አቶ ወርቁ አይተነው የገንዘብ ቀውስ እየገጠማቸው መሆኑ ተሰማ

በደብረ ማርቆስ ከተማ “WA (ደብሊዉ ኤ)” የምግብ ዘይት ማምረቻና ማቀነባበሪያ ፋብሪ ያስገነቡትና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስማቸው በስፋት የሚነሳው ባለሃብት የገንዘብ ቀውስ እየገጠማቸው መሆኑ ተሰማ። አቶ ወርቁ ከተለያዩ ባንኮች በቢሊዮን የሚቆጠር እዳ ያለባቸው ከፍተኛ ተበዳሪ መሆናቸውም የባንክ ታሪካቸው ያስረዳል።

አቶ ወርቁ በምን ምክንያት የገንዘብ ቀውስ እንደገጠማቸው ለጊዜው ሳያብራሩ መረጃውን ለአዲስ አበባ ተባባሪያችን የገለጹ እንዳሉት፣ ባለሃብቱ ምክንያቱ በግልጽ ባልታወቀ መልኩ ብር ሲረጩ ማየት የተለመደ ነው። በመንግስት በኩል በጥብቅ ቀለበት ውስጥ ከገቡ ክፍሎች ጋር ያዘወትሩ እንደነበር የሚነገርላቸው አቶ ወርቁ ለነዚሁ ክፍሎችና ለሌሎች የሚዘሩት ብር ደግሞ በእዳ ከወሰዱት ላይ መሆኑ አሁን ለገቡበት ቀውስ ዳርጓቸዋል።

አቶ ወርቁ የዕዳ ክፍያቸውን አስመልክቶ በባንኮች በኩል ምን እንደተነገራቸው ባያውቁም፣ የክልሉ መንግስት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክር እንደለገሳቸው አመልክተዋል። እሳቸውም ምክሩን መቀበላቸው ተሰምቷል።

ወርቁ አይተነው በህግ ማስከበሩ ዘመቻ ወቅት ግንባር በመመላለስ ሞራል በመስተትና በቁስ ድጋፍ አቅራቢነት ያበረከቱት አስተዋጾ የመንግስትን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛዎች በስፋትና በልዩ ሁኔታ ሲዘገብላቸው እንደነበር ይታወሳል።

“የራሳችንን ሃይል እናሰለጥናለን” ከሚሉት ወገኖች ጋር በአንድ ወቅት ሲታዩ የነበሩት አቶ ወርቁ “አገር ወዳድ” የሚሏቸው በርካቶች ቢሆኑም፤ አካሄዳቸው እንዳላማራቸው የሚገልጹም ነበሩ።

አሁን ላይ አቶ ወርቁ እንደቀድሞ በሚዲያ አታዩም። አይሰሙም። የዜናው ሰዎች እንዳሉት ጥሞና ላይ ሆነው በሙሉ ሃያላቸው ዘይት ፋብሪካውን ለማስሮጥ ሳያስቡ እንዳልቀሩ ነው።

በቀን አንድ ሚሊየን 350 ሺህ ሊትር ዘይት የማምረት አቅም እንዳለው የተነገረለት ፋብሪካው ለአንድ ሺህ 500 ሰራተኞች የስራ እድል ፈጥሮ ስራ መጀመሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተገኙበት ይፋ መሆኑ ይታወሳል። ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ በሶስት ፈረቃ ማምረት ሲጀምር ለ6 ሺህ ሰራተኞች የስራ ዕድል እንደሚያስገኝ በውቅቱ ተመልክቶ ነበር።

ከአጠቃላይ ምርቱ 40 በመቶው የሰሊጥ ዘይት እንደሚሆን፣ የሃገር ውስጥ ፍላጎትን መሰረት በማድረግም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሀገር ውስጥ የዘይት ፍጆታን 60 በመቶ ለመሸፈን፣ የምርት መቆራረጥ እንዳይፈጠርም ፋብሪካው ምርቱን ወደ ገበያው በቅርቡ በተደራጀ መልኩ እንደሚያስገባ ተጠቅሶ በምረቃው ወቅት የተነገለት የዘይት ፋብሪካ፣ በዓመት እስከ 18 ቢሊየን ብር የስራ ማስኬጃ ወጪ አለው ተብሎ እንደነበር ይታወሳል። ፋብሪካው 5 ቢሊዮን ብር ወጪ የወጣበት ነው።

አቶ ወርቁን በቅርብ የሚያውቋቸው ፈጣን አሳቢና በቀላሉ ነገሮችን የማስላት ተፈጥሮ ያላቸው እንደሆኑ ይመስክሩላቸዋል። አቶ ወርቁ ኢትዮጵያን የማሳደግ ህልም እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይታወቃሉ።

አቶ ወርቁ የእጅ ስላካቸው ላይ በተደጋጋሚ ቢደውለላቸውም መልስ ስላልሰጡ ተባባሪያችን አሳባቸውን ማካተት አልቻለም። አለሁ ባሉ ጊዜ ለማመጣጠን እንደሚስተናገዱ ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን።

Leave a Reply