Site icon ETHIO12.COM

ቡሬ ላይ የተተከለው አዲሱ የዘይት ፋብሪካ ስለምን ትችት ቀደመው? ባለቤቱ ” ቅናት ይቅርብን ብለው ነበር”

አዲሱ የዘይት ፋብሪካ መቶ ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስቀራል፤ እንዴት ቢባል የዘይት ኢምፖርትን በስልሳ በመቶ ስለሚያስቀር፤ በቀን 1.5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ያመርታል፤ 30 በመቶ ዋጋ ቅናሽ ያደርጋል፤ መቶ ቶን የአትክልት ቅቤ ያመርታል፣ ካርቶን ፋብሪካ አለው፣ ሰሊጥ ማጠቢያና ማቀናበሪያ አለው። በዚህ ማቀነባበሪያው የሰሊጥ ኤክስፖርትን ጥራት ጨምሮ የውጭ ምንዛሬ ያስገባል። የፕላስቲክ ማምረቻ አለው፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ አስገራሚው ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀመር ሶስት ሺህ ዜጎች የስራ እድል ማግኘታቸውና ፋብሪካው የሰፊ እርሻ ባለቤት ለመሆን ጉዞእ መጀመሩ ነው።

ከላይ የተቀመጠው መጠነኛ ማሳያ ነው። የተወሰደው ከፖለቲካ አመራሮቹ ሳይሆን ከባለሃብቱና ከዋና ስራ አስኪያጁ አንደበት ነው። ይህ ንብረትነቱ የአቶ በላይ ክንዴ የሆነው የዘይት ፋብሪካ እንደ ቀድሞው የሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ ፕሮጀክቶች ውስጡ ለቄስ ሳይሆን የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የሙከራ ምርት ሲያመርት ያሳየ ፋብሪካ ነው። የመኪና መገጣጠሚያው 160 የሚሆኑ ኢቬኮ ገጣጥሞ አዘጋጅቷል። የተዘረዘሩት ሰባት የሚጠጉ ምርቶችና ማምረቻዎች ሲሰሩ አይተው ምስክሮች ጽፈዋል። በቪዲዮ ታይቷል። ከሁሉም በላይ የዘይት ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ፖለትካና የዝርፊያው ትሥስር ለሚገባቸው ዜናው በብዙ መልኩ ይበል የሚያሰኝ ነው።

4.5 ቢሊዮን ብር የፈጀው ይህ ፋብሪካ ለግዜው የጥሬ ዕቃ ወይም የቅባት እህል ችግር ካልገጠመው በስተቀር ዓላማውን እንደሚያሳካ ባለሃብቱ ሲያስታውቁ እንዳሉት መንግስት ካለችው መጠነኛ የውጭ ምንዛሬ ላይ በመቀነስ ከውጭ አገር የሚገባውን የዘይት ምርት ቢያንስ ስድሳ ከመቶ ያስቀራል። በውስጡ ያሉት ፋብሪካዎች ተመጋጋቢ መሆናቸው ደግሞ ፋብሪካውን ዘመናዊ ያሰኘዋል።

ከመንግስት በቂ ክትትልና እገዛ የነበረው ይህ ፋብሪካ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የተወሰኑ ካቢኒያቸው በአካል ተገኝተው የመረቁትና መልዕክት ይስተላለፉበት ቢሆንም እንደ ቢቢሲ አይነቱ ቅጥረኛ የዜና አውታር ሲዘግበው እሬት እሬት እያለው እንደሆነ ያሳያል። ለወትሮ ምናምንቴ ዜና የሚመስጠው ቢቢሲ በዘገባው የጠቅላይ ሚኒስትሩንና መንግስታቸው የደረገውን ተሳትፎ እየነቀው ሳይጠቅስ፣ በላህብቱን ሳያነሳ ስራ አስኪያጁን ጠቁሞ የዘገበው ይህ ትልቅ ዜና እውነት ለሚሰማቸው ሁሉ አስገራሚ ነው ብዬ አምናለሁ።

ይህ ፋብሪካ ነው እንግዲህ ከወዲሁ እየተረገመ ያለው። በአገራችን እርግማን፣ ማንኳሰስ፣ ማጣጣልና አስቀድሞ ሟርት ማሰማት የተለመደ የአዋቂነት መለኪያ ተደርጎ በመወሰዱ ፋብሪካው ሲመረቅ ” እሰይ” ከሚለው ድምጽ ጋር መነሻውና ዓላማው ምን እንደሆነ በግልጽ የማይታወቅ ተቃውሞ እየተደመጠ ነው።

ዘይት ያረረበት ህዝብ ዘይት በሰላሳ በመቶ ቅናሽ እንደሚያገኝ በተሰማ ሰዓታት ውስጥ ለተቃውሞና ጥርጥር ውስጥ የሚጥል መረጃ ለማሰራጨት የሚሽቀዳደሙ ወገኖች፣ እንዲህ ባለ ፍጥነት ዜጎች ያደነቁትን ፋብሪካ ማጣጣጣልና ማናናቅ ለምን እንዳስፈለጋቸው ከነሱ በቀር የሚያውቅ የለም። ማሰቡ በራሱ ጉልበት ይበላል። ያማልም።

በምረቃ ስነ ስረዓት ላይ ” ለምን ኦሮሞዎች ተገኙ” ሲሉ የተቹም አሉ። ይህ ብቻ አይደለም ” እንዴት ጎንደር አንድ ኢንደስትሪ መንደር የላትም” በሚል አማራ ክልል በተሰራ ፕሮጀክት ላይ ሌላ የአማራ ክልል አይኑ ደም እንደለበሰ አድረገው ክፋትን የሚዘሩ ተሰምተዋል።

ላለፉት 27 ዓመታት የአማራ ክልል በልማትም ሆነ በማናቸውም በጎ ጉዳዮች የተገፋ፣ የተጎዳና የተዘነጋ መሆኑ ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለው የሚረዳው ሃቅ ነው። ጎንደርም የኢንደስትሪ መንደር ቀርቶባት ውስጧ ያለው ታሪካዊ ቅርስ እየነተበ ሲወድም እንኳን ሊታደስ ” እሰይ” የሚባልበት ዘመን ላይ ነበረች። ሰሜን ሸዋ በቁሙ የተቆለፈበት ህዝብ ነበር።

ዛሬ ያ ቀድሞ የነበረው አድልዎ ተነስቶ በቡሬ የታየው ታላቅ ጅማሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም እንዲስፋፋ መመኘትና ግፊት ማድርግ አገሩን ከሚወድ ሁሉ ይጠበቃል። እንደ አቶ በላይ ሌሎች ዜጎችም ለሕዝብ በሚጠቅም ኢንቨስትመንት ላይ መረባብረብ እንዲችሉ የሚያነሳሳ ሰላማዊ ቅናትን መስበክ አሁንም የሚዲያዎችና ተሰሚነት ያላቸው ክፍሎች ተግባር ሊሆን ይገባል። ከዚህ ውጭ ግን አንድ ነገር በተሰራና በተመረቀ ቁጥር በርግማን ማልቀስ እንደ ዜጋም ሆነ እንደ ሰው ክብር አያሰጥም።

ፋብሪካው የሚታውቅ መሰረታዊ የቴክኒክም ሆነ ሌላ ችግር ካለበት በጨዋነት እንደ ባለሙያ ጥቆማ መስጠት፣ ስጋትን ማስቀመጥ፣ ከተቻለ በማስረጃ አስደግፎ ማስጠንቀቅና ማሳሰብ ያሸልማል። ይህ በየተኛውም ዘርፍ ሊተገበር ይገባል። አስፈለጊም ነው። በተቃራኒ መስቀል አደባባይን የማስዋብ ስራ ሲሰራ ” የኦርቶዶክስን ንብረት አወደሙ” የሚል ድንቁርና አገርን የቁም ሞት የሚያከናንብ አስተያየት ስንሰማ እንደነበረው ” 1.5 ሊትር እንዴት ሊያመርት ይችላል? ቁጩ ነው” እያሉ መሳለቅ ግብዝነት ይሆናል።

ዛሬ ዛሬ በአገራችን የተለመደው በድፍረት የማያውቁትን ጉዳይ አንስቶ መዘላበድና ዘላባጆች የደፉትን አፍሶ መብላት ወይም መጋት ነው። አብዝኛው ሕዝብ ባይሆንም ጥቂቶች የተደፋውን ለራሳቸው ከመጠቀም አልፈው እንደ እውነት እያጋሩ ሌላው ላይ በመርጨት የተባበራሉ። ለምሳሌ ታላላቅ ሞሎች፣ አንፊ ቲያትሮችና የህዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎችን ከስራቸው ለመኪና ማቆሚያ መጠቀም ዓለማችን ላይ የተለመደ አሰራር ነው። ዘመናዊነት ነው። ተሽከርካሪዎች ከመሬት ስር ሲቆሙ ከላይ ያለው ህዝብ ሰፊ ቦታ ያገኛል። አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ይህ ሲሆን ነው ተቃውሞው የተሰማው። ዲዛይኑ ላይ ወይም አካሄዱ ላይ ችግር ካለ በማስረጃና በመረጃ መጠቆም የሚበረታታ ቢሆንም ሌላው መብት እንደሌለው ተደርጎ እንዲሁ በጅምላ በሃይማኖት ስምና በወፍ በረር ወቀሳ ሲረጭ ነበር። ሁሉም አልፎ ዛሬ ፕሮጀክቱ የሚያጓጓ እንደሆነ አላፊ አግዳሚው እያወራ ነው።

የቡሬ ዘይት ማምረቻ ይፋ መሆኑንን ተከትሎ እግር በግር የሚሰሙትና ይህንን ፕሮጀክት ዳር ያደረሱ ባለስልጣኖችን ስራ ለማጣጣል ሲባል ብቻ የሚሰነዘረው ውግዘት እንደ አገር መክሸፋችንን፣ በአስተሳሰብ መዛጋችንን፣ በልቡናችን መጥቆራችንን፣ በግብር ክፋታችንን የሚያሳይ ሆኖ ይታየኛል። ይህ የተጠናወተን ክፉ አስተሳሰብ ባህላችንም የሆነ ይመስላል። ስድብና ማውገዝ፣ መጠራጠርና ማጣጣል እንደ ኮሶ እናታችን ውስጥ ተጣብቶናል። በዚህ እሳቤ የት ልንደርስ ይሆን?

በቅርቡ መንግስት የ”ህግ ማስከበር” ባለው ዘመቻ የትህነግን ነብሰ በላ ቡድን በሳምንት ውስጥ ተረት ሲያደርግ፣ ሟርት ሲያሰሙ፣ ትህነግ እንደሚያሸንፍ ሲሰብኩና ለትህነግ ወግነው በመናበብ የሚሰሩ የነበሩ ድሉን ባይክዱም የጠሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ከድሉ ፈልቅቀው ለማውጣት ምን ያህል ሲላላጡ እንደነበር እዚህ ላይ ማስታወስ ግድ ያላል። አንዳንዶቹ አፋቸውን ሞልተውም ” እኛም አለንበት” ሲሉ ዋሺንግቶን ካለው ለዚሁ ተግባር ከተከራኡት ከግራውንድ ቤታቸው ሆነው ነገረውናል።

ማንም ባላሰበውና ባልገመተው ፍጥነት፣ ማንም ሊያስበው በማይሽል ስልት አብጦ የነበረው ትህነግ ሲፈራርስ፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት መኮንኖች በይፋ ጦርነቱ ከማዕከል እንዴት ይመራና መመሪያ ይወርድ እንደነበር ሲመሰክሩ የተሰማበትን ጉዳይ በአደባባይ ሲያሟርቱ የነበሩ አሁንም ባደባባይ በተሳደቡት መጠን ” ይቅርታ” መጠየቅ ሲገባቸው አላደረጉትም። ይልቁኑም ውግናቸውን ለሞተው ሃይል ለመስጠት በታረደው የመከላከያ ሰራዊት ደም ላይ ሲረማመዱ ይታያል። በነብስ የደረሰችልንን ኤርትራን እየታከኩ አገራቸውን ሲገዘግዙ እየዋሉ ያድራሉ። እግረ መንገዳቸውን መልካም ነገር ሲከናወን መሪውን የማጥላላቱ ዘመቻ እንዳይደናቀፍ ወዲያውኑ ለመልካሙ ነገር እርግማን ያመርታሉ። ይህ እርም የሆነ ክህደት ተለምዷል። በቃ ሊባል ግን ይገባል።

ዛሬም አዲስ የተከፈተው የዘይት ፋብሪካ ” ለምን ቡሬ ሆነ? ኦሮሞዎች ምርቃቱ ላይ ለምን ተገኙ” በሚል የሚረጨው የቅናትና መርዝ ያዘለ ፕሮፓጋንዳ ልክ እንደ ህግ ማስከበሩ ዘመቻ አፍ የሚያሲዝ ውጤት ሲያስመዘግብ ምን ይባል ይሆን?

ጎሹ ሰለሞን

ዝግጅት ክፍሉ – አስተያየቱ የጸሃፊው ሃሳብ ብቻ ነው

Exit mobile version