Site icon ETHIO12.COM

አዲስዓለም ሁከትና ግጭት ለመቀስቀስና ታጣቂዎችን ለመደገፍ ሲሰሩ ነበር- መርማሪ ፖሊስ

አምባሳደር አዲስዓለም ባሌማ ለአምስተኛ ጊዜ በዛሬው እለት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

የፌደራል ፖሊስ የምርመራ ቡድን በፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ከዚህ በፊት በተሰጠው 14 ቀናት ውስጥ የሰራውን የምርመራ ስራ ይፋ አድርጓል።

ተጠርጣሪው ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሻከር ወይም ለማቋረጥ ሲሰሩ ነበር ፣ ከዶክተር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ጋር በጋራ በመሆን በምዕራብ ወለጋ ለኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የግብዓት እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ደረጃ ሲሰሩ እንደነበር እንዲሁም ከእነ አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር በመሆንም ሁከት እና ግጭት ለመስቀስ ሲሰሩ እንደነበር የሚገልፅ የቴክኒክ እና ሌሎች ማስረጃዎች መሰብሰቡን መርማሪ ፖሊስ ገልጿል።

እንዲሁም ከ100 በላይ የሰዎች ምስክር መቀበሉን እና በመሰረተ ልማት ላይ የደረሰ የጉዳት መጠንን በባለሙያ አስለይቶ ከምርመራ መዝገቡ ጋር ማያያዙንም ነው የገለጸው።

በቀሪ ስራዎች ማለትም ወደ ትግራይ ክልል የተላከው የምርመራ ቡድን ውጤቱን ለማምጣት እና ለቀሪ ስራዎች ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው መርማሪ ፖሊስ አስታውቋል።

ተጠርጣሪውም ያረፈደው ጠበቃቸው እስከሚመጣ ልጠብቅ ማለታቸውን ተከትሎ ችሎቱ ከ30 ደቂቃ በላይ ጠብቆ ጠበቃቸው ባለመቅረቡ መዝገባቸውን ለመመልከት ተገዷል።

በዚህ ጊዜ ተጠርጣሪው የዋስትና ጥያቄ ያነሱ ሲሆን ፍርድ ቤቱም የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ መርማሪ ፖሊስ ያቀረበው ምክንያት ተገቢ መሆኑን በመግለፅ 14 ተጨማሪ ቀናት ፈቅዷል።

መዝገቡ ከተጠናቀቀ በኋላ ችሎት የደረሱት ጠበቃቸው አስተያየት ልስጥ ያሉ ቢሆንም ከበቂ በላይ ተጠብቀው መዝገቡ በመታየቱ ፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጓል።

በታሪክ አዱኛ FBC

Exit mobile version