Site icon ETHIO12.COM

በጉሮሮ ተማምኖ ጉሮሮውን ያጣው ጁንታው

“ጉሮሮ” በቆላ ተንቤን የሚገኝ በሚገርም መልከኣ-ምድራዊ አቀማመጥ የታጀበ የአካባቢ ስያሜ ነው፡፡

በሁሉም ግንባሮች የሽንፈቱን ፅዋ የተጎነጨው የህወሃት ጁንታ የመቀሌን ከተማ ለቆ በሀገረ-ሰላም በኩል አብይ አዲ …ጉያ እና ጎሮሮ እያለ የተንቤንን የምድር ገፅ የመጨረሻ እድል ፋንታው ለማድረግ ወሰነ፡፡

በሽንጠ ረጃጅም የጭነት ተሸከርካሪዎች ላይ ስንቅ እና ትጥቁን እስኪበቃው ድረስ ጭኖ ጉዞውን ወደ አዴት /ሰመማ/ አድጓል፡፡

የሎጀስቲካዊ ድጋፉን አስቀድሞ ፊቱን ወደ ኋላ በመመለስ ከወደ መቀሌ የሚመጣውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለመመከት ከፍተኛ መፍጨርጨር አደረገ፡፡

በከፍተኛ እልህ እና ሀገራዊ ወኔ የጁንታውን ኃይል ድባቅ እየመታ ወደፊት የሚገሰግሰውን ኃይል ለማቆም ያቃተው ራሱን የትግራይ መከላከያ ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን “እንቀብራቸዋለን!!” እያለ ወደ መቀበሪያው ይገሰግስ ነበር፡፡

መንገዶችን በከፍተኛ ጥልቀት ቢቆፍር አልያም ደግሞ መንገዶች ላይ የአፈር ቁልሎችን እያስቀመጠ ሰው ሰራሽ ተራራዎችን ሲሰራ የነበረው ይሔው ቡድን ምንም አይነት ስልት ከጭንቅ ሊያስጠልለው አቃተው፡፡

ሁሌም ቢሆን ሲሸሽ የሚያገኘውን ምድር ሁሉ ከወታደራዊ ጠቀሜታው አንፃር መረጥኩት ቢልም ብዙም ሳይቆይ ትቶት ከመፈርጠጥ አይድንም፡፡

በቆላ ተንቤን የጉሮሮ አካባቢም የመከላከያ ሰራዊቱ የመግደያ ወረዳ እንደሆነ በተለመደው አንደበቱ ያላዘነበት ቦታ ነበር፡፡

ግን ደግሞ የተመረጠ ቦታ ወይም በቂ መሳሪያ ወይም ደግሞ የሰው ሃይል ብዛት ብቻውን ድልን ስለማያመጣ ጉሮሮውን ተይዞ እዬዬም ሲደላ ነው እንዲሉ ለቁጥር የሚያታክቱ ስንቅና ትጥቅ የጫኑ ተሸከርካሪዎችን እና የመሳሪያ ዴፖውን ተሰናብቶ በእግሩ እግሬ አውጭኝ አለ፡፡

በጉሮሮ በኩል የ24ኛ ቴዎድሮስ ክፍለጦርን የፊት ለፊት የማጥቃት ክንድ መቋቋም ያቃታቸው የጁንታው ታጣቂ ኃይሎች ቁልቁል ሲዎርዱ የሲኦል ያህል የሚጨንቀውን የወርኢ ወንዝ ሸጣሸጥ ተሻግረው ቆረጣ የፈፀሙት የ12ኛ መተማ ክ/ጦር ጀግኖች የጁንታውን አከርካሪ ቀጭ አድርገው ሲሰግሩ ይታወቅ ነበር፡፡

እናማ ጉሮሮ ላይ ጉሮሮ ሊይዝ የተመኘው የጁንታው ኃይል ጉሮሮው ተያዘ፡፡ ሁሉንም ነገር ትቶ የተበታተነውም ጉሮሮ አካባቢ ከደረሰበት ውርጂብኝ ነበር፡፡

ክብር ለመከላከያ ሰራዊታችን!! FB

ሰለሞን ሁነኛው ( ከግዳጅ ቀጣና )
ፎቶግራፍ ሰለሞን ሁነኛው ጥር 22 ቀን 2013

Exit mobile version