Site icon ETHIO12.COM

ተመሥገን ጥሩነህ “ ሰው በጠፋበት ሰው ሆነው የተገኙ” መሪ

በአቶ ተመሥገን ጥሩነህ የሽኝት ዝግጅት ላይ የተገኙ የክልል ርዕሳነ መሥተዳድሮች መልዕክት አስተላልፈዋል። የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሰው በጠፋበት ሰው ሆነው የተገኙ፣ ብልህ፣ አስተዋይና አርቆ አሳቢ የሆኑ ናቸውም ብለዋል። አቶ ተመስገን አስቸጋሪ በሆነ ወቅት ከጎኔ ሆነው አመራር ሰጥተውኛልም ነው ያሉት። በፈተና ውስጥ ሆነው ከፈተና በኋላ ያለውን ድል የሚመለከቱ እንደሆኑም ተናግረዋል። የአማራ ክልልም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ተመሥገን ያለ መሪ በመኖሩ እድለኛ ነው ብለዋል።

ሀገራችን ብዙ ፈተናዎችን አልፋለች፣ አሁንም ሊኖር ይችላል የሚቀር ቀርቶ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች ነው ያሉት።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ የአማራ ክልልን ሕዝብ ምን አይነት ሰው አክባሪ እንደሆነ አውቃለሁ ብለዋል። የትግራይ እና የአማራ ክልል ሕዝቦች ከመዋሰን በላይ በደም የተሳሰረ፣ ይለይ ቢባል የማይለይ ሕዝብ ነውም ብለዋል።

በክፉ ጊዜ ኃላፊነት መውሰድ እድልም ነው ፈተናም ነው ያሉት ዶክተር ሙሉ በክፉ ጊዜ ኃላፊነት መወጣት መታደል ነው፤ ለሠራ ሰው እናመሰግናለን ማለት የታላቅነት መገለጫ ነውም ብለዋል። ሕዝብን በማስቀደም ከተዋያዬን መልካም ነገሮችን እንሠራለንም ሲሉ ተናግረዋል።

የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር ሆኖ ሳለ በጥቂት ቡድኖች ችግር ላይ ወድቋል፤ ይሄን ችግር ለመፍታት እስካሁን ያለውን ወንድማማችነት እና የሁላችንንም ርብርብ ያስፈልገናል ብለዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ እግር እንዳይተከል ጁንታው ሰርቷልም ነው ያሉት። ከዚህ በኋላ የትኛውም ችግር ቢኖር በውይይት እንፈተዋለንም፤ የወደፊት ተስፋችንን ማዬትና አብሮነትን ማጠናከር አለብንም ነው ያሉት።

የአማራ ሕዝብ ለሀገርና ለአብሮነት የማይደራደር ነው ያሉት ዶክተር ሙሉ ይሄን መልካም እሴት ማጎልበት ይገባልም ብለዋል።

አቶ ተመሥገን ሁሉም ነገር በሕግና ስርዓት ይፈታ የሚል አቋማቸው፣ ለአብሮነት ያላቸው ሥራ የሚደነቅ ነውም ብለዋል።

ከአማራ ክልል ጋር በጋራ እንሠራለን፤ ከአሁን በኋላ በትግራይና በአማራ ሕዝቦች መካከል ተግዳሮት የለም በማለት ገልጸዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ሙሰጠፌ መሐመድ የሶማሌ ክልል ከፍተኛ ችግር በነበረበት ጊዜ አቶ ተመሥገን ድጋፍ ያደረጉልን መሪ ናቸው ብለዋል።

አቶ ተመሥገን የአማራ ክልልን ብቻ ሳይሆን የሶማሌ ክልልንም አሻግረዋል ነው ያሉት።

የሶማሌ ክልል መዋቅር ፈርሶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሙስጠፌ ክልሉ መዋቅሩ እንዲስተካከል ከፍተኛ ሥራ መሥራታቸውንም ተናግረዋል።

አቶ ተመስገን የጥሩ ሰው ባህሪ የሚባሉትን የያዙ ናቸውም ብለዋል። ለእውነት የቆሙና ሀገራቸውን የሚወዱ መሪ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ከአንድ ፈተና ወደ ሌላ ፈተና የሄዱ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ሙስጠፌ ያሉበትን ተቋም እንደሚያሻግሩትም ዕምነት አለኝ ፤ የሥራ ቁርጠኝነታቸውንም ማስቀጠል ይገባቸዋል ብለዋል።

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ርስቱ ይርዳው ጁንታው የደገሰውን እልቂት ጉም ሆኖ እንዲቀር፣ የለኩሱት እሳት ራሳቸውን እንዲያቃጥልና ለእኛ ብርሃን እንዲወጣ ላደረጉ፣ የትግራይ ሕዝብ ከአፈና እንዲወጣ፣ የተደበቀውን ሕብረ ብሔራዊነት እንዲታይ ላደረጉ የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ የአማራ ሕዝብ ሳይነሳ አያልፍም ያሉት አቶ ርስቱ የአማራ ክልል ሕዝብ ኢትዮጵያን ያፀናና ያኮራ ሕዝብ ፣ የትኛውንም ሀገር እንደ ራሱ ሀገር የሚያይና የማይታጠር፣ ታታሪ ሰራተኛ፣ በፍቅርና በአብሮነት የሚኖር ሕዝብ ነው፤ ለረጅም ዘመናት የዘለቀው አብሮነታችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ መንግሥትና ሕዝቡ ከጎናችሁ ነውም ብለዋል።

ከአማራ ሕዝብ ጋር ሁለንተናዊ አጋርነታችንን እናጠናክራለንም ነው ያሉት።

የጋምቤላ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጅሉ ከነበረው ችግር አንፃር አቶ ተመስገን ክልሉን በሁለት እግሩ ያቆሙታል ወይ የሚል ጥያቄ ነበረኝ አሁን ግን ጥያቄዬ ተመልሶ ክልሉ ወደ ትክክለኛ አቋሙ መጥቷል ነው ያሉት።

የጋምቤላ ክልልና ሕዝብ ከአማራ ክልል ጋር በጋራ ይሠራልም ብለዋል።

አቶ ተመስገን በቁርጥ ቀን የተገኙ መሪ በመሆናቸው የጋምቤላ ሕዝብና መንግሥት ያመሰግናቸዋልም ብለዋል።

የአፋር ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ኡሌማ አቡበክር አቶ ተመስገን ከጀግና ሕዝብ የወጡ ስለሆኑ ጀግንነታቸው የዚያ ውጤት ነው ብለዋል። ለአፋር ክልልም ጀግናችን ናቸው፤ በሀገራችን የመጣው ለወጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጉልህ ሚና የተወጡ መሪ ናቸው በማለት ተናግረዋል።

የአፋርና የአማራ ክልል ሕዝቦች ጉርብትና እንዲጠናከር ሠርተዋልም ብለዋል። የአፋር ክልል በጎርፍ በተጎዳ ጊዜ የአማራ ሕዝብና መንግሥት ከጎናችን ቆመዋል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

Via (አብመድ)

Exit mobile version