Site icon ETHIO12.COM

አብን “ስውሩ ትህነግ!” ወይስ “የአማራው ልብ?”

“አብን ከአመሰራረቱ ጀምሮ የሚታውቀ፣ እንቅስቃሴው በሙሉ በመረጃ የተደገፈ፣ መረጃውም ማስረጃውም እጅ ላይ ያለ የሞተው ትህነግ የእጅ ስራ መሆኑንን ይፋ ማድረጊያው ወቅት ቀርቧል” በሚል የሚናገሩ የአማራ ብልጽግና ሰዎች ” ለጊዜው ማወቅ የሚገባቸው አውቀዋል” ሲሉ አብን የምርጫ ስጋት እንዳልሆነ ይናገራሉ። ከአብን ወገን የሆኑት ደግሞ ” አብን የአማራ ልብ ነው” ሲሉ ቢያንስ የአማራ ክልልን ለመግዛት እርግጠኛ ሆነው እየሰሩ መሆናቸውን በኩራት ያስተጋባሉ። ሁሉንም ወገን የሚያውቁ ደግሞ ነባር ኢህአዴጎችና ኢህአዴግ ያስለጠናቸው ጨዋታውን እየመሩት እንደሆነ ይነገራሉ። ጨውታው አብን “ስውሩ ትህነግ” በሚሉና አብን ” የአማራው ልብ” በሚሉት መካከል ይመስላል።

የኢትዮ 12 ሪፖርተር ይህን የዘገበው ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ረብሻ ይነሳል ወይስ አይነሳም በሚለው ጉዳይ በቅርቡ አዲስ አበባ ሄደው ከነበሩ የዓለም አቀፍ የሚዲያ ሰዎችን በጠየቀበት ወቅት ካገኘው መረጃ በመነሳት ሲሆን፣ የምርጫው የጸጥታ ጉዳይ ላይ ያለው ስጋትና ቅድመ ትንተና ለጊዜው በማቆየት የአብንና የአማራ ብልጽግናን አጀንዳ ቅድሚያ ሰጥቷል። ይሁን እንጂ የአማራ ክልል ሰፊ ዘማቻና የቀደሙ ጠባሳዎቹን ለማሻር ትኩረቱን ሰጥቶ በህብረት በሚሰራበት ወቅት ፓርቲውን ለመሸርሸር እየሰሩ መኖራቸውን፣ ዋልታ ረገጥ ሆነው የሚንቀሳቀሱትን ማየታቸው እንዳሳሰባቸው በርካቶች ይገልጻሉ።

ከሁለቱም ወገን እንዳልሆኑ የሚናገሩ እንደሚሉት የአማራ ክልል ብርቅ ልጆቹን በሴራ ካጣ በሁዋላ በአቶ ተመስገን አመራር ተረጋግቶ ባለበት ወቅት፣ ያለበትን የወሰንና የማንነት ጥያቄ ምላሽ ሰጥቶ በሚሰራበት በዚህ ጊዜ በገሃድ አንድነት መፍጥርን እንጂ በጓሮ የሚደረግ ትንቅንቅ በወጉ ያረጋውን ጉዳይ የመበጥበጥ ያህል ነው። ከዛም በላይ ወቅትን ባለማገናዘብ የሚከናወን ተግባር ሆኖ ሊቀለበስ የማይችል ስህተት ሊያስከትል እንደሚችል ይናገራሉ። እነዚህ ወገኖች አብንና አማራ ብልጽግና ሆነው በድብቅ የሚሰሩ ሊጠነቀቁ እንደሚገባ ይመክራሉ።

ሰሞኑንን ኢትዮጵያ ከነበሩና ፈቃድ ከተከለከሉ ኢትዮጵያ ላይ የዘመቱ የውጭ አገር ሚዲያዎች ጋር አዲስ አበባ ተገናኝተው ሲያወጉ የነበሩት የአብን ዋና መሪና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ በቀጣዩ ምርጫ ቢያንስ አማራ ክልል ላይ እንደሚያሸንፉ እርግጠኛ ሆነው እንደገለጹላቸው ኢትዮ12 ሰምታለች። ሚዲያዎቹ ፈቃድ ስላላገኙ የማይታተም ወይም ስም ተጠቅሶ የማይወጣ በሆነው መረጃ እንደተናገሩት አብን በገዢው የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ውስጥ እጁ ስር ሰዶ ስለገባ አማራ ክልልን እንደሚያሸንፍ በርግጠኛነት መስክረውላቸዋል።

አብን በገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን በባልደራስና በአዜማ ፓርቲዎች ውስጥ በሚገባ እጁን እንዳስገባና አስፈላጊ በሚሆንበት ወቅት ከየአቅጣጫው የሚያገኘውን ድምጽ አዳምሮ ምኞቱን አማራ ክልልን ከመረከብ በላይም ሊያደርገው እንደሚችል ጠቅሷል። ሁሉንም መረጃ ያካፈሉን እንዳሉት በኢትዮጵያ በተቀናቃኝ ፓርቲነት ከተመዘገቡት ውስጥ አብዝቶ ኤንባሲዎችን የሚገናኝና ድርጅት ቢኖር አብን ነው። አብን ለበርካታ ኤንባሲዎች ቀጣዩ የአማራ ክልል መሪ እንደሚሆን በፍጹም እምነት እየተናገረ ነው።

ሪፖርተራችን ያናገራቸው የአማራ ክልል ብልጽግና አመራር ” አብን ወዳጅ የሆኑ እገራት ኤምባሲዎች ዘንድ ሁሉ ሄዶ የሚሰጠውን ማብራሪያ እናውቃለን” ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሚጀመሩት። ሲቀጥሉ ደግሞ አብን ድርጅታቸው ብልጽግና ውስጥ እጁን ማስገባት ብቻ ሳይሆን አስተዳደር ክልሉን እንዲወስድ ተደርጎ ወደ ምርጫ ቢገባ የት አካባቢ ድምጽ እንደሚያገኝ ስለሚታወቅ የአማራ ብልጽግና አመራር ሆኖ እንዲህ ያለ ቁማር ውስጥ የሚገባ አለ ብለው እንደማያምኑ ያስረዳሉ። ያም ሆኖ ግን ስውር ነገር እንደሌለ ሲናገሩ በፍጹም እምነት ነው።

አብን ” የአማራ ልብ ነኝ” በሚል የሚያቀርበውን የዕርዳታ ፕሮፖዛል እንደሚያውቁ የጠቀሱት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፣ እሳቸው እስከሚያዉቁት ድረስ አብን በረከት ስምዖን ከቋቋመው ቀን ጀመሮ እስካሁን ድረስ ማንነቱን የሚያሳይ መረጃና ማስረጃ አለ። በህዝብ ደረጃም ቢሆን ማወቅ የሚገባቸው እንዲያውቁት በመደረጉ ቀጣዩን ስራ እንደሚያቀለው አስታውቀዋል።

ወቅቱ ባለመሆኑ ስም ጠቅሶ መናገር እንደማይቻል የገለጹት የአማራ ብልጽግና አመራር ” አብን ያልሞተው ትህነግ እንደሆነ ህዝብ ጸሃይ እየሞቀ ያየዋል” ሲሉ ገልጸዋል። እሳቸው እንደዚህ አቃለው ቢያወሩም አብን ጠንካራ አቋም ላይ እንደሚገኝ የሚያምኑ አሉ። በወሎ፣ጎጃምና አገው ጥቂት አካባቢዎች ውስን ቦታ አብን ድምጽ እንደሚያገኝ የሚገምቱት እነዚህ ወገኖች የውስጥ ለውስጥ ስርሰራውን አጥብቀው ይኮንናሉ።

ስጋርታቸው የሚያስቀምጡ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ የአማራ ህዝብ ከመቼውም በላይ ጠንካራ ፓርቲና አደረጃጀት በሚያሻው በአሁኑ ወቅት የውስጥ ለውስጥ ግዝገዛው ክልሉን መሪ አልባ እንዳያደርገው ነው የሚፈሩት። እነ ዶክተር አምባቸውን የመሰሉ መሪዎችን የከሰረው የአማራ ክልል ከሃዘኑ አገግሞ አሁን ተረጋግቶ ወደ ልማት በገባበት ወቅት ላይ እንደገና የማተራመስና ይህንን በቁጭት የተነሳ ድርጅት አፍርስው ከአጋር ድርጅቶቹ እንዳይለዩት ፍርሃቻ ያላቸው አካላት ህዝብ በተለይም ልሂቃኑ ጥንቃቄን እንዲሰብኩ ይጠይቃሉ።

አብን ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ ኤምባሲዎችን በቀጣዩ ምርጫ እንደሚያሸንፍ መግለጽ ብቻ ሳይሆን ድጋፍም እየጠየቀ ነው። የመረጃው ምንጭ እንዳሉት ከሆነ አብን በአማራ ክልል መቶ ከመቶ ስልጣን እንደሚይዝ በማስረዳት ላይ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ድምጽ አጣለሁ ብሎ በሚሰጋባቸው አካባቢዎች ሁሉ የአዜማንና ድምጽ ለመውሰድ በድርጅቱ ውስጥ በበቂ ሁኔታ እጁን ማስገባቱ ሲነገር ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

አብን በኦፊሳል ከባልደራስና መኢአድ ጋር ለመቀላቀል ንግግር ላይ መሆናቸው ቢነገርም ከዘገየ የተጀመረ በመሆኑ ህጉ ይህንን እንደማይፈቅድ የሚያውቁ እየገለጹ ነው። ያም ሆኖ ከምርጫ በሁዋላ ድምጽን ይዘው ጥምረት የመፍጠር አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ይታመናል።

ራሱን ከትህነግ ማዕቀፍ ውስጥ ያወጣውና አቶ ደመቀ የሚመሩት የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ዛሬ ላይ አቋሙ የፈረጠመ በመሆኑ፣ በአገራዊው ብልጽግና ፓርቲ ውስጥም መሰረቱ የጎላ በመሆኑ ፓርቲውን ውስጥ ውስጡ የመሸርሸር ስራ አደጋ ሊያስከትል የሚሰጉ መኖራቸውን በመጥቀስ ሪፖርተራችን ያናገራቸው የድርጅቱ አንድ አመራር ” ስጋት የለብንም። ሁሉንም በትዕግስት ማየት ነው። አገርን የሚመራ ፓርቲ መሆኑ መዘንጋት አግባብ አይሆንም” በማለት ጥቅልል ምልሻ ከሰጡ በሁዋላ ” መናበቡ በሚዲያዎችና ስልጣን በተከለከሉ አክቲቪስቶች እንዲሁም ነባር ኢህአዴጎች ተሰባስበው የሚያልሙት ነው። ሁሉም ይታወቃል” በሚል ዘግተውታል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትህነግ ከተመታ በሁዋላ አዳዲስ አሰላልፈፎች ብቅ እያሉ ነው። ከተመታው ትህነግ ጋር ድርድር እንዲደረግ የሚጠይቁ፣ ጥንት ኢህአዴግ ” ሌላ” ብሎ ያባረራቸው፣ ትህነግ ” ቆሻሻ ልክስክስ” ብሎ ወህኒ የወረወራቸውና እነዚሁ ወገኖች ቀደም ሲል ያስለተኗቸው፣ ዛሬ ደግሞ የሚደጉሟቸው ሚዲያዎች ናቸው አብረው የመጡት። አብን ከእነዚህ ሃይላት ጋር በቀጥታ ተባባሪ ይሁን አይሁን ስም ጠቅሶ የሚናገር ባይኖርም፣ አብን አብራቸው ለመስራት ሂደት ከጀመረው ባልደራስ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ኤርሚያስ የ360 ሚዲያ መስራችና አንዱ ባለቤት መሆናቸው ይታወቃል።

ርዕዮትን 360 በጥምረት ተናበው የሚሰሩ ሲሆን ምርጫው ላይ ከወዲሁ ” ኦርቶዶክስ ለህልውናዋ ትነሳ” በሚል ዘመቻ ለመጀመር እቅድ ነድፈው በመስራት ላይ መሆናቸውን በመረጃ ቲቪ በኩል አስታውቀዋል። የአማራ ብልጽግና ሃላፊ እነዚህን ለመንካት ይሁን ለሌላ ሚዲያዎች አብረው በመናበብ እንደሚሰሩ አመላክተዋል። የተባረሩ የቀድሞ ኢህአዴጎች እንደ አቶ ታምራት ላይኔ አይነቶቹ ከመሰለቾቻቸው ጋር ህብረት መፈጸማቸው እንደተደረሰበት፣ ከቀድሞ ኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች ወገን ግን ምላሽ እንዳጡ ጠቁመዋል።

በካናዳ የሚኖርና ቀደም ሲል የአብን አባል ሆኖ ተመልምሎ እንደነበር የሚናገር እንዳለው በሂደት ድርጅቱን ሳቀውና አፈጣጠሩ ሲገባው እራሱን አግልሏል። የአብን አባል ሲሆን ሌሎች አባላትን በተቀጽላ ስም ያውቃቸው እንደነበር፣ በቡድን የማህበራዊ ገጽ አምድ ስልጠና ይወስድ እንደነበርና “ላይሊበላ የአገው ነው” የሚል ትምህርት ሲሰጥ ግራ መጋባቱን፣ ይህ ሲሆን ለበለጠ ትምህርት በሚል እጅግ ታዋቂ የሆነ ኤማህበራዊ ሚድያ ጸሃፊና አንቂ እንዲያስረዳው ከተደረገ በሁዋላ ድርጅቱን በራሱ ፈቃድ ተሰናብቷል። ከዛ በሁዋላ የነበረውን ኔት ዎርክ ተጠቅሞ ባደረገው ክትትል በርካታ መረጃዎች በማግኘቱ አዝኖ መቀመጡን አስታውቋል።

ኢትዮ 12 ከዚህ ሰው ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ በሚቀጥለው ሳምንት ታትማለች።

Exit mobile version