የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስም ዘርዝሮ ዕውቅና የሰጣቸውን አካባቢና ዘር ተኮር ፓርቲዎች ዕውቅና መስጠቱን ተከትሎ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር፣ ትህነግም ዕውቅና እንደተሰጠው ተደርጎ እየተሰራጨ ያለው ዜና ሃሰት መሆኑን አስታወቀ።
ቦርዱ በኢትዮጵያ የምርጫ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ዓ.ም. የተሰጠውን ሥልጣን ጠቅሶ ‘የወሎ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ’ ተብሎ ለሚጠራ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ፤‘የኩሽ ህዝቦች ብሔራዊ ንቅናቄ’ ተብሎ ለሚጠራ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ እና ‘ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ’ ለተባለ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ጥር 21 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የፖለቲካ ፓርቲ የምዝገባና የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠቱን በይፋዊ ገጹ አስታውቋል።
ባይቶናና የወሎ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲንና ባይቶ አባይን “አገር አቀፍ” ፓርቲዎች ቢላቸውም ሁለቱም ፓርቲዎች የክልልና የብሄር መሰረት ላይ ተንተርሰው የተደራጁ መሆናቸውን አስቀድመው ሲያስታውቁ ነበር። የኩሽ ህዝቦች ብሔራዊ ንቅናቄም በተመሳሳይ ኩሽ ዘር ላይ የተንጠለጠለና አንዳንዴም ከተሰየመበት የዘር ግንድ ጋር የተገናኙ የሚላቸውን ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉትንም “አካሌ” ሲላቸው ይደመጣል። የዘር ድርጅትና ፓርቲዎች ኢትዮጵያን እየናጧት ባለበት ወቅት ቀድመው የተፍለፈሉት ሳያንሱ አዳዲስ መምጣታቸው በርካቶችን አስገርሟል።
የወሎ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር ክልልነትን የሚጠይቅና በስሙ የሰየመው የወሎ ግዛት ከአማራ ክልል ወጥቶ የራሱ አስተዳደር እንዲያቋቁም የሚጠይቅ እንደሆነ አስረግጦ ማስታወቁ አይዘነጋም። የፓርቲውን ዕውቅና ማግኘት ተከትሎ ከወዲሁ መነጋገሪያ የሆነውም ይኸው ጉዳይ ነው።
ይህ በንዲህ እንዳለ ” ለትህነግ የሰጠነው ምንም አዲስ እውቅና የለም ” ሲል የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ለቲክቫህ ማረጋገጫ ሰጥቷል። በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ ለትህነግ እውቅና ስለ መሰጠቱ የሚሰራጨውን አስመልክቶ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኮሚኒኬሽን ለቲክቫህ እንዳለው ለትህነግ የሰጠው ምንም ዓይነት ዕውቅና የለም።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ኮሚኒኬሽን ቢሮ በማህበራዊ ትስስር ገፆች በተለይም በፌስቡክ ለትህነግ እውቅና ስለመሰጠቱ ሀሰተኛ መረጃዎች እየተሰራጩ መሆኑን በተደረገ ቅኝት ማየት መቻሉንአመልክቷል።
ቦርዱ አክሎም ማንኛውም የብሄራዊ ምርጫ ቦርድን የተመለከተ መረጃ በቦርዱ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ እስካልወጣ ድረስ መረጃዎቹ ሀሰተኛ መሆናቸውንና ቦርዱን የማይወክሉ መሆኑ እንዲታወቅለት አሳስቧል።