Site icon ETHIO12.COM

በወልቃይት ጠገዴ ሴቲት – በሁሉም ወረዳና ቀበሌዎች ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስልጠና እየተሰጠ ነው

በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ከሚለቀቁ ሃሰተኛ መረጃዎች እና የአካባቢን ሰላም ከሚያውኩ ጉዳዮች ራሱን በማራቅ ሰላምን አስጠብቆ ስለማቆየትም የፖለቲካና የምግባር ስልጠና እንደሚካተትበት ሃላፊዎች አስታውቀዋል።

መረጃው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የመንግሥት ኮምኒኬሽን መምሪያ ነው
በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በሁሉም ወረዳዎች የፖሊስና ሚሊሻ ስልጠና መሰጠት መጀመሩ ይፋ ሆኗል። በስልጠናው የፖሊስ፣ የሚሊሻ፣ የሰላም አስከባሪ አመራሮች እና አባላት እየተሳተፉ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን ዓላማው ሰላም ማስጠበቅ እንደሆነ ተመለክቷል።
ለጸጥታ አካላት እየተሰጠ የሚገኘው ሥልጠና ለሕዝብና ለሕገ መንግሥት ታማኝና ተገዥ የኾነ፣ ውስጣዊ አንድነትን የሚያረጋግጥ ጠንካራ የጸጥታ አካል ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ተገልጿል። ቀደም ባሉት ጊዚያት ኮሎኔል ደመቀ “ከመከላከያ ሰራዊት ብጋር በመናበብ አንድ ሆነን እየሰራን ነው። የሚወራው ሁሉ አሉባልታ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ሰላም ሲደፈርስ በወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ አንድም ዓይነት የሰላም ችግር አለመከሰቱ ይታወቃል። የአማራ ክልል የፖለቲካ ዋና ማተንጠኛ በሆነው ስፍራ የተገኘውን ሰላም ለማስተበቅ ህዝቡ ሁሉ ስልተና ባይወስድም ራሱን ወታደር ማድረጉ ቀደም ሲል በተለያዩ አውዶች ሲገለጽ ነበር።
ከሙያዊ ስልጠናው በተለየ ከለውጥ ማግስት ጀምሮ የተገኘውን ነጻነት እና ሰላም ለማስጠበቅ፤ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ከሚለቀቁ ሃሰተኛ መረጃዎች እና የአካባቢን ሰላም ከሚያውኩ ጉዳዮች ራሱን በማራቅ ሰላምን አስጠብቆ ስለማቆየትም የፖለቲካና የምግባር ስልጠና እንደሚካተትበት ሃላፊዎች አስታውቀዋል።
በስልጠና ማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የወልቃት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና ሰላምና ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ እንደ ክልል የሚሰጥ የፖሊስና ሚሊሻ ስልጠና መሆኑን ጠቅሰው ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
የዞኑ ኮሙኒከሽን ጽህፈት ቤት ስለሰልጣኞች ብዛት ይፋ ባያደርግም ከጦርነቱ ማግስት ጀምሮ አንዳችም የተኩስ ድምጽ የማይሰማባት ወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ ዞን አሁንም ሰላሟን ለማስጠበቅ ልዩ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ አመልክቷል።
ዓመት ሙሉ አምራች የኾነውን የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ሰላም ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መኾናቸውን ስልጠና ከማኢካሄድባቸው ወረዳዎች መካከል አንዷ በሆነችው የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር የጸጥታ አካላት ተገልጿል።
አሚኮ እንዳለው በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በአምስት ከተማ እና በአራት ወረዳ አሥተዳደሮች የጸጥታ አካላት ሥልጠና እየተሰጠ በስፋት እየተካሄደ ነው። በሥልጠናው የፖሊስ፣ የሚሊሻ፣ የሰላም አስከባሪ የተባሉ አመራሮች እንዲሁም አባላት እየተሳተፉ ተሳታፊ ሆነዋል።
በዳንሻ ከተማ አሥተዳደር የሥልጠና ማዕከል ያገኘናቸው ሠልጣኝ የጸጥታ አባላት የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ዓመቱን ሙሉ አምራች መኾኑን አንስተው የአርሶ አደሩ ምርታማነት እና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የአካባቢያቸውን ሰላም በቁርጠኝነት እያስጠበቁ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።
የዞኑ ሕዝብ ከራሱ አልፎ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የሚኾን ምርታማነትን እያረጋገጠ እንደሚገኝ ገልጸው በዞኑ እየተካሄደ የሚገኘው ዘርፈ ብዙ ልማት እንዲቀጥል እና ኅብረተሰቡ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ማልማት እንዲችል በቀጣይም የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ ቀን ከሌሊት እንደሚተጉ አረጋግጠዋል።
በሥልጠናው የተገኙት የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አብዱልውሃብ ማሞ የጸጥታ አካላቱ በአመለካከት በክህሎት እና በእውቀት በቂ ልምድን እንዲያገኙ የሚያስችል ሥልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለጸጥታ አካላት የፖለቲካዊ እና የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና መሰጠቱ የአካባቢን ሰላም ለማረጋገጥ ወሳኝነት አለው ያሉት ከንቲባው ዘርፈ ብዙ ብቃት ያለው የጸጥታ አካል ለመፍጠር ሥልጠናው ጉልህ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እና የዳንሻ ከተማ አሥተዳደር ማሠልጠኛ ማዕከል አሥተባባሪ ደጋለም ሲሳይ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ ለሦስት አስርት ዓመታት የሰላም እና የነጻነት አየር በማጣቱ የሰላም እጦት የሚያሰከትለውን ጉዳት ስለሚያውቅ የአካባቢውን ሰላም በቁርጠኝነት እየጠበቀ ነው ብለዋል።
ከለውጥ ማግስት ያገኘውን ነጻነት እና ሰላም ይጠብቃል፤ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ከሚለቀቁ ሃሰተኛ መረጃዎች እና የአካባቢን ሰላም ከሚያውኩ ጉዳዮች ራሱን በማራቅ ሰላሙን እያረጋገጠ መኾኑን ተናግረዋል።
ለጸጥታ አካላት እየተሰጠ የሚገኘው ሥልጠና ለሕዝብ ታማኝ እና ለሕገ መንግሥት ተገዥ የኾነ ውስጣዊ አንድነትን የሚያረጋግጥ ጠንካራ የጸጥታ አካል ለመፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል።
ሠልጣኝ የጸጥታ አካላት ሥልጠናውን በትኩረት በመከታተል የኅብረተሰቡን ሰላም እና ነጻነት አስጠብቆ ለመዝለቅ ቁርጠኛ ሊኾኑ እንደሚገባም ገልጸዋል።

Exit mobile version