Site icon ETHIO12.COM

የሪህ በሽታ ምንድን ነው?

በዓላትን ተገን አድርገዉ ከሚከሰቱ በሽታዎች መካከል አንደኛዉ ሪህ ሲሆን በበዓላት ወቅት ከአመጋገባችን ጋር በተያያዘ የሚከሰት ነዉ፡፡ በሽታው ከበዓላት መምጣት ጋር ተያይዞ በብዛት ቢስተዋልም በአዘቦት ቀንም ሊከሰት ይችላል፡፡

የሪህ በሽታ በማንኛውም ሰው ላይ የሚከሰት የበሽታ ዓይነት መሆኑን እና የሚከሰተውም ዩሪክ አሲድ የተባለው ኬሚካል በአጥንት መገጣጠሚያዎች ውስጥ በሚከማችበት ወቅት እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ሪህ በጣም ከተለመዱት የአርትራይተስ በሽታ ዓይነቶች አንዱ ሲሆን ከፍተኛ ህመም ሊያስከትል ይችላል።

የሪህ በሽታ በመገጣጠሚያዎች አካባቢ፣ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ በአውራ ጣታችን ላይ ድንገት በሚከሰት ከፍተኛ የሕመም ስሜት፣ እብጠት እና ቅላት ባህሪው ይታወቃል።

በሽታው የሚያስከትለው ሕመም በድንገት የሚከሰት እና ብዙውን ጊዜ በሌሊት ከእንቅልፍ የሚቀሰቅስ ዓይነት ሲሆን በተለይ የአውራ ጣት በእሳት የተቃጠለ ያህል ሊሰማ ይችላል።

የሪህ ችግር አንድ ጊዜ ከጀመረ በኋላ የመከላከያ እርምጃዎችን ካልወሰድን የመመላለስ ባህሪም አለው።

የሪህ በሽታ መንሥኤዎች ፦

ሪህ የሚከሰተው ዩሪክ አሲድ የተባለው ኬሚካል በአጥንት መገጣጠሚያዎች ውስጥ በሚከማችበት ወቅት ነው። ዩሪክ አሲድ በመገጣጠሚያዎች ላይ ሲከማች እብጠትን እና ከፍተኛ ሕመምን ያስከትላል።

ዩሪክ አሲድ የሚፈጠረው ሰውነታችን ፒዩሪን የተባለ ንጥረ-ነገርን በሚሰባብርበት ጊዜ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ፒዩሪን በተፈጥሮ በሰውነታችን ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በተጨማሪም በበሬ ቀይ ሥጋ እና ጉበትን በመሳሰሉ ተዋፅኦች ላይ ይገኛል።

የሪህ በሽታ ምልክቶች

*የመገጣጠሚያ ላይ ህመም

*የመገጣጠሚያ አካባቢ መቆጣት (አካባቢው ላይ ሙቀት፣ መቅላት እና ማበጥ)

*በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የመገጣጠሚያ ህመም (ለመንቀሳቀስ መቸገር)

*በመገጣጠሚያ አካባቢ የማቃጠል ስሜት መኖር

*ቁርጥማት፣ ትኩሳት እና ብርደ ብርደ ማለት የሚጠቀሱ ምልክቶች ናቸው

ለበሽታው አጋላጭ ነገሮች:-

*ፆታ (ወንዶች ዮሪክ አሲድ በብዛት ስለሚያመርቱ በወንዶች ላይ የመከሰት እድሉ ይጨምራል)

*እድሜ (ሴቶች ላይ ካረጡ በኋላ የዮሪክ አሲድ ማምረት ይጨምራሉ)

*አልኮል መጠጦች (ዮሪክ አሲድ ከሰውነት በበቂ ሁኔታ እንዳይወገድ ያደርጋሉ

*የዩሪን መጠኑ ከፍተኛ የሆኑ የአመጋገብ ስርአት (ስጋ፣ እንቁላል፣ ዶሮ፣ አሳ…..)

*የሰውነት ክብደት

የሪህ በሽታ መከላከያ መንገዶች :-

*አመጋገብ ማስተካከል (የዩሪክ ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦችን አለመመገብ ወይም ለጊዜው መቀነስ)

*አልኮል መጠጦችን አለመጠጣት

*የስውነት ክብደት መቆጣጠር

*መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ

*በቀን ከሁለት እስከ ሶስት ሊትር ውሃ መጠጣት የሚመከር መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የሪህ በሽታ ሕክምና:-

የሪህ በሽታ ሕክምና ሁለት ዓይነት ሲሆን አንደኛው ሪህ የሚያስከትለውን የእብጠት እና የሕመም መጠን ማስታገስ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ በደም ውስጥ የሚገኘውን የዩሪክ አሲድ መጠን በመቀነስ በሪህ በሽታ ምክንያት የሚከሰተውን ጉዳት መቀነስ እንደሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጤና መረጃ የሚታወቀው የማዮ ክሊኒክ መረጃ ያመለክታል።

በሜሮን ንብረት EBC

Exit mobile version