Site icon ETHIO12.COM

አይ ኤም ኤፍ የኢትዮጵያን የተራዘመ ብድርና ገንዘውብ ድጋፍ ስምምነት ገመገመ

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) የባለሙያዎች ቡድን በሁለት ዙር በገመገመው የተራዘመ የብድር እና የገንዘብ ድጋፍ አሰጣጥ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን አስታወቀ፡፡

በሶናሊ ጃይን ቻንድራ የተመራው ቡድን ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ ከብሄራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ ከገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ፣ ከምክትል ገዢው ፍቃዱ ሁሪሶ እና ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች ጋር በበይነ መረብ ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱ በዋናነት ተቋሙ በሁለት ዙር የገመገመው የተራዘመ የብድር እና እርዳታ አሰጣጥ፥ በኮቪድ19 ምክንያት የሚደርሰውን ተፅዕኖ በማመጣጠን እንዲሁም የሃገር ውስጥ ደህንነትን በማረጋገጥ የፖሊሲ ማሻሻያዎቹ ለጠንካራና አካታች እድገት መሰረት መጣላቸውን ማረጋገጥን አላማ ያደረገ ነበር፡፡

የአይ ኤም ኤፍ የባለሙያዎች ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር በሁለት ዙር በገመገመው የተራዘመ የብድር እና የገንዘብ ድጋፍ አሰጣጥ ላይ መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም አይ ኤም ኤፍ ለኢትዮጵያ የ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ብድር ማፅደቁ ይታወሳል፡፡

ያንን ተከትሎም ኢትዮጵያ ተቋሙ የተራዘመ የብድርና የገንዘብ መመለሻ ስርአትን እንዲተገብር የጠየቀች ሲሆን፥ ለዚህ ይረዳ ዘንድም የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን መተግበሯም ይታወሳል፡፡

የተቋሙ ባለሙያዎችም በሃገር ደረጃ የተተገበሩ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች የፖሊሲ ማሻሻያዎችን የገመገሙ ሲሆን፥ ማሻሻያዎቹ ውጤታማ እንደነበሩም ገምግመዋል፡፡ ኮቪድ19 በኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም በጤናው ዘርፍ ከፍ ያለ ተፅዕኖ መፍጠሩን ተቋሙ አስታውሷል፡፡

በሃገር ደረጃ የተተገበሩት የፖሊሲ ማሻሻያዎችም በሃገሪቱ ከኮቪድ19 ጋር በተያያዘ ይደርስ የነበረውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የጤና ተፅዕኖ መቀነስ መቻሉ በባለሙያዎች ቡድን ተገምግሟል፡፡

ይህም ማክሮ ኢኮኖሚው እንዲረጋጋ በማድረግ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉም በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ ባለፈም ብሄራዊ ባንክ በባንኮች ላይ የገንዘብ እጥረት እንዳይከሰት ለማድረግ ለባንኮች ገንዘብ በማከፋፈል የወሰደው እርምጃም ውጤት ማሳየቱም ተነስቷል፡፡

የተወሰዱት ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ኮቪድ19 በሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ መነቀስ እና መቋቋም ማስቻሉም ነው የተነሳው፡፡ ኮቪድ19 ባስከተለው ተፅዕኖ ሳቢያ 23 በመቶ ደርሶ የነበረው የዋጋ ግሽበት አሁን ላይ ወደ 19 በመቶ መውረዱም በዚህ ወቅት ተገልጿል፡፡

በአንጻሩ አሁን ላይ ምግብ ነክ የሆኑ ሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱንንም ነው የገለጸው፡፡ በተያዘው በጀት አመት 2 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደሚመዘገብ ያነሳው ቡድኑ፥ በፈረንጆቹ 2021/2022 የዓለም ኢኮኖሚ እንደሚያገግም በማውሳት ኢትዮጵያ 8 ነጥብ 7 በመቶ እድገት ታስመዘግባለችም ብሏል፡፡

አሁን ላይ የተቀማጭ ገንዘብ ክምችትም የዋጋ ግሽበቱን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማምጣት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ማገዝ ያስችላልም ነው ያለው፡፡ ሃገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያውን ያደነቀው ተቋሙ፥ ማሻሻያው የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ላይ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚያስችልም አስረድቷል፡፡

አሁን በባለሙያዎች ደረጃ የተደረሰው ስምምነት ፀድቆ ተግባራዊ ይሆን ዘንድም ለተቋሙ የዳይሬክተሮች ቦርድ ቀርቦ መፅደቅ እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ከገንዘብ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ማስተማመኛ መገኘት እንደሚኖርበት መረጃውን ጠቅሶ ፋና ዘግቧል።

Exit mobile version