Site icon ETHIO12.COM

“የትግራይ ልሂቃን የት ገቡ? ዳያስፖራው ለቆሰቆሰው፣ ወያኔ ላነደደው እሳት ማን እንደሚጠየቅ ለምን ፊትለፊት አይናገሩም ? “

አስመሮም ጣይቄ አለው። ጥያቄው በቀጥታ ለትግራይ ልሂቃኖች ነው። ” የትገቡ” ይላል። ” ዳያስፖራው ለቆሰቆሰው፣ ወያኔ ላነደደው እሳት ማን እንደሚጠየቅ ለምን አይናገሩም” አስከትሎም “የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃያ ሰባት ዓመት ተሰራ የሚለውን ጥፋት ሕዝቡ ላይ እንዳይለጥፍ ለምን አይሰሩም?” ሲል ቅሬታውን ይገልጻል።

ዙፋን ይሄይስ የአስመሮም ባልንጀራ ስትሆን ሁለቱም ነዋሪነታቸው አውሮፓ ነው። ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁን አደባባይ ወጥተው የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ አስተያየት አልሰጡም። ዛጎል ዛሬ ሲያናግራቸው ግን አላቅማሙም። ሁለቱም እጅግ አዝነዋል። ” አፍረናል” ይላሉ።

ዙፋን ” እንደው ይህን ሁሉ ጉድ ይዘው ነበር አደባባይ ሲጨፍሩና ሲያስጨፍሩ የኖሩት?” ስትል የሃዘኗን መነሻ ታስረዳለች። አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ስንዴ እየተሰፈረለት የሚኖር ሕዝብ በትግራይ ክልል ነበር። ይህን አስታውሳ ” ታላቅ ነበርን፣ ታላቅ እንሆናለን የሚለው ስብከት ለሰላሳ ዓመታት ስንዴ የሚሰፈርለት ህዝብ ተሸክሞ ” አለችና ተነፈሰች። 

ትህነግን የሚያመልኩ ሳይቀሩ ዛሬ ላይ በውስጣቸው እየተብላላ ያለው ጥያቄ ይህ ነው። የትግራይ ምሁራን፣ አንቂዎችና አዋቂዎች የት ነበሩ? ትግራይን ነጻ ካወጡበት ጊዜ ጀምሮ እንኳን መቁጠር ባይቻል ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ትህነግ ያለ አንዳች ተቀናቃኝ ትግራይን ሲመራ ነበረና ችግሩን ማንም ላይ ሊገፋው አይቻለውም።

አሜሪካ የሚኖረው ናትኔል አስመላሽ በተደጋጋሚ እንደሚለው ትህነግ የትግራይን ሕዝብ አንገት አስደፍቷል። አሳፍሯል። ምን አልባትም ረዘም ላለ ጊዜ ከዚህ ድብርት ውስጥ መውጣት አይቻል ይሆናል። ዙፋን ይህን ሃሳብ ትጋራለች። እንደ እሷ አባባል ዛሬ በዓለም ዙሪያ በማህበራዊ መድረኮች ሳይቀር የሚሰራጩ ምስሎችን ስትመከት ያማታል። ስታስበው አንዳች ክፉ ስሜት ይፈታተናታል። 

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በትግራይ 1.2 የሚሆኑ የሴፍቲ ኔት ወይም በየወሩ እህል የሚሰፈርላቸው፣ ከ600 ሽህ በላይ ለውጡን ተከትሎ የተፈናቀሉ ተረጂዎች ነበሩ። አሁን ላይ መነጋገሪያ የሆነው 1.2 ሚሊዮን ሕዝብ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ስንዴና ዘይት፣ አልሚ ምግብና መስለ የምግብ አይነቶች የሚረዳ ሕዝብ ይዞ፣ትህነግ ስለ አዲስ አገር መሆንና መገንጠል ሲያስተምር መኖሩ ነው።

አስመሮም እክርሮ ሲናገር የትግራይ ሕዝብ የተነፈገው የተፈጥሮ መብቱን ጭምር ነው። ሲያስረዳ ” የትግራይ ሕዝብ ጠላት ተፈጥሮለት፣ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በአገሪቱ እንዳሻው ተዛውሮ እንዳይሰራ ተደርጓል። ለዚህ ሁሉ የዳረገው ሕወሃት ነው። ሰው በተፈጥሮው አንድ ቦታ አይኖርም። በአብዛኛው እንደሚታየው የሰው ልጅ የተወለደበት መንደር አይሞትም። አንድ ስፍራ ካልተመቸው የተሻለ አማራጭ ፍለጋ ስፋር ይቀይራል። እኛ አውሮፓ የመጣነው በዚህ ሂሳብ ነው። የትግራይ ሕዝብ ግን አገሩ ውስጥ እስረኛ እንዲሆን አድርገውታል” ሲል ህወሃትን ይከሳል።

ዙፋን ታለቅሳለች። ባልደረባዋ ሲናገር ራስዋን መቆጣጠር አልቻለችም። በዛው ስሜት ሆና በለሆሳስ ድምጽ ” አይ የትግራይ እናቶች እምባ” ስትል የከሰሩትን ልጆቻቸውን በማንሳት ፍርዱን አምላክ እንዲሰጥ ዝም አለች። 

በትግራይ የምግብ ችግሩ ሰው እስከመግደል መድረሱ የተነገረው ከተፈናቀሉት በተጨማሪ የሴፍቲ ኔት ተጠቃሚዎቹ ለሁለት ወር ያህል እርዳታ ስለተቋረተባቸው ነው። አሁን በተደጋጋሚ እየወጣ ባለው መረጃ መንግስት እህል፣ መድሃኒትና አልሚ ምግብ እያደረሰና እያከፋፈለ ይገኛል።

ዜናው መልካም ቢሆንም ዙፋን የትግራይ ሕዝብ ንጹህ የሚጠጣ ውሃ እንደሌለው ጦርነቱ እንደተነሳ መነገሩ ጣቷን ወደ ልሂቃኑ እንድትቀስር አድርጓታል። ” ከጦርነቱ በፊት የትግራይ ልሂቃን የት ነበሩ” የመትለው ዙፋን ” ህዝብ ሰላሳ ዓመታት ስንዴ ሲሰፈርለት፣ ንጹህ ውሃ እንደሌለው እያዩ እንዴት ነው ዝም ብለው አብረው እስክስታ ሲወርዱ የኖሩት” ስትል ትጠይቃለች። 

አስመሮም ያለፉት ሰላሳ ዓመታት ነጹህ ውሃ ያልቀረበለት ሕዝብ፣ ስንዴ ሲሰፈርለት የነበረ ህዝብ ዛሬ መራቡ እንደማያስገርመው፣ ይልቁኑም የትግራይ ህዝብ ራሱን እንዲያይ ምክንያት ሊሆነው እንደሚገባ ያምናል። አክሎም ” የትግራይ ልሂቃን ብቻ ሳይሆኑ እሳቱን ሲቆሰቁሱ የነበሩ የዲያስፖራ አባላትም ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል” ሲል ጥሪውን ያስተላልፋል።

ኤፈርት የአፍሪካ ትልቁ ሃብታም የንግድ ተቋም ባለቤት ፣ የትግራይ ልማት ድርጅትን ያክል ሃብታም ማህበር የያዘ፣ የመላው ኢትዮጵያን ቢሮክራሲ ያለ ከልካይ ሲመራ የነበረ ድርጅት ለሶስት አስርት ዓመታት ትግራይ ውስጥ በጣሳ እህል እየተሰፈረለት የሚኖር ህዝብ ስለመኖሩ ማንንም ተጠያቂ ሊያደርግ እንደማይችል ይናገራል። 

የትህነግ አመራሮች ትግራይን እንዴት ሲያስተዳድሯት እንደነበር ለማስታወስ አስመሮም በውቅሮ አካባቢ በርካታ ታጋዮች በአንዴድ አልቀውባታል በምትባል ስፍራ ትምህርት ቤት ተከፍቶ በድርጅቱ መመስረቻ ቀን ሲመረቅ የተባለውን ይጠቅሳል።

አርከበ ዕቁባይ፣ ሃየሎም አርአያ፣ ስዬ አብርሃ፣ የወቅቱ የክልሉ ሊቀመንበር ገብሩ አስራት … ባሉበት የትምህርትቤቱ ምረቃ ላይ ” ድሮ ከተማ ድረስ እየተጓዛችሁ ልጆቻችሁን አማርኛ ታስተምሩ ነበር። ዛሬ በአካባቢያችሁ በትግርኛ መማር ቻላችሁ…” ሲሉ ከተጠቀሱት አንዱ ባለስልጣን ይናገራሉ።

አንድ አዛውንት ገበሬ ይነሱና ” ድል ማለት በትግርኛ መማር ከሆነ እናንተ ልጆቻችሁን ለምን አዲስ አበባ ልካችሁ ታስተምራላችሁ” ሌላም ሌላም ተናግረዋል / በማለት ጥያቄ አቀረቡ። አስመሮም የአዛውንቱ ጥያቄ ገና ወያኔ ስልታን በያዘ በአራተኛ ዓመት የቀረበ እንደነበር አንስቶ ” የትግራይ ልሂቃንና ዳያስፖራው ከኚህ አርሶ አደር ያነሰ እይታ አላቸው” ሲል በንፅፅር ይገልጻል። 

በዛት እንደሚሰማው የትህነግ መሪዎች ልጆች ሃብታም ናቸው። የተማሩትና እያተማሩ ያሉት በከፍተና ሃብት ነው። ትምህርት የጨረሱ ወይም ያልገፉት ከፍተኛ ሃብት ያንቀሳቅሳሉ። እገሌ እገሌ ባይባልም በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ሃብታሞች ተፈጥረዋል። የግል አውሮፕላን ያላቸው አሉ። ባህር ላይ ቤተመንግስት አሰርተው የሚንፈላሰሱና በውጭ ምንዛሬ የሰከሩ ጥቂት አይደሉም። ስማቸው እየተነሳ ሁሉ መረጃ የሚቀርብባቸው አሉ።

የትግራይ ሕዝብ አርፎ ስንዴ እየተሰፈረለት እንኳን እንዳይኖር ወደ መቀለ ሲሰባሰቡ መከራ ይዘውበት እንደሄዱ የሚገልጸው የመቀለዋ ዙፋን ባልንጀራ፣ የትግራይ ልሂቃን ዝምታ ከምንም በላይ ያበሳጨዋል። ከለውጡ በሁዋላ ላለፉት ሁለት ዓመት ተኩል በየሚዲያው ዲስኩር ሲያቀርቡ የነበሩ ምሁራኖች የት እንደገቡ ይጠይቅና ” ስህተትም ካለ በቀድሞው አቋማቸው ፊትለፊት በመውጣት መሟገት፣ አለያም ችግሩን አምነው ህዝብ ከደረሰበት ስብራት በአስቸኳይ እንዲያገግም ተሳታፊ መሆን ይገባቸዋል” ሲል ይጠይቃል።

ዙፋን በበኩለዋ የትግራይ ተወላጆች ረጋ ብለው ሊያስቡ እንደሚገባ፣ ረጋ ብሎ በማሰብ የውስጥ ችግርም ቀድሞ መየት እንደሚጠቅም፣ ስሜታዊነት አሁንም ህዝቡን እንደሚጎዳው፣ ወሃኔ ለመኖር ሲል ጠላት ፈጥሮለት እንዲታፈን የተገደደውን ህዝብ ነጻ ለማውጣት የሚጠቅመውን መንገድ መከተል ሊቀድም እንደሚገባ፣ ለኤላውም የህብረተሰብ ክፍል ይህን ምስኪን ህዝብ ተረድቶ ፍቅር እንዲሰጥ ታሳስባለች።

በሌላ ወገን ከፍተኛ ሃብት በማሰባሰብ እየተደረገ ያለውን የትጥቅ ትግል ማገዝ አስፈላጊ እንደሆነና ቅድሚያ የሚሰጠውም ለዚሁ ተግባር እንደሆነ የሚገልጹ የሚታወቁ የትግራይ ተውላጆች ጥቂት አይደሉም። አቶ ስዬ አብርሃ ሰሞኑን ” ትግሉ አላለቀም፤ ትህነግ አልተሸነፈም” በሚል መናገራቸና ረሃብ ለጸናባቸው የተሰበሰበ 2.5 ሚልዮን ዶላር ለአክቲቪስቶች ደሞዝ፣ ለትግሉ ማከናወኛ … ይሁን የሚል ክርክርም እየተሰማ ነው። አንዳንዶች የሚጠበቀው የሱዳንና የኢትዮጵያ ጦርነት መጀመር እንጂ ትግራይ ያለው የመከላከያ ሰራዊት እንደሚለቀም በድፍረት የሚናገሩ አሉ። 

መከላከያን አስመልክቶ ግን አብዛኞች የትግራይ ተውላጆች ክብር አንዳላቸው ሲገልጹ ነው የሚሰማው። መከላከያ ላይ በተፈጸመው ተግባር ማዘናቸውን በግልጽ ባይናገሩም ፈጽሞ የማይቀበሉትና ለትህነግ መጥፋት ዋናው መነሻ ምክንያት እንደሆነ የሚቀበሉ በርካቶች ናቸው። 

ዝግጅት ክፍሉ

እዚህ ሃሳብ ላይ መከራከሪያም ሆነ ተቃውሞ መጻፍ የምትፍለጉ በአግባቡ ተስተናገዳላቹህ 

Exit mobile version