Site icon ETHIO12.COM

በተቀናጀ መልኩ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ፕሮፖጋንዳዎች!

ኦክስፎርድ ኢንተርኔት ኢንስቲትዩት ሰሞኑን “2020 Global Inventory of Organized Social Media Manipulation” የሚል ሪፖርቱን ይፋ አድርጎ ነበር። ሪፖርቱ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያን ጨምሮ 81 ሀገራት ኢንተርኔትን፣ በተለይም ማህበራዊ ሚድያን፣ በመጠቀም የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ ስራ ሲያከናውኑ ነበር።

እንደሚታወቀው የማህበራዊ ሚዲያ ጥቅሙ እና አገልግሎቱ ሰፊ ቢሆንም ጉዳቱም በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል። በሀሰተኛ መረጃዎች፣ በተወሰኑ ሀይሎች በተደገፉ ክትትሎች (trolling)፣ እና በትንኮሳዎች የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች የሚያቃልሉ እና የተመረጡ የመንግስት ወይም የተቃዋሚ መሪዎችን ድርሻ ሲያወርዱ እና ሲያወጡ እየታዘብን ነው።

በአሁኑ ወቅትም በአለም ላይ ለዲሞክራሲ ሂደት ፈተና ከሆኑት ነገሮች ውስጥ አንዱ የሰዎች ሃሳብ ወይም አመለካከት ላይ ተመርኩዞ ማጭበርበር፣ ማሳሳት ወይም አንድን ሃሳብ ብቻ እንዲይዙ መገፋፋት ነው።

የኦክስፎርድ ሪፖርት እንደሚያሳየው በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በመንግስት ወይም በፖለቲካ ፓርቲዎች የተደገፉ የበይነ-መረብ ወታደሮች (cyber troops) በብዛት ይገኛሉ። ከአመት አመትም በስልቶቻቸው እያደጉ እና በህገወጥ መንገድ የሰዎችን መረጃዎች በመሰብሰብ ወይም ይህን የሚሰሩ ሰዎችን በማሰማራት ላይ ይገኛሉ።

እንደ ሪፖርቱ ዘገባ ከሆነ ባሳለፍነው አመት ይህ ድርጊት በስፋት ከተፈፀመባቸው 81 ሀገራት ውስጥ አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን አውስትራሊያ፣ ቻይና፣ ኤርትራ፣ ህንድ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ ዝርዝሩ ውስጥ ይገኙበታል። ፌስቡክ እና ትዊተር ከጃንዋሪ 2019 እስከ ኖቬምበር 2020 ድረስ ከ317,000 በላይ አካውንቶች እና ገጾችን ከሚዲያዎቻቸው ላይ እንዳስወገዱ በይፋ ካወጡት መረጃ መመልከት ይቻላል። ኢትዮጵያ ውስጥም በመንግስት አካላት፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በፖለቲከኞች፣ እና ተጽእኖ ፈጣሪ በሚባሉ ግለሰቦች ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጫና ሲፈጠር ይታያል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩት የበይነ- መረብ ወታደሮች (social media troops) እነዚህን መልዕክቶቻቸውን ለማስተላለፍ የሚጠቀሙባቸው አካውንቶች በሰዎች የተከፈቱ ወይም የተሰረቁ (hack የተደረጉ) አካውንቶችን ነው።

ይዘው የሚወጧቸው ሃሳቦች አብዛኞቹ የፖለቲካ ጥግ በመያዝ የሌሎችን ሃሳብ ለማፈን ወይም ለማጥቃት ሲውል ይስተዋላል፣ ሌላኛው በሰፊው የሚታየው ደግሞ የሰዎችን ሃሳብ በማጠልሸት ለማፈን መጠቀምን ነው። እነዚህ ‘ወታደሮች’ ገንዘብ የወጣባቸው መሆናቸውን ከዚህ ጥናት ላይ ማየት ተችሏል።

read the original story on 2020 Global Inventory of Organized Social Media

Exit mobile version