Site icon ETHIO12.COM

በሰሜን ሸዋና ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች የተከሰተው የፀጥታ ችግር አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩን የክልሉ ሰላምና ደህንነት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች የተከሰተው የፀጥታ ችግር አንጻራዊ ሰላም መፈጠሩን የክልሉ ሰላምና ደህንነት ቢሮ አስታወቀ፡፡


የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ በክልሉ የተከሰተውን የፀጥታ ችግር አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
የፀጥታ ችግሩ የተከሰተው መጋቢት 1ዐ/2ዐ13 ዓ.ም በአንድ ሰላማዊ ነዋሪ ላይ በተፈፀመ ጥቃት ነው ያሉት ኃላፊው በዋናነት ጉዳዩ ታቅዶበት ኦነግ ሸኔ በተባለ አሸባሪ ቡድን የተቀነባበረ የሽብር ድርጊት በሰላማዊ ሰዎች ግድያ እና ሃብት ንብረት ማውደም ላይ ያነጣጠረ ዕቅድ እንደነበር የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

አማራ ክልልን የትርምስ የብጥብት ቀጠና ለማድረግ ታቅዶበት የቀጠናው የመንግስት ኃላፊዎች ጭምር በሚያሳፍር መንገድ ተባባሪ ሆነው የክልሉን ህዝብ ሰላም ለመንጠቅ የተደረገ ጥረት እንደነበር አብራርተዋል፡፡

አቶ ሲሳይ በመግለጫቸው የፀጥታ መዋቅሩ በወሰደው የተቀናጀ የፀጥታ ማስከበር ስራ ዛሬ ላይ በአጣየ፣ ሸዋሮቢት ፣ ከሚሴ ፣ ማጀቴ ፣ ሰበቴ እና ጀውሃ አካባቢዎች አንፃራዊ መረጋጋት ቢኖርም ህብረተሰቡ በስጋት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የሽብር ድርጊቱ ኤፍራታና ግድም ወረዳ፣ አጣየ ከተማ አካባቢዎች እንደተጀመረ የገልፀት አቶ ሲሳይ በኦሮሞ እና በአማራ ተወላጆች መካከል ያለውን ግንኙነት በማሻከር ሁለቱን ብሔሮች ወዳልተፈለገ ትርምስ ለመክተት የታሰበና የታቀደ ነበር ብለዋል ኃላፊው፡፡n
አቶ ሲሳይ በመግለጫቸው ጨምረውም በቀጠናው ለጠፋው የሰው ህይወት ፣ ሀብትና ንብረት በህግ አግባብ የሚጠየቀውን አካል እንዲጠየቅበት መረጃው እየተሰበሰበ ይገኛል ብለዋል፡፡ፀጥታ ችግሩን በመቆጣጠር በኩልም የአማራ ልዩ ኃይልና የፌዴራል ፖሊስ በትብብር መስራታቸው አመስግነዋል፡፡

አቶ ሲሳይ የአማራ ልዩ ሀይል የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ እየሰራ ያሉውን ስራ በእጅጉ አድንቀው ልዩ ሃይሉ ምንም እንኳን የአማራ ስም ቢሰጠው በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ማንኛውም ነዋሪ ሰላም መረጋገጥ እየሰራ ያለ ኢትዮጵያዊ ስብዕናን የተላበሰ ነው፤ ይህን
ሃይል ያልተገባ ስም የሚሰጡ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታረሙ አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ ከመችውም ጊዜ በላይ አንድ ሆኖ ጠላቱን በመመከት ሰላሙን መጠበቅ አለበት ያሉት ሃላፊው ህዝቡ የተጋረጠበትን የሰላም መደፍረስ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት በመመከት የአባቶቹን ታሪክ መድገም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

አማራ ኮሚኒኬሽን
መጋቢት 14/2013 ዓ.ም

Exit mobile version