Site icon ETHIO12.COM

ኦነግ ምርጫ ቦርድ ከፈቀደለት በምርጫው እንደሚወዳደር አስታወቀ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ ምርጫ ቦርድ ከፈቀደለት በምርጫው እንደሚወዳደር አስታወቀ። ለሁለት ቀናት አጠቃላይ ጉባዔውን ያካሄደው ፓርቲው አዲስ ሊቀመንበርም መርጧል። ፓርቲው ባደረገው ጉባኤ አቶ አራርሶ ቢቂላን የግንባሩ ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል።

አቶ ብርሃኑ ለማ እና አቶ ቀጄላ መርዳሳን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ሆነዋል። ጉባዔው 43 ቋሚ እና 5 ተለዋጭ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትንም መርጧል። በጠቅላላ ጉባኤው ህገ ደንቡን ያሻሻለው ፓርቲው የስነ ስርዓትና ቁጥጥር ኮሚቴም አቋቁሟል። ፓርቲው እራሱን ከምርጫ ማግለል እንደማይፈልግ የገለጸ ሲሆን የዕጩዎች መዝገባ ከመጠናቀቁ ጋር በተያያዘ ግን ምርጫ ቦርድ ከፈቀደ ወደ ምርጫው እንደሚገቡም አስረድተዋል።

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከጥቂት ወራት በኋላ በሚካሄደው ምርጫ እንደማይሳተፍ ባወጣው መግለጫ ማውጣቱ አይዘነጋም። ቀደም ብሎ ኦነግ እንደ ድርጅት ጉቤውን አካሂዶ ሪፖርት ማቅረብ ባለመቻሉ ምርጫ ቦርድ መሰብሰቢያ አዳራሽና ታዛቢ እንደሚመድብ ቢገልጽም አቶ ዳውድ ከሚቃወሟቸው አብዛኞች ጋር ታዛቢ ፊት ለመሰብሰብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸው የሚዘነጋ አይደለም። በመጨረሻም አቶ አራርሳ የሚመሩት ቡድን ጉቤውን አካሂዶ አቶ ዳውድን በማስወገድ አዲስ ማዕከላዊ ኮሚቴና የዲሲፒሊን ኮሚቴ ማቋቋሙን ይፋ አድርጓል።

አቶ ዳውድ አቶ አራርሶ የሚመሩትን ቡድን እንደማይቀበሉ ያስታወቁ ሲሆን፣ አስቀድመውም ፖሊስ ምርጫውን እንዲያስቆም፣ ከቢሮም እንዲያሰናብታቸው የሚጠየቅ አቤቱታ ለፖሊስ አሰምተው ነበር። አገር ቤት ከገባ በሁዋላ ለሁለት ተከፍሎ በየፊናው ሲጓዝ የነበረው ኦነግ ዋና የልዩነቱ ምክንያት ድርጅቱ በጫካ ውስጥ ካለ ሃይል ጋር የሚያደርገው ሚስጢራዊ ግንኙነት፣ ከትህነግ ሃያሎች ጋር የተዘረጋው የህቡዕ የትብብር ትግልና አቶ ዳውድ የምክር ቤት ስብሰባ እንዲጠሩ በተደጋጋሚ ለቀረበላቸው ጥያቄ ዝምታን በመምረጣቸው እንደሆነ በወቅቱ ሲገለጽ ነበር።

Exit mobile version