Site icon ETHIO12.COM

በመሬት ጉዳይ የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስችሉ ጥናቶች ይፋ ሆኑ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ ትብብር በከተማ መሬት ጉዳይ የሚስተዋሉ አለመግባበቶችን መፍታት የሚያስችሉ ጥናቶች ይፋ ተደረጉ፡፡ጥናቶቹ በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ፣ በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት ፕሮጀክትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል አማካኝነት የተሰሩ ናቸው፡፡

በሁለቱ ተቋማት የተሰሩት 12 የጥናት ውጤቶች የከተማ መሬት ላይ ፖሊስ እንዲዘጋጅና ውይይት እንዲካሄድ እንዲሁም ለተለያዩ ምርምሮች ግብዓት ማግኛ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው ተብሏል፡፡ ጥናቶቹ ይፋ በሆኑበት መርሃ ግብር ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ክፍል መምህርና የጥናቱ አስተባባሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሙራድ አብዶ እንዳሉት፤ ከዚህ ቀደም የወጡ የከተማ መሬት ሕግጋት ጉድለቶች አሉባቸው።ሕግጋቱ በአወጣጥ ሂደታቸው፣ ግልጸኝነትን በተመለከተና አፈጻጸማቸው ላይ ጉደለት እንደሚታይባቸው ጠቁመዋል

ጉድለቶቹን ለማረምና የመፍትሄ አቅጣጫ ለማመላከትም 12 ጥናቶች መካሄዳቸውን ተናግረው፤ በጥናቶቹ የተመላከቱት ጉድለቶች የሚፈቱባቸው ምክረ ሃሳቦች መቀመጣቸውን አስረድተዋ፡፡ተቀባይነት ያለው የከተማ ፖሊሲ የቤቶች ልማት ችግርን፣ በምግብ ዋስትና፣ በአካባቢ ጥበቃና በማኅበራዊ ፍትህ የሚታዩ ጉድለቶችን የሚፈታ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

ጥናቶቹ ሲሰሩም የታዩ ጉድለቶችን በሚፈታ መልኩና ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት በሚሆኑበት ሁኔታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት ፕሮጀክት ምክትል ዋና ሃላፊ አቶ ማንደፍሮት በላይ በበኩላቸው በጥናቶቹ ውጤቶች ዙሪያ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ውይይቶች መካሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ጥናቶቹ በሚሰሩበት ወቅትም በርካታ ሃሳቦች መነሳታቸውን ገልጸዋል፡፡የሚመለከተው የመንግስት አካል የምርምር ውጤቶቹን ወደፊት ለሚወጡ ፖሊሲዎችና ማሻሻያዎች በግብዓትነት ሊጠቀምበት መግባባት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል፡፡

በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት ፕሮጀክት ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ በፍትህ ዘርፍ ለውጥ እንዲመጣ ተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል።

Exit mobile version