Site icon ETHIO12.COM

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕወሓትን ሕጋዊ ሰውነት መሰረዙን አስታወቀ – ቅንጅት “በተጭበረበረ ተግባር”እንዲሰረዝ ተወስኗል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ላይ ዛሬ ባስተላለፈው ውሳኔ የሕወሃትን ሕጋዊ ሰውነት መሰረዙን አስታውቋል፡፡የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕግ ከተቋቋመባቸው ዋና ዋና ተግባራት አንዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ፣ ቁጥጥር እና ክትትል ነው።

በመሆኑም በምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት ፓርቲዎች የተለያዩ መስፈርቶችን ማሟላታቸውን ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።በዚህም መሠረት ቀደም ብሎ መስፈርት አሟልተው ምዝገባቸው የተጠናቀቀ እና በሂደት ላይ ያሉ ፓርቲዎች ዝርዝርን ማሳወቁ ይታወሳል።ቦርዱ ከዚህ ቀደም ውሳኔ ያልሰጠባቸው እንዲሁም የተጠየቁትን ማብራሪያዎች ያቀረቡ ፓርቲዎችን አስመልክቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል።

1. ቦርዱ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የአመፃ ተግባር ላይ ተሰማርቷል ወይ የሚለውን ሁኔታ ለማጣራት በፓርቲው የተሰጡ መግለጫዎችንና በይፋ የሚታወቁ ጥሬ ሐቆችን በማቅረብ ፓርቲው ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመፃ ተግባር ላይ መሳተፉን አረጋግጧል።በተጨማሪም ፓርቲው መልስ የመስጠት እድል እንዲኖረው በማሰብ በፓርቲው እና በቦርዱ መካከል አገናኝ በመሆን ይሠሩ የነበሩትን የፓርቲውን የአዲስ አበባ ቢሮ የቀድሞ ተወካይ ለማነጋገር ጥረት ያደረገ ሲሆን፣ ተወካዩም ፓርቲውን መወከል እንደማይችሉ ገልጸዋል።በመሆኑም፦

ሀ. በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 98/1//4/ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት ሰርዞታል። በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 99 መሠረት የፓርቲው ሓላፊዎች በፓርቲው ስም መንቀሳቀስ እንደማይችሉም ውሳኔ አስተላልፏል።

ለ. የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በፓርቲው እና በፓርቲው አመራሮች ላይ በሚያደርገው ምርመራ የሚገኙ በሕወሓት ሥም የተመዘገቡ ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀስ ንብረቶችን በተመለከተ ያገኘውን ዝርዝር መረጃ እንዲልክ ቦርዱ ጥያቄ አቅርቧል።

ሐ. የፓርቲው ንብረት በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 99/2/ መሠረት ንብረቱ ተጣርቶ ዕዳ ካለበት ለዕዳው መሸፈኛ እንዲውል፣ ይሁንና እዳውን ሸፍኖ የሚተርፍ ንብረት ከተገኘ ቀሪው ገንዘብ እና ንብረት በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 99/3/ መሠረት ለሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት እንዲውል ቦርዱ ወስኗል።

2. ቦርዱ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሦስት ፓርቲዎችን ላይ በቦርዱ የትግራይ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በቀረቡ መረጃዎች እና ሌሎች ጥቆማዎች መሠረት ተጨማሪ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ስለእንቅስቃሴያቸው ማብራሪያ እንዲያቀርቡ ትእዛዝ ሰጥቷል። ትእዛዝ የተሰጣቸው ፓርቲዎችም የሚከተሉት ናቸው።

ሀ. “ዓሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /ዓዴፓ/”- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምዝገባ ሂደት ላይ እያሉ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ በተካሄደ ሕገ ወጥ ምርጫ ስለመሳተፋቸው፣

ለ. “ብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ /ባይቶና/” – በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምዝገባ ሂደት ላይ እያሉ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በተካሄደ ሕገ ወጥ ምርጫ ስለመሳተፋቸው እንዲሁም የፓርቲው አመራሮች በአመፃ ተግባር በመሳተፋቸው ለቦርዱ መረጃ በመድረሱ፣

ሐ. “ሣልሳይ ወያነ ትግራይ /ሣወት/”- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምዝገባ ሂደት ላይ እያሉ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ በተካሄደ ህገወጥ ምርጫ ስለመሳተፋቸው እንዲሁም የፓርቲው አመራሮች በአመፃ ተግባር በመሳተፋቸው በቦርዱ መረጃ በመድረሱ ፣

3. የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የመሥራች አባላት ጉዳይን አስመልክቶ ፓርቲው ያቀረበው የመሥራች አባላት ዝርዝር ላይ ቦርዱ 50 የሚሆን ናሙና በመውሰድ ያደረገው ማጣራት ስለትክክለኛነቱ ከፍተኛ ጥርጣሬ ውስጥ ያስገባው በመሆኑ፣ ቦርዱ ጉዳዩን ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ልኮት እንደነበር ይታወሳል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንም ባደረገው የማጣራት ሥራ ከሶማሌ ክልል 1145 መሥራች አባላት፣ ከአፋር ክልል 72 መሥራች አባላት፣ ከኦሮሚያ ክልል 23 መሥራች አባላት፣ ከአ.አ. ከተማ አስተዳደር 58 መሥራች አባላት በጠቅላላው የ1298 መሥራች አባላት በተጠቀሱት አድራሻ ያለመኖራቸውን ማረጋገጡን የሚያስረዳ መግለጫ በመስጠቱ የቦርዱም ሆነ የፖሊስ ኮሚሽኑ የማጣራት ሥራ የሚያሳየው ፓርቲው እያወቀ ወይም ማወቅ እየተገባው በቃለ መኃላ በተረጋገጠ ሰነድ ያቀረበው የመሥራች አባላት ስም ዝርዝር በተጭበረበረ ተግባር የፓርቲውን የዳግም ምዝገባውን ሂደት ማስፈጸም መፈለጉን እንደሆነ ተረድቷል።

ስለዚህ በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 98/1/ /ሠ/ መሠረት የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ እንዲሰረዝ ተወስኗል። ጉዳዩም በዐቃቤ ሕግ በኩል ክስ ተመሥርቶበት ይገኛል።4. የተለያዩ ነጥቦች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ወይም ሰነዶችን አሟልተው እንዲያቀርቡ ተገልጾላቸው የማጣራት ሂደታቸው ካልተጠናቀቁት ፓርቲዎች መካከል የሚከተሉት ላይ ቦርዱ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።ሀ. በቂ ማብራሪያ በማቅረብ መስፈርቱ ሟሟላት አጠናቅቀው ምዝገባቸው የጸደቀ ፓርቲዎች

• ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ – 43%

• ሐረሪ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት /ሐዲድ/ (የመሥራች ቁጥር የማይመለከታቸው አነስተኛ ቁጥር ያለው ብሔረሰብ ፓርቲ)

• የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) – 62%ለ. የማጣራት ሂደታቸው የተጠናቀቀ ነገር ግን የቴክኒክመስፈርቶች ይቀራቸው ከነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሂደታቸውን አሟልተው ያጠናቀቁ እና ተቀባይነት ያገኙ

• ሕዳሴ ፓርቲ /ሕዳሴ/ – 100%

• የካፋ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት /ካሕዴኅ/ – 71%

• የሲዳማ አንድነት ፓርቲ /ሲአፓ/ – 85%ሐ. ከቦርዱ በተሰጠው አስተያየት መሠረት በሰነዶች ላይ ማስተካከያ ባለማድረግ የተሰረዘ

• የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ጉሕዴን/መ. በፓርቲ አርማቸው ላይ ቅሬታ በመቅረቡ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትኖግራፊ የትምህርት ክፍል የባለሞያ ማብራሪያ የተጠየቀበት

• የራያራዩማ ፓርቲ5. ከዚህም በተጨማሪ አፈጻጸሙ በተጀመረው የ6ኛው አገራዊ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ መሳተፍ የሚችሉት ፓርቲዎች በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፉት 52 የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆናቸውን ቦርዱ ያሳውቃል። ለመሳተፍ ቅቡልነት ያላቸው እስከአሁን ያለውን ሂደት አጠናቅቀው የጨረሱ ፓርቲዎች መሆናቸውን አሳውቋል።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድጥር 10 ቀን 2013

Exit mobile version