Site icon ETHIO12.COM

የአፍሪካ ዋንጫ – ክንውኖች

አልጀሪያ ተሰናበተች ካሜሮን ወደ ቀጣዩ ዙር ገባች

የአፍሪካ ዋንጫ አሁንም ያልተጠበቁ ውጤቶችን እያስመዘገበ የትም አይደርሱም የተባሉት ቡድኖች የዋንጫ ግምት የተሰጣቸውን አገራት በጊዜ እየሸኙ ነው። ትልቅ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው አልጄሪያ ከውድድሩ በጊዜ መሰናበቷን ተረጋግጧል።

 ካሜሮን ደግሞ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከምድቧ ማለፏን አረጋግጣለች።

የማይበገሩት አንበሶች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ደካማ አቋም አሳይተው ነበር። ግብ ጠባቂውን አንድሬ ኦናናን ከቋሚ አሰላለፍ ውጭ አድርጋም ነበር ጨዋታውን የጀመሩት።

አጣብቂኝ ውስጥ የነበረችው ካሜሮን በቶኮ ኤካምቢ አማካይነት ቀድማ ጎል በማስቆጠር መምራት ችላ ነበር።

አብሊ ጃሎው ጋምቢያ አቻ ያደረገች ጎል ካስቆጠረ በኋላ ጨዋታው በአጫ ውጤት የሚጠናቀቅ መስሎ ነበር።

ኮሊ በ85ኛው ደቂቃ ተጨማሪ ጎል አስቆጥሮ ጋምቢያን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ።

ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ከጫፍ ደርሰው የነበሩት ጋምቢያዎች በጎሜዝ እና ዉህ በተቆጠሩባቸው ጎሎች 3 ለ 2 ለመሸነፍ ተገደዋል።

ጨዋታውን ኢትዮጵያዊው ዳኛ ባምላክ ተሰማ መርቶታል።

ከዚሁ ምድብ የተገናኙት ጊኒ እና ሴኔጋል ናቸው።

ጨዋታውን ሴኔጋል 2 ለምንም በማሸነፍ ምድቡን በቀዳሚነት ለማጠናቀቅ በቅታለች።

አብዱላዬ ሴክ እና ኢሊማን ንዲዬ ሁለቱን ጎሎች አስቆጥረዋል።

ሴኔጋል በዘጠኝ ነጥብ ካሜሮን እና ጊኒ ደግሞ በአራት ነጥብ በመያዝ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል።

የምስሉ መግለጫ,ካሜሮን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠረቻቸው ጎሎች ወደ ቀጣይ ዙር አልፋለች።

በምድብ አራት የተደለደለችው አልጄሪያ ደግሞ በጊዜ ከውድድሩ ውጭ ሆናለች።

ሞሪታንያ በተከላካዩ ያሊ ዴላሂ ጎል ከጨዋታው ሦስት ነጥቦችን ለማግኘት በቅታለች።

የ2019ኙ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዋ አልጄሪያ የመድቡ ግርጌ ላይ በመቀመጥ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ ከምድብ ድልድል ማለፍ ሳትችል ቀርታለች።

ብዙም ግምት ያልተሰጣት ሞሪታንያ በሦስት ነጥብ ወደ ጥሎ ማለፍ የማለፍ ዕድሏ በጣም ሰፊ ነው።

የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎቻቸውን በአቻ ውጤት ያጠናቀቁት አልጄሪያዎች ይህንንም ጨዋታ አቻ ቢለያዩ ወደ ጥሎ ማለፉን መቀላቀል ይችሉ ነበር።

መድቡን በበላይነት የሚመሩት አንጎላ እና ቡርኪናፋሶም ተገናኝተው ነበር።

ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ወደ ጥሎ ማለፉ ማለፋቸውን አረጋግጠው ነበር።

በጨዋታው ፓሴንሲያ እና ቻባካ ሳልቫዶር ባስቆጠሯቸው ጎሎች አንጎላ 2 ለ 0 ለማሸነፍ በቅታለች።

በዚህም ምድቡን በሰባት ነጥብ በመምራት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋለች።

ሞሮኮ ይግባኝ አለች

ሞሮኮ በአሰልጣኝ ዋሊድ ረግራጊ የሁለት ጨዋታዎች ቅጣት ውሳኔ ላይ ለካፍ የይግባኝ ደብዳቤ ማስገባቷን የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስታውቋል፡፡

አሰልጣኝ ዋሊድ ረግራጊ  አቻ በተጠናቀቀው የሞሮኮ እና ኮንጎ ጨዋታ በኮንጎ ብሄራዊ ቡድን አምበል ቻንሴል ምቤምባ ላይ በፈፀሙት ያልተገባ ባህሪ በካፍ የሁለት ጨዋታዎች እገዳ ተጥሎበት መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

ካፍ የቅጣቱን ምክንያት በግልፅ ባያሳውቅም አሰልጣኝ ዋሊድ ረግራጊ በቻንሴል ምቤምባ ላይ የዘረኝነት ጥቃት በመሰዘራቸው መሆኑን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡

የአሰልጣኙን የዲስፕሊን ግድፈት ካጣራ በኋላ ካፍ  የሁለት ጨዋታ ቅጣት ያስተላለፈበት ሲሆን÷ውሳኔውን ተከትሎም የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለካፍ ይግባኝ መጠየቁ ተገልጿል፡፡

የቅጣት ውሳኔውን ተከትሎም አሰልጠኙ ትላንት ምሽት ሞሮኮ ዛምቢያን 1 ለ 0 ባሸነፈችበት ጨዋታ ላይ ያልተገኙ ሲሆን÷በቀጣይ በጥሎ ማለፉ በሚደረገው ሌላ አንድ ጨዋታ ላይም የማይገኙ ይሆናል፡፡

ጋና አሰልጣኝ ክሪስ ሁተንን አሰናበተች

ጋና በአፍሪካ ዋንጫ ከምድብ አለማለፏን ተከትሎ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኙን ክሪስ ሂውተንን አሰናብታለች፡፡

ጋና በ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የሻምፒዮናነት ግምት ከተሰጣቸው አራት ቡድኖች አንዷ ብትሆንም ሳትጠበቅ የምድብ ተሰናባች ሀገር ሆናለች፡፡

የበርካታ ከዋከብቶች ስብስብ የሆነችው የጋና ከሞዛምቢክ እና ግብፅ ጋር አቻ በኬፕ ቬርዴ ደግሞ ተሸንፋ ከምድብ 2 ነጥቦችን ብቻ በመያዝ ከውድድሩ ውጭ ሆናለቸ፡፡

የጋናን ደካማ የአፍሪካ ዋንጫ ውጤት ተከትሎም የጋና የእግር ኳስ ማህበር አሰልጣኝ ክሪስ ሂውተንን ከሃላፊነት ያነሳ ሲሆን÷የቡድኑ የቴክኒክ ክፍል ሃላፊዎች መሰናበታቸውም ተገልጿል፡፡

የእግር ኳስ ማህበሩ የጥቁር ከዋክብቶችን የወደፊት እጣ ፋንታ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ እና የእቅድ ፍኖተ ካርታ ያቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ ስፖርት አስነብቧል፡፡

የቀድሞ የኒውካስትል እና የብራይተን አሰልጣኝ የነበሩት ክሪስ ሂውተን የቀድሞውን የጋና ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኦቶ አዶን በመተካት በፈረንጀቹ የካቲት 2022 ብሄራዊ ቡድኑን መቀበላቸው የሚታወስ ነው፡፡

ቢቢሲን ጨምሮ ከተለያዩ ሚዲያዎች የተሰባሰበ

Exit mobile version