Site icon ETHIO12.COM

ታማኞችና ቀናዎችን መሾም ይቀጥላል …!

ኢትዮጵያን በብቃት፣ በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል የሚችሉ ዜጎችን በካቢኔ ውስጥ የማካተት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ15ኛ መደበኛ ስብሰባው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቀረቡለትን የአስፈጻሚ አካላት ሹመት አጽድቋል።

በሹመቱም አቶ ተመስገን ጥሩነህ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም ዶክተር መቅደስ ዳባ የጤና ሚኒስትር ሆነው በመሾም ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ሚኒስትሮቹን ለመሾም ላለፉት ሶስት ወራት የብልጽግና ከፍተኛ አመራር መክሮበታል ብለዋል።

በሂደቱም በርካታ እጩዎች ከተለዩ በኋላ ሀገሩን በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ እስከሆነ ድረስ እንዲሾም መግባባት ላይ መደረሱን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ባልተለመደ መልኩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በሚኒስትርነትና የተለያዩ ሃላፊነቶች ተሹመው እያገለገሉ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይም ተመሳሳይ አድሎች የሚሰጡ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የብልጽግና ፓርቲ አባል ባይሆኑም ሀገራቸውን በቅንነትና በብቃት ለማገልገል የሚችሉትን በተለያዩ ሃላፊነቶች መሾማችን ይቀጥላል ብለዋል።

ከአለም አቀፍ ተቋማትና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጭምር በተለያዩ ሃላፊነቶች ኢትዮጵያን ለማገልገል ብቃት ያላቸውን ዜጎች የማሳተፉ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት በመገንባት ሂደት ሁሉም ተሳትፎ በማድረግ የድርሻውን መወጣት አንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስገንዘባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በተመሳሳይ የሹመት ዜና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለሁለት የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ሹመት ሰጥተዋል።

በዚሁ መሰረት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ትዕግስት ሃሚድን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አድርገው መሾማቸውን ከጽህፈት ቤታቸው የወጣው መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version