Site icon ETHIO12.COM

” … ያለቀለት የተደመደመ ጉዳይ ነው” በኢትዮጵያ የሶማሊላንድ ተወካይ አምባሳደር አብዱላሂ ሞሀመድ

” የዓረብ ሊግ፣ ግብፅና ሶማሊያን በተመለከተ፣ በኔ እምነት በዚህ ረገድ ምንም ማድረግ የማይችሉ ይመስለኛል። ያለቀለት የተደመደመ ጉዳይ ነው። ከአካባቢው ጋር በተያያዘ ሰፊ ሌላ ዓላማ ላላቸው ግብፆች ምን አስጨነቀን ”

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ለማጠናቀቅ ” አሁን ከሁለቱም ወገኖች የቴክኒክ ኮሚቴ በመዋቀር ላይ ነው ” ሲሉ በኢትዮጵያ የሶማሊላንድ ተወካይ አምባሳደር አብዱላሂ ሞሀመድ ተናገሩ።

አምባሳደር አብዱላሂ ይህን ያሉት ለዶቼ ቨለ ሬድዮ ጣቢያ በሰጡት ቃል ነው።

የሶማሊላንዱ ተወካይ ፦ ” ጉዳዩን ለማጠናቀቅ አሁን ከሁለቱም ወገኖች የቴክኒክ ኮሚቴ በማዋቀር ላይ ነን። እና ይህ ቀድሞውኑ በሂደት ላይ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ።

(ፊርማውን ትከትሎ) ግንኙነቶች ነበሩ። በሁለቱ ሀገሮች መካከል ጉብኝቶች ነበሩ።

የውጭ ጉዳይ እና የአለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትራችን ባለፈው ሳምንት ነው የተመለሱት። እሳቸው እዚህ (አዲስ አበባ) ከእኔ ጋር ነበሩ። ዋና ተግባራቸውም ጉዳዩ መሠረት እንዲይዝ ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር ለመምከር ነበር።

ይዋል ይደር እንጂ ሁለቱ ኮሚቴዎች ወደ ስራ እንዲገቡ እናደርጋለን። ስለዚህ ይህ በጣም በቅርቡ ይከናወናል ብዬ አስባለሁ ” ብለዋል።

ሶማሊላንድ አለምአቀፍ እውቅና ያገኘ ባይሆንም ባለፉት 30 ዓመታት ፦

ከሶማሊያ እና ሌሎች ሀገሮች የተነሳውን ተቃውሞ እንዴት እንደሚመለከቱት የተጠየቁት አምባሳደሩ ፦ ” የዓረብ ሊግ፣ ግብፅና ሶማሊያን በተመለከተ፣ በኔ እምነት በዚህ ረገድ ምንም ማድረግ የማይችሉ ይመስለኛል። ያለቀለት የተደመደመ ጉዳይ ነው። ከአካባቢው ጋር በተያያዘ ሰፊ ሌላ ዓላማ ላላቸው ግብፆች ምን አስጨነቀን ” ብለዋል።

በመግባቢያ ስምምነቱ መሠረት ሶማሌላንድ በአፀፋው ምን ታገኝ እንደሆንም ተጠይቀው ፥ ” ለሶማሌላንድ ዕውቅና መስጠት። ይህ እርግጥ ነው። የዚህ ፕሮግራምም አካል ነው። የስምምነቱም ክፍል እና አካል ነው ” ብለዋል።

አምባሳደር አብዱላሂ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የቀጣናው አለመረጋጋት ምንጭ ናት ብለዋል።

ይልቁንም ሶማሊላንድ ለቀጣናው መረጋጋት ጉልህ ድርሻ ያላት መሆኑን ገልፀዋል።

” ኢትዮጵያም፣ ድንበሯም እንዲከበር እንጠብቃለን። ሁለተኛ ፣ ሶማሊላንድ በሕግ የፀና እውቅና ያለው ግዛት ሆኖ መታወቅ አለበት። ምክንያቱም እኛ የአካባቢው ጂኦ ፖለቲካዊ መረጋጋት አካል እና ባለድርሻ ነበርን። ባለፉት አመታት አልሸባብን እና ሽብርተኝነትን እየተዋጋን ነበር። ” ብለዋል።

የሶማሊላንድ የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር አብዱላሂ ሞሀመድ ፤ ” ሶማሊላንድ የሌሎች ሀገሮችም ድጋፍ አላት ” ሲሉ ተናግረዋል።

” ሶማሊላንድ በቀጣዩ የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ይህንን ጉዳይ በሚገባ ትይዘዋለች ” ያሉት አምባሳደሩ ፤ ” ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ወዳጆችም አሉን። ከ5 የተለያዩ ክልሎች፤ ለጉዳያችን በጣም በጣም አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው አባል ሀገራት (የአፍሪካ ሕብረት) አሉን። ” ብለዋል።

” እኛ ሕጋዊ ጉዳይ አለን ፣ የሞራል ጉዳይም አለን ፣ የሚቀረው የፖለቲካ ጉዳይ ብቻ ነው። ለአካባቢው እና ለአህጉሪቱ የምናደርገው በጎ አስተዋፅኦ ተዘንግቷል። የትኛውም አካል የህዝባችን ውሳኔ ላይ ሊወስን አይችልም። ህዝባችን ሕዝበ ውሳኔ አድርጎል። 97.5 በመቶው ነፃ ሀገር መሆንን በመደገፍ ድምጽ ሰጥቷል ” ሲሉ ሃሳባቸውን ደምድመዋል።

ይህ ቃለምልልስ የዶቼ ቨለ ሬድዮ ሲሆን ያዘጋጀው ቲክቫህ ኢትዮጵያ ነው

Exit mobile version