Site icon ETHIO12.COM

ክቡር ገና በመጪው ምርጫ ኢዜማን ወክለው በአዲስ አበባ ምክር ቤት ለመወዳደር በዕጩነት ቀረቡ

የኢዜማ መሪ እና ምክትላቸው ለተወካዮች ምክር ቤት ለመወዳደር ነገ በየምርጫ ወረዳዎቻቸው ይፎካከራሉ

በተስፋለም ወልደየስ

የቀድሞው የኢትዮጵያ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት ፕሬዘዳንት የነበሩት አቶ ክቡር ገና፤ በመጪው ምርጫ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲን ወክለው በአዲስ አበባ ምክር ቤት ለመወዳደር በዕጩነት ቀረቡ። በኢዜማ የመሪነት እና የምክትል መሪነት ስልጣን ያላቸው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አንዷለም አራጌ፤ ለተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመመረጥ ከሌሎች የፓርቲው እጩዎች ጋር በነገው ዕለት ይፎካከራሉ።

ኢዜማ፤ ፓርቲውን ወክለው ለተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ ለክልል ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ ዕጩዎችን የሚያስመርጠው፤ በየምርጫ ወረዳዎቹ ባሉ ጠቅላላ ጉባኤ አባላት በሚሰጥ ድምጽ ነው። ፓርቲው አሉኝ ከሚላቸው 435 የምርጫ ወረዳዎች ውስጥ በ329ቱ የዕጩዎች ምርጫ አካሄዶ ማጠናቀቁን አስታውቋል። በዛሬ እና በነገው ዕለት ደግሞ በ71 የምርጫ ወረዳዎች የዕጩዎች ምርጫ ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ ይዟል። 

በነገው ዕለት ከሚካሄዱ የፓርቲው የምርጫ ዕጩዎች ፉክክር ውስጥ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረጉቱና ዕውቅ ግለሰቦች የሚሳተፉባቸው ውድድሮች የሚጠበቁ ሆነዋል። ከዚህ ቀደም ከኢዜማ ጋር በተያያዘ ስማቸው ተነስቶ ከማያውቀው ከአቶ ክቡር ገና በተጨማሪ ቀድሞ በግብርና ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታነት አገልግለው የነበሩት ዶ/ር በላይ በጋሻው በነገው የዕጩዎች ምርጫ እንደሚሳተፉ ከፓርቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

አቶ ክቡር ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ለመወዳደር በዕጩነት የቀረቡት በሚኖሩበት ወረዳ 21 እና 22 ነው።  የፓርቲው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት አቶ ክቡር ኢዜማን በአባልነት የተቀላቀሉት ከሁለት ሳምንት በፊት ቢሆንም እርሳቸውን ለማግባባት ጥረቶች ሲደርጉ የቆዩት ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ ነው። 

ኢዜማ “ለምክር ቤቶች የሚደረጉ የዕጩዎች ውድድርን” አስመልክቶ ያወጣው ህግ፤ አባል ከሆኑ ስድስት ወር ያልሞላቸው አባላት የመመረጥም ሆነ የመምረጥ መብት እንደሚኖራቸው ይደነግጋል። እነዚህ አዲስ አባላት ይህን መብት ለማግኘት ግን ወደ ኋላ ተመልሰው የስድስት ወር የአባልነት መዋጮ መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ያትታል። ኢዜማ ይህን አካሄድ የተከተለው፤ ፓርቲው ከተመሰረተ አጭር ጊዜ አንጻር “ስድስት ወር ያልሞላው አባል መምረጥና መመረጥ እንዳይችል ማገድ የፓርቲውን የተሻሉ ዕጩዎች የማቅረብ አቅም የሚያጠብ በመሆኑ” እንደሆነ በህጉ ላይ አብራርቷል። 

የዚህ ህግ ተጠቃሚ የሆኑት ሌላኛው ዕጩ ዶ/ር በላይ በጋሻው ናቸው። መኖሪያቸውን ለበርካታ ዓመታት በአሜሪካ ያደረጉት እኚሁ ተወዳዳሪ፤ በምርጫው ላይ ለመሳተፍ በማሰብ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ፤ ኢዜማን በአባልነት የተቀላቀሉት የዛሬ ወር ገደማ መሆኑን የፓርቲው ምንጮች ተናግረዋል። ዶ/ር በላይ ኢዜማን ወክለው ለተወካዮች ምክር ቤት በተወዳዳሪነት ለመቅረብ የሚፎካከሩት በአዲስ አበባ ወረዳ 15 ነው። 

ኢዜማ እንደ አቶ ክቡር እና ዶ/ር በላይ አይነት “በስራቸውም፣ በልምዳቸውም” የሚታወቁ ግለሰቦችን በመጪው ምርጫ በተወዳዳሪነት ለማሳተፍ ለበርካቶች ጥያቄዎች አቅርቦ እንደነበር የሚናገሩት አንድ የፓርቲው ምንጭ፤ ሆኖም ብዙዎቹ የፓርቲውን ጥያቄ ሳይቀበሉ በመቅረታቸው ጥረቱ ሳይሳካ መቅረቱን አስረድተዋል። ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ፤ ፓርቲው በዚህ ምርጫ በህዝብ ዘንድ ከሚታወቁ ሰዎች ይልቅ፤ በሚኖሩባቸው አካባቢዎች አስፈላጊ ለሆኑ ሰዎች ይበልጥ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል። 

ባለፉት ሳምንታት በተካሄዱ የዕጩ ተወዳዳሪ ምርጫዎች ኢዜማን እንዲወክሉ ከተመረጡት ውስጥ አብዛኞቹ ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች መሆኑ የጠቀሱት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ይህም ፓርቲው “ለወጣቶች እና የመስራት ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የሰጠውን ቦታ ያመለክታል” ብለዋል። በዕጩ ተወዳዳሪነት ከተመረጡት ውስጥ አብዛኞቹ “ትምህርት ቀመስ” መሆናቸውንም አክለዋል። 

ኢዜማ እያካሄደው ባለው የዕጩዎች ምርጫ፤ በፓርቲው መዋቅር ውስጥ ቁልፍ ቦታ የያዙ ግለሰቦች በተወዳዳሪነት ሳይሳተፉ ቀርተዋል። ከተወዳዳሪነት ውጪ እንዲሆኑ ከተደረጉት ውስጥ የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ ምክትላቸው ዶ/ር ጫኔ ከበደ እንዲሆም የፓርቲው ዋና ጸሀፊ አቶ አበበ አካሉ ይገኙበታል።  

የፓርቲዎቹ አመራሮች በምርጫው የማይሳተፉት በፓርቲው ህገ ደንብ በተቀመጠባቸው ክልከላ ምክንያት እንደሆነ አቶ ናትናኤል ተናግረዋል። ከእነርሱ በተጨማሪ የፓርቲው የምርጫ ወረዳዎች በሊቀመንበርነት፣ በምክትል ሊቀመንበር እና በጸሀፊነት የሚያገለግሉ አመራሮችም በህገ ደንቡ መሰረት በተወዳዳሪነት እንደማይሳተፉ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አስረድተዋል። የኢዜማ ህገ ደንብ ከምርጫ ተሳትፎ የማያግዳቸው የፓርቲው መሪ እና ምክትላቸው ግን በነገው ዕለት በዕጩዎች ምርጫ ላይ እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።

የኢዜማ መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በመኖሪያቸው ወረዳ 23፤ ፓርቲውን ወክለው ለተወካዮች ምክር ቤት በዕጩነት ለመቅረብ ከሌሎች ሶስት የፓርቲው አባላት ጋር ነገ እሁድ ይወዳደራሉ። የእርሳቸው ምክትል የሆኑት አቶ አንዷለም አራጌም ተመሳሳይ ቁጥር ካላቸው ተፎካካሪዎች ጋር በወረዳ 12 እና 13 ለምርጫ ይቀርባሉ። 

እያንዳንዱ የፓርቲው የምርጫ ወረዳ፤ ለተወካዮች ምክር ቤት በዕጩ ተወዳዳሪነት የሚያሳልፈው አንድ ግለሰብ ቢሆንም በወረዳ 24 ግን በተቃውሞ ፖለቲካ ዝና ያላቸው ሁለት ግለሰቦች ለምርጫ እንደሚወዳደሩ ታውቋል። ተወዳዳሪዎቹ ዕውቁ ኢኮኖሚስት ዶ/ር በፍቃዱ ደግፌ እና በርካታ ዓመታትን በእስር ያሳለፈው ክንፈሚካኤል አበበ (አበበ ቀስቶ) ናቸው።

በአንድ ወቅት ብቸኛ የተቃዋሚ የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ ግርማ ሰይፉ፤ ኢዜማን ወክለው በድጋሚ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት ለመግባት በሚቀጥለው ሳምንት በሚኖሩበት ወረዳ 6 ከሌሎች ፓርቲ አባላቶች ጋር እንደሚፎካከሩ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሰረት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎች ምዝገባ ከየካቲት 8 እስከ 21 ባሉት ቀናት ይካሄዳል። ዕጩዎቹ የምረጡኝ ቅስቀሳ ወይም የምርጫ ዘመቻ እንዲያካሄዱ የተፈቀደላቸው ከየካቲት 8 እስከ ግንቦት 23 ባለው ጊዜ ነው።

(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Exit mobile version