ ሰዎችን ጭምር በህግ አግባብ ተጠያቂ ለማድረግ የተሰራው ስራ አመርቂ መሆኑን በማንሳት እነሱም በቀጣይ ከፖሊስ ጎን ሆነው እንደሚሰሩ በየመድረኮቹ የተሳተፉ የከተማችን ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ገልፀዋል፡፡

ለወንጀል መንስኤ በሆኑ እና በህብረተሰቡ ላይ አሉታዊ ጫና ከማሳደር ባሻገር ወጣቱን ትውልድ በሱስ በማደንዘዝ አምራች ዜጋን የማሳጣት ስራ በሚሰሩ ሺሻ ቤት እና ቁማር ቤቶች ላይ ፖሊስ የወሰደው እርምጃ ወደ ኋላ እንዳይመለስ፣ በአጠቃላይ ሰሞኑን የታዩ ውጤታማ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ፣የወንጀል እና ትራፊክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ሃላፊ ምክትል ኮሚሽነር መንገሻ ሞላ፣ የኮሚሽነር ፅ/ቤት እና ስታፍ ዳይሬክተር አህመዲን ጀማል እና የሰው ሃብት ስራ አመራር ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር ዮሃንስ ጭልጆ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በመገኘት የስራ መመሪያ የሰጡ ሲሆን በተገኘው ውጤት የፀጥታ ሃይሉን ጨምሮ ህብረተሰቡ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን በማቅረብ በተለያዩ ጊዜያት መሰል ውይይቶችን ከህዝብ ጋር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የውይይት መድረኮቹን የመሩት የፖሊስ መምሪያዎቹ ሃላፊዎች እንደተናገሩት ለተከታታይ ሳምንታት በተሰራው ኦፕሬሽን የተገኘው ውጤት የህብረተሰቡ እና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የታከለበት ነበር፡፡ ህዝብ እና ፖሊስ ተቀናጅቶ ከሰራ ከዚህ የበለጠ ውጤት በማምጣት የከተማችንን እና የነዋሪዎቿን ሰላም በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚቻል የጠቀሱት ሃላፊዎቹ፤ ህብረተሰቡ እስካሁን ሲያደርገው እንደቆየው ሁሉ ወደፊትም በምናከናውናቸው የፀጥታ ማስከበር ተግባራት ከጎናችን እንዳይለይ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለህብረተሰቡ ስጋት የሚሆኑ ወንጀሎችን በመከላከልና በመቆጣጠር እንዲሁም በአጥፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ እየሰራ ያለውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሃላፊዎቹ አረጋግጠዋል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ላለፉት ተከታታይ ሳምንታት ባከናወነው ኦፕሬሽን እና በቀጣይ ስራዎች ዙሪያ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር ያደረገው ውይይት በዛሬው ዕለት ተጠናቋል፡፡

Exit mobile version