Site icon ETHIO12.COM

ወደ ላልይበላ፣ ጎንደር እና ባህር ዳር ይደረጉ የነበሩ በረራዎች ተስተጓጉለው የነበረው የሱዳን ድንበር አካባቢ ባለው ውጥረት ምክንያት ነው?

ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአንዳንድ የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች ባጋጠመው አስቸጋሪ የአየር ጠባይ ምክንያት ከጥር 29 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ላልይበላ፣ ጎንደር እና ባህር ዳር ይደረጉ የነበሩ በረራዎች መስተጓጎላቸውን የሚገልጽ መልዕክት በፌስቡክ ገጹ ለጥፎ ነበር።

ይህን መልዕክት ተከትሎ በአንዳንድ የትዊተር እና የፌስቡክ ገጾች በረራዎቹ የተቋረጡት በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር በተፈጠረው ውጥረት ምክንያት መሆኑን የሚገልጹ መረጃዎች ተሰራጭተዋል።

በረራዎቹ በአየር ጠባይ ምክንያት ስለመቋረጣቸው ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ ቼክ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጅ ኤጀንሲ የአቪዬሽን ሚቲዎሮሎጅ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ካሳ ፍቃዱን ያናገረ ሲሆን “በረራዎቹ የተሰረዙት ከሱዳን የተነሳ አቧራማ ጭጋግ የሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱን ክፍሎች በመሸፈኑ ነው” የሚል ምላሽ አግኝቷል።

አቧራማ ጭጋጉ የተለመደ እና የአየመቱ የሚከሰት መሆኑንም የገለጹት አቶ አቶ ፍቃዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን የሰረዘው ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጅ ኤጀንሲ በደረሰው መረጃ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል። ባሳለፍነው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት በባህርዳር ነዋሪ የሆኑ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ከተማዋ በአቧራማ ጭጋግ ተሸፍና የሚያሳዩ ምስሎችን ሲለጥፉ ኢትዮጵያ ቼክ የተመለከ ሲሆን ዛሬ ያናገርናቸው ሁለት የከተማዋ ነዋሪዎችም ምስሎቹ ትክክል መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጅ ኤጀንሲ የባህርዳር ቅርንጫፍ ዳሬክተር አቶ ንጋቱ መልሴ ባሳለፍነው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት አካባቢው ከሱዳን በመጣ አቧራማ ጭጋግ ተሸፍኖ እንደነበር እና ከትናንት ጀምሮ ጭጋጉ ወደ ምስራቅ ጎጃም በመሸሹ የበረራ አገልግሎት እንደገና መጀመሩን ለኢትዮጵያ ቼክ ተናግረዋል።

የጎንደር አየር ማረፊያ የሚቲዎሮሎጅ ባለሙያ አቶ አሰፋ በጎንደርም ተመሳሳይ ክስተት እንደነበር ገልጸው ጭጋጉ አካባቢውን በመልቀቁ ከትናት ጀምሮ በረራ መጀመሩን ገልጸዋል። ባለፈው አመትም በሰሜን እና በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ክስተት ተከስቶ የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ መቀሌ፣ ላልይበላ፣ ጎንደር፣ አክሱምና ሽሬ ይደረጉ የነበሩ በረራዎችን ለቀናት ሰርዞ ነበር። ባህርዳር እና አካባቢዋ አቧራማ ጭጋግ ለብሰው የሚያሳዩ ምስሎችም በማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት መሰራጨታቸው ይታወሳል።

#FactCheck Exclusive

Exit mobile version