Site icon ETHIO12.COM

የመቀሌ ቆይታዬ !

በ : Fekadu Getachew Mesfin

የመቀሌ ቆይታዬን በተመለከተ ለጠየቃችሁኝ እነሆ ትዝብቴን ይኸው።

በትግራይ ክልል 12ኛ ክፍል ለመፈተን ከየትምህርት ቤቱ የተመረጥን መምህራን የተመደብነው በራያ ፣ በመቀሌ ፣ በሽሬና በአክሱም ዩኒቨርስቲዎች ሲሆን እኔ የደረሰኝ ኩኽያ የሚገኘው መቀሌ ዩኒቨርስቲ መለስ ዜናዊ ካምፓስ ነበር።
ከአዲስ አበባ ሳልነሳ በፊት ቤተሰቦቼም ሆኑ ጓደኞቼ እንዳልሔድ የቻሉትን ምክር ቢመክሩኝም ከተማዋን ከሚንጣት የስጋት መንፈስ ጋር እየታገልኩ ከነፍርሃቴ በ25/06/13 በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአክሱምና ከሽሬ ምድብተኞች ጋር በረርኩ። የራያ ምድብተኞች ግን ከአዲስ አበባ በመኪና ተንቀሳቀሱ።

ወደ አስር ሰዓት አካባቢ መቀሌ ከተማ ገባን። በሶስት ተከፍለንም አክሱም ሆቴል፣ ዘማሪያስ ሆቴልና፣ አፄ ዮሃንስ ሆቴል አረፍን። ከአንድ ተጨማሪ ቀን አዳር በኋላ የአክሱምና ሽሬ ተጓዦች በመኪና ጉዞ ስለጀመሩ የመቀሌ ፈታኞች በሙሉ አክሱም ሆቴል ገባን።

ከዚህ ይዤው ከሔድኩት ፍርሃት እና ሽብር ጋር እየታገልኩ ብቻዬን ወጥቼ በእግሬ የቻልኩት ያህል ወክ አደረግኩ።
አልፎ አልፎ መከላከያ ፓትሮል ሲያደርግ እና በአገልግሎት ላይ ያሉ ባንኮች በመከላከያ ሲጠበቁ ከማየቴ ውጪ ከተማዋ ላይ ሕይወት በሰላም ቀጥላለች። ከመንገድ ላይ ንግድ ጀምሮ ከትንሽ እስከ ትልቅ ሆቴሎች ባሮች ግልጋሎት ከመስጠት አልፈው ደመቅመቅ ያሉ ነበሩ።የጀበና ቡና መሸጫዎችም በብዛት ደንበኛ ሲያስተናግዱ ታዝቤአለሁ። ከዚሕ በኋላ ፍርሃቴ ሙሉ በሙሉ ስለጠፋ በቀጣይ ቀናት ከሊስትሮው እስከ ባጃጅ ሹፌሮች ስላለውና ስለነበረው ነገር ለማውራት ሞክሬያለሁ።

መቀሌ በኮማንድ ፖስት ስር በመሆኗ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኋላ ረጭ ትላለች። ቀን በየቅያሱ ጠረጴዛ ሞልቶ ሲጠጣ ሚታየው ወጣት አንድ ሰአትን በስካር አይገድፋትም።
እኛ ከመግባታችን በፊት ሰዓት እላፊው የሚያልቀው ከምሽቱ 12 ሰዓት የነበረ ቢሆንም እሱን ጥሰው የተገኙ ወጣቶች ርምጃ እንደተወሰደባቸው ከየሰፈሩም ወጣቶች መገደላቸውን ከብዙ ሰዎች ሰምቻለሁ። አሁን ላይ ግን ግፋ ቢል በዱላ ብቻ እንደሚጠቀሙ ራሳቸው ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

እዚህ ያለው የሽብር ወሬ እዛ በተግባር የለም አንዲት ጥይት ስትጮህ በቆይታዬ አላስተዋልኩም። ፈተና ከተጀመረበት 29/06/13 ሰኞ ጀምሮ ከአክሱም ሆቴል እስከ ኩኽያ መቀሌ ዩኒቨርስቲ መለስ ዜናዊ ካምፓስ በሰርቢስ ስንመላለስ ጥቃት የተፈፀመበት ሰሜን እዝን ጨምሮ በየቦታው ካምፖችን እና በርካታ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ማየት የተለመደ ሲሆን ከመቀሌ ኩህያ መሔጃ መንገድ ኬላ ላይ ጠንካራ ፍተሻ ይደረጋል።

የሶስት ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ሽመልስ አብዲሳ አሻድሌ ሃሰን እንዲሁም የጋምቤላው መስተዳድር የመጡ ቀን ሕዝቡ የንግድ ተቋማትን በመዝጋት ተቃውሞውን አሳይቷል።
ሰብዓዊ ድጋፍን በተመለከተም የሱር ኮንስትራክሽን ተሳቢ መኪኖች እህል ጭነው ያለማቋረጥ ወደተለያዩ የትግራይ ክልሎች ሲሔዱ አይቻለሁ።

በተረፈ <

ስለፈተናውና ሌሎች ትዝብቶቼ በቀጣይ እፅፋለሁ።

Exit mobile version