Site icon ETHIO12.COM

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ተጠሪ ተቋማት በ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ግመገማዊ ውይይት አካሄዱ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ግመገማዊ ውይይት አካሂደዋል፡፡ በውይይቱም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክቡር ዶ/ር ጌዲዎን ጢሞቲዎስን ጨምሮ የየተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን የአፈጻጸም ሪፖርታቸውን ያቀረቡ ተጠሪ ተቋማትም የኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ፣ የፌደራል የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ፣ የፌደራል የፍትሕና የሕግ ምርምር እና ስልጠና ኢንስቲትዩት፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን፣ የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ የአእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት መሆናቸው ታውቋል፡፡

ተቋማቱ ውይይት ያደረጉት በ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያው 6 ወር ዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ሲሆን ምንም እንኳ የኮቪድ 19 ተግዳሮቶችንና ሌሎች ማነቆዎች ቢኖሩም በነበረው የተግባር ሂደት ጠንካራ አፈጻጸም የተመዘገበ መሆኑንና በዚህም የተሻለ ውጤት ማስመዝገበ መቻሉን ከቀረበው የአፈፃፀም ሪፖረት መረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖረቱ በዝርዝር እንደተብራራው ተጠሪ ተቋማቱ የተጣለባቸውን ተግባርና ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ያስችላቸው ዘንድ በዕቅድ ያስቀመጧቸውን ቁልፍና አበይት ተግባርት መሰረት በማድረግ በተለይ ጥራት ላለውና ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ቅንጂታዊ አሰራሮችን ማጎልበት፣ የመረጃ አያያዝን ማዘመንና ለተጠናከረ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሰፊ ተኩረት በመሰጠቱ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ተብሏል፡፡

ከተከናወኑ ተግባራት መካከል በተለይ የቅጂ፣ የፓተንትና ንግድ ምልክት ምዝገባና መብት ማስጠበቅ፣ ከታክስ ስወራ እና ማጭበርበር ጋር ተያይዞ በበርካታ መዛግብት ላይ የቃል ክርክር ማድረግና ወሳኔ ማሰጠት፣ የድሬዳዋና ዝዋይ ማረሚያ ቤቶችን ጨምሮ በ3 ማረሚያ ቤቶች የተለያዩ ዘመናዊ ህንፃዎች ማለትም፡የታራሚዎች መኖሪያ ህንፃ፣ ከፍተኛ ክሊኒክ፣ የቴክኒክና ሞያ ህንፃ፣ ወርክሾፕ፣ የልዩ ታራሚ መኖሪያ ቤት እና ሌሎች የግቢ ውስጥ መሰረተ ልማት ግንባታቸው ተጠናቆ ርክክብ መከናወኑ፣ ለ7,044 እስረኞች ለልዩ ልዩ ስነ-ልቦናዊ ችግሮች እና ማህበራዊ ቀውሶች እንዳይጋለጡ የተለያዩ የቅድመ-መከላከል ስራዎች መሰራታቸው፣ ከህግና ፍትህ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ሰነዶች መሰባሰባቸውና የሚገኙበትን ሁኔታ የመለየት ሥራ መከናወኑ፣ በርካታ ሠነዶችን የማረጋገጥና የመመዝገብ አገልግሎት መከናወኑ፣ በግማሽ አመቱ ከ354 በላይ አዲስ አገር በቀል እና የውጭ የሲቨል ማህብራት ድርጅቶችን መመዝገብ መቻሉ ተቋማቱ ካስመዘገቧቸው ጠንካራ አፈጻጸሞች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በመጨረሻም የተመዘገበው ውጤት ከነበረው የአሰራር ማነቆ አንፃር ሲታይ የተሻለ መሆኑ ቢገለጽም በዚህ መዘናጋት ሳያስፈልግ እንደተግዳሮት የተገለጹ ጉዳዮችን በፍጥነት በመፍታት ለላቀ ውጤት መስራት እንደሚገባ በመድረኩ ተሳታፊዎች የተገለጸ ሲሆን በቀጣይ ትኩረት መደረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

Exit mobile version