ETHIO12.COM

ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ፡ ከ20 ዓመታት በፊት የተቀዳው የሙዚቃው ንጉሡ ‘ምርቃት’

ያላዜመበት አርዕስት የለም። በሙዚቃ ሥራዎቹ ያልመዘዘው የሕይወት ሰበዝ፣ ያልዳሰሰው የኑሮ ቋጠሮ፣ ያልደረሰበት የሐሳብ ጥግ የለም ይላሉ በርካቶች።

አገርና ሰንደቅ፤ ሰላምና ፍቅር፤ ትዝታና ናፍቆት፤ ማግኘትና ማጣት፤ ሳቅና ለቅሶ፤ ሕይወትና ሞት፤ መውደቅና ስኬት፤ ጥያቄና ምፀት፤ ጊዜና ቀጠሮ፤ ነጻነትና ፍትሕ፤ መውደድና መጥላት፤ እውነትና እብለት፤ ዝምታና ጩኸት፤ ፅድቅና ኩነኔ፤ ሐብትና ድህነት፤ ተፈጥሮና ውበት፤ መጠጥና ምግብ፤ ስለሳር ቅጠሉም. . . ሌላም ሌላም።

እልፍ ሥራዎችን ሰርቷል። ቆጥሮ የደረሰበት ስለመኖሩም እንጃ።

የጠየቅናቸውም “እሱ መሥራት እንጂ ቆጠራው ላይ መቼ አለበት” ነው ያሉት።

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ እንደ ብላቴና የሙዚቃን እግር የሙጥኝ ብሎ ጥበብን ከፍ አድርጓታል። ሙዚቃ እራሷ በእሱ ስም ትጠራ የሚሉለትም አሉ።

ሙዚቃዎቹ በእድሜና በዘመን የሚለዩ አይደሉም። ትውልድ እየተቀባበለው የሚሻገሩ እንጂ።

ታዲያ ሙዚቃ ወዳጁ ብትሆንም እንደ ክፉ ባልንጀራም ፍዳውን አብልታዋለች። ፖለቲካዊ ይዘት አላቸው በተባሉ ሥራዎቹ ቡጢና እርግጫ፤ እንዲሁም እስርን ቀምሶባታል። የሙዚቃው ንጉሥ ክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ።

ጥላሁን በሞት ከተለየ አስራ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል።

በስኳር ህመም ሲሰቃይ የነበረው ጥላሁን ድንገት ባጋጠመው ህመም፤ በ68 ዓመቱ ይችን ዓለም የተሰናበተው ሚያዚያ 12/2001 ዓ.ም ነበር።

ምንም እንኳን በሞት ከተለየ ዓመታት ቢነጉዱም ድምጹ ከሙዚቃ አፍቃሪዎች ጆሮ ርቆ አያውቅም።

ጀማሪ ድምጻዊያንም የእሱን ሥራ የብቃታቸው ጥግ ሚዛን አድርገው ሲያነሱ ሲጥሉ ነው የሚውሉት። በየሙዚቃ ውድድሮቹ ተወዳዳሪዎች ይዘዋቸው ከሚቀርቡ ሥራዎችም አብዛኞቹ የእርሱ ናቸው።

አሁን ደግሞ ‘የመጨረሻው’ የሙዚቃ እስትንፋሱ ለአድማጭ ጆሮ በቅቷል – ምርቃት።

‘ምርቃት’ የአልበሙ መጠሪያ ነው። በውስጡ አስር ዘፈኖችን ይዟል። ዜማው የሞገስ ተካ፤ ያቀናበረው ደግሞ አንጋፋው የሙዚቃ አቀናባሪ አበጋሱ ክብረወርቅ ሺዮታ ነው።

በግጥም ሥራዎቹም ሞገስ ተካን ጨምሮ ያየህይራድ አላምረው፣ ሶስና ታደሰና አለምፀሐይ ወዳጆ ተሳትፈውበታል።

‘ምርቃት’

‘ምርቃት’ ሕይወቱ ካለፈ ከ12 ዓመታት በኋላ ነው የወጣው።

ይህ አልበም የጥላሁን ስንተኛው ሥራ እንደሆነ ግን በቁጥር ያወቀ አላገኘንም።

በግምት ከ300 ወይም ከ400 በላይ የሙዚቃ ሥራዎችን ሳያበረክት እንዳልቀረ ግን ባለቤቱ ወ/ሮ ሮማን በዙ ይናገራሉ።

ወ/ሮ ሮማን “ጥላሁን ምን ያህል ሥራዎችን እንደሰራ ባለሙያም፤ ቤተሰብም መናገር መቻል ነበረበት። ግን ይህን ያህል ሥራ አለው ማለት ያልቻልነው፤ ታሪክ የማሰባሰቡ ሥራ ላይ ደካማ ስለሆንን ነው” ሲሉም ይወቅሳሉ።

በእርግጥ ከሙት ዓመቱ በኋላ የሰራቸውን ሥራዎች ሰብስቦ በታሪክ ለማስቀመጥ ሲንቀሳቀሱ ነበር የቆዩት። ሆኖም ዳር አልደረሰላቸውም።

ይህን አልበም ያቀናበረው እውቁ የሙዚቃ አቀናባሪም “ካሉ አርቲስቶች በጣም ቁጥሩ የበለጠ ሥራ የሠራ አርቲስት እንደሆነ እንጂ ቁጥሩን አላውቀውም፤ ግን በርካታ ነው” ብሏል።

አገራዊ ዜማ ከአልበሙ የማይታጣው ጥላሁን፤ በዚህ አልበሙም ስለ አገር አዚሟል።

“. . . ሴራው ይክሸፍበት የመታብሽ አድማ

እጁን ሳር ያድርገው፤ ጉልበቱን ቄጠማ . . .” ብሎላታል አገሩን ሲመርቅ፤ ጠላቶቿን ሲረግም።

ይህ የሙዚቃ አልበም ስለፍቅር፣ ፍትሕ፣ እርቅ፣ አገር እንዲሁም ስለራሱ ሕይወት የሚያነሱ ሥራዎች የተካተቱበት ነው።

‘ቆሜ ልመርቅሽ’ የተሰኘው አገራዊ ዜማ፤ አሁን ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የሚሄድ በመሆኑ በርካቶች የትንቢት ያህል ቆጥረውታል።

ወ/ሮ ሮማንም “‘ቆሜ ልመርቅሽ’ን ለየት የሚያደርገው የአገራችንን የአሁኑን ሁኔታ የሚያንፀባርቅ መሆኑ ነው” ይላሉ። ‘ያኔ ባለሙያዎቹ ምን ታይቷቸው ነበር?’ ያስባለ እንደሆነም ተናግረዋል።

አልበሙ በሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲንና በአቶ አብነት ገብረመስቀል ፕሮዲዩስ መደረጉን የገለጹት ወ/ሮ ሮማን፤ ‘ምርቃት’ ለሕዝብ እንዲደርስ ላደረጉት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።

ይህ ሙዚቃ በምን ሁኔታ ነበር የተሰራው?

የሙዚቃ አቀናባሪው አበጋሱ ለጥላሁን ሥራዎች እንግዳ አይደለም።

ከዚህ ቀደም የወጡ አራት አልበሞቹን ከሙላቱ አስታጥቄና ቴዲ ማክ ጋር በመሆን እንደገና አቀናብሯል። የአሁኑን ጨምሮ ሁለት አዲስ አልበሞችንም ሰርቷል።

ይህንን አልበም በማቀናበሩም “በጣም እድለኛ እንደሆንኩ ነው የሚሰማኝ” ይላል።

አበጋሱ እንደሚለው ይህ አልበም መጀመሪያ ከተቀረጸ 20 ዓመት ገደማ ይሆነዋል። የቀረጸውም እራሱ ነበር። የተጀመረው አሜሪካ በአበጋሱ ስቱዲዮ፤ የተጠናቀቀው ደግሞ አዲስ አበባ።

‘ምርቃት’ በአበጋሱ እጅ ለ18 ዓመታት ያህል ቆይቷል።

“ከእኔ ጋር መሆኑ ትልቅ እድል ነው፤ በጣም ደስተኛ ነኝ” ይላል አበጋሱ።

በአልበሙ ላይ የምንሰማቸው የጥላሁን ድምፆች ከህመም ጋር እየታገለ ያወጣቸው ናቸው። የልምምድ እንጂ የመጨረሻ ያለቀላቸው ቅጂዎች አልነበሩም።

በዚያ ላይ ደግሞ በህመሙ ምክንያት ወጣ ገባ እየተባለ የተሰራ።

አበጋሱ እንደሚለው በጊዜው ጥላሁን ጥሩ ቀኖችም፤ መጥፎ ቀኖችም ነበሩት። የሁኔታዎችና የስሜት ለውጦችም እንዲሁ።

“ትዝታዎች ውስጥ የሚገባበት ጊዜም ነበር። የዝምታ ድባቦችም ነበሩ። ጥሩ ግንኙነቶችም ነበሩን። ታሪኮችን እጠይቀው ነበር። እኔ ከእርሱ መውሰድ እፈልግ ነበር። ጋሽ ጥላሁን ህልመኛ ነው፤ በራሱ ዓለም የሚሆንበት ጊዜም ነበር” ይላል አበጋሱ-በወቅቱ የነበረውን ሲያስታውስ።

በእርግጥ ያኔ ሙዚቃውን እንደ ሥራ እንጂ፤ ሰው ጋ እንዲህ ዓይነት ስሜት ይፈጥራል ብሎ አላሰበም ነበር።

የምስሉ መግለጫ,ድምጻዊ ሚኒሊክ ወስናቸው፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ አለማየሁ እሸቴና ማህሙድ አሕመድ [ከግራ ወደ ቀኝ]

ጥላሁን ሌሎች ያልወጡ ሥራዎች ይኖሩት ይሆን?

አበጋሱ ይህ አልበም የጥላሁን የመጨረሻ ሥራ እንደሆነ ነው የሚያስበው።

“በእርግጥ እንደ ጥላሁንና ማህሙድ ዓይነት የመዝፈን ፍቅር ያላቸው ባለሙያዎች የሆነ ቦታ ሄደው ‘ሙዳቸው’ ከመጣ ሊዘፍኑ ይችላሉ። በዚህ ምክንያት ያልወጡ ይኖሩ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ” ይላል።

ወ/ሮ ሮማንም ‘ይህን የሚያውቁት ባለሙያዎች ናቸው’ የሚል ምላሽ ሰጥተውናል።

አልበሙ ይህን ያህል ዓመት ለምን ቆየ?

አበጋሱ እንደሚለው ሥራው ሳይጠናቀቅ ጥላሁን ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ ነገሮች እንደታሰቡት አልሆኑም።

ከ20 ዓመታት በፊት የተቀዳን ድምፅ አሁን ካለው ቴክኖሎጂ ጋር ማጣጣም ፈተና ነበር ይላል። ብዙ ድካሞችና ልፋቶች ነበሩት።

የመጨረሻ ቅጂም ስላልነበር ጥላሁን በወቅቱ የነበረበት እውነተኛ ስሜት በድምፁ ተይዟል።

አንዳንዴ ከጀርባ የሚሰሙ ድምፆች ነበሩ። ያንን ማፅዳቱም ጊዜ ፈጅቷል። ቢሆንም ግን “በውጤቱ ረክቻለሁ” ብሏል አበጋሱ።

ከዚህም ባሻገር የነበሩበት የሥራ ጫናዎችም፤ አልበሙ የአፍላ ወጣት እድሜ ያህል ቆይቶ እንዲወጣ ምክንያት ሆነዋል።

አበጋሱ እንዳለው ሙዚቃዎቹን አሳምሮ ለማውጣት የተጠቀመው የተለየ ቴክኒክ የለም። ድምፁን ማሻሻልም አልተፈለገም።

ይሁን እንጂ በተለያየ ጊዜና በተለያየ የሙዚቃ ‘ኪይ’ ሲለማመድ ስለነበር እነርሱን ለማጣጣም “‘አውቶ ቲዩን'[የድምፅ ፒች ማስተካከያ] በትንሹ በመጠቀም ስሜቱን ለማውጣት ሙከራ አድርገናል” ብሏል።

“አንድም ቀን ያለ ስሜት ሲዘፍን አይቼው አላውቅም”

ጥላሁን አንድን ዜማ ሲቀበል ወደ ራሱ በማምጣቱና ወደ ራሱ ቅላጼና ገለጻ በማጣጣም ችሎታው ለአበጋሱ ለየት ይልበታል።

“ከጥላሁን ጀርባ ከባድ ስሜት አለ። መመሰጥ አለው። ከስሜት ጋር ቁርኝት አለው” የሚለው አበጋሱ አንድም ቀን ያለ ስሜት ሲዘፍን አይቶት እንደማያውቅ ይናገራል።

“በህመም ላይ ሆኖም ሲቀረጽ ያ ተፅእኖ አያሳድርበትም ነበር። ታሞም ይመሰጣል። እንደዚያ መሆን ሲያቅተው ‘በቃኝ ቤት ውሰደኝ’ ይለኛል” ይላል አበጋሱ።

አበጋሱ እንደሚለው ጥላሁን ስሜት ከሌለው ለሙዚቃ የሚገባውን ነገር ያልሰጠ ይመስለዋል።

ወ/ሮ ሮማንም ሥራዎቹ በግርድፍ ያሉ ስለነበሩ እንደዚህ ይሰራል የሚል ሃሳብ እንዳልነበራቸው ገልፀው፤ “ታሞ የነበረ ድምፅ እኮ ራሱ ታሪካዊ ነው” ይላሉ።

“ጥላሁን የሙዚቃ ጥጉን አስቀምጦ የሄደ ባለሙያ ነው። እያቃሰተም፤ እያለቀሰም ቢዘፍነው ታሪክ ነው” ብለዋል ወ/ሮ ሮማን።

የዋለውን ያህል ያልተዋለለት ጥላሁን

ጥላሁን ይህችን ዓለም ከተሰናበተ ድፍን 12 ዓመታት ተቆጥረዋል።

ነገር ግን ከዘመን አይሽሬ ሙዚቃዎቹ በስተቀር ለስሙ መጠሪያ አንድም ማስታወሻ አልቆመለትም፤ አልተሰየመለትም። ለምን? ይህ የብዙዎች ጥያቄ ነው።

ባለቤቱ ወ/ሮ ሮማን ለጥላሁን በስሙ መንገድ ለማሰየም፤ አደባባይ ለማሰራት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን በር ሲያንኳኩ ነው የቆዩት። ግን በአሰቡት ልክ አልሄደላቸውም።

“ጥላሁን የገንዘብ ሰው አይደለም። እያነባ እያለቀሰ ‘አገሬ አገሬ’ እያለ የሞተ ሰው ነው። ይህንን ሥራ ለሰራ ሰው፤ አደባባይ ለመሥራት እንኳን 12 ዓመት 12 ወር መፍጀት አልነበረበትም” ይላሉ ወጥተው የወረዱትን በማስታወስ።

ለነገሩ ወደ መሿለኪያ አካባቢ አደባባይ ለማሰራት ፈቃድ አግኝተው ነበር። ይሁን እንጂ ኋላ ላይ ቀለበት መንገድ ተሰርቶበት በመፍረሱ ሳይሆን መቅረቱን ይናገራሉ።

ተለዋጭ ቦታ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም ሰሚ ሳያገኙ ቆይተዋል።

“አሁን ከረዥም ዓመታት በኋላም ቢሆን፤ በአገር ደረጃ መታየት የነበረበት ባለሙያ በክብር ስለታየልን ደስ ብሎናል” ብለዋል ወ/ሮ ሮማን።

ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ እና ባለቤቱ ሮማን በዙ
የምስሉ መግለጫ,ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ እና ባለቤቱ ሮማን በዙ

ይህን ያህል ደጅ መጥናት ለምን? ያልናቸው ወ/ሮ ሮማን ዝርዝር መልስ አልሰጡም።

“ምንም እንኳን ጥላሁን የአገር ሐብት ቢሆንም፤ የሚመጣውም፤ የሚሄደውም መንግሥት ጥላሁንን እንዴት ያየዋል የሚለው ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው” ሲሉ በደምሳሳው አልፈውታል።

“ባለታሪክን የምናደንቀውና የምናወድሰው ጊዜና ወቅት እየጠበቅን መሆን የለበትም” ሲሉም በተለያየ ሙያ ላይ ብዙ ጀግኖች አስታዋሽ አጥተው ደብዛቸው ጠፍቶ የቀሩ ስለመኖራቸው ያወሳሉ።

በዚህ መንግሥት የታየው ጭላንጭል ግን ተስፋ ሰጭ ነው ብለዋል።

በጥላሁን ስም ምን ለመስራት ታስቧል?

ጥላሁን በሕይወት እያለም፤ ከህልፈቱ በኋላም በስሙ ለመስራት የተያዙ ፕሮጀክቶች እንደነበሩ ወ/ሮ ሮማን ይናገራሉ።

ወ/ሮ ሮማን እንደሚሉት ጥላሁን የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎች በነጻ የሚታከሙበት የስኳር ህሙማን ሆስፒታል ለማቋቋም ቃል ገብቶ ነበር።

እርሱም ጤንነቱ የተጓደለው በዚሁ በሽታ ነበር።

በሕይወት ሳለም ሆስፒታሉን ለማሰራት የተወሰነ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ግን ይህ እውን ሳይሆን ነው ሕይወቱ ያለፈው።

“ከስኳር ህሙማን ማኅበር ጋር ለመስራት ተስማምተን፤ የሆስፒታሉ ዲዛይን ተቀርጾ እዚያ ላይ ነው በእንጥልጥል የቆመው” ብለዋል ወ/ሮ ሮማን።

ሙዚቃዎቹን እንዲሰባሰቡ ለማድረግ ሞክረውም በቤተሰብ አቅም ይህን ማድረግ ሳይቻል ቀርቷል።

አሁን ምላሽ ያገኘው የአደባባይ ጉዳይም የእቅዳቸው አካል ነበር።

የሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲሁም ሌሎች መታሰቢያዎችን ለመስራት እየታሰበ መሆኑን ወ/ሮ ሮማን ተናግረዋል።

“ባለሙያውም፣ ባለሃብቱም፣ መንግሥትም ተረባርቦ እቅዱ እውን እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

Exit mobile version