Site icon ETHIO12.COM

” የእዳጋሀሙሱ አዛውንት እንባ “

ታሪኩ ፤ በትግራይ ክልል እዳጋሀሙስና አካባቢው ላይ ወንጀለኞችን አድኖ ለህግ በማቅረብ ተልዕኮ ወደተሰማራ አንድ የሰራዊቱ ክፍል ለስራ ጉዳይ ስልክ በደወልኩ ጊዜ የተነገረኝ ነው ።

የእዳጋሀሙሱ አዛውንትና ታሪኩን ያካፈለኝ የሰራዊቱ አመራር ጊዜ ወስደው የሆድ የሆዳቸውን ብዙ የተጨዋወቱ ቢሆንም ፤ እኔ ግን እንዳንሰለች አንዷን ነጥብ ብቻ መርጫለሁ ፤ ጁንታውን በተመለከተ አዛውንቱ በምሬት የተናገሩትን ።

” የእዳጋሀሙሱ አዛውንት እንባ ” ብየዋለሁ ፡፡መልካም ንባብ :-

ሲመቻቸው መሀል አዲስ አበባ ገብተው ከሚረሱን ፤ የግል ጥቅማቸው ሲነካ ደግሞ በየዋሻው ተወሽቀው ለጦርነት ከሚያጩን አዋራጆች ይልቅ ፤ በክፉውም በበጎውም ጊዜ እኛን መስሎ የኖረው ሠራዊት ነው – የእኛ ።

” የራሷን ግልገል የበላች ድመት ለዶሮ ጫጩት ምን ግድ አላት ” እንዲሉም ፤ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የተሻለ ሀሳብ ባላቸው ታጋይ ልጆቻችን ደም እየታጠበ እዚህ የደረሰው ሰውበላ ቡድን ፤ መብራት አጥፍቶ በጥቁር ምሽት የመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ያን በደልና ግፍ ሲፈፅም ፤ የመሸው የእኛ ልብና ህሊና ውስጥም ነበር ።

አክሱም ፅዮን አስቀድሰን ፤ አልነጃሺ መሰጊድ ሶላት ሰግደን ፤ ስጋ ወደሙን ተቀብለን ፤ እንደየ እምነታችን ለፈጣሪያችን ተገዝተን ለምንኖረው ለእኛ ፤ ክቡሩ የዕምነት ቤታችንን የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ያደረጉት እምነት የለሾች ፤ ባንታደል እንጂ ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባ ነበር ።

ለሩብ ክፍለ ዘመን በቀረበ ዕድሜ ከሰራዊቱ ጋር የገነባነውን ወዳጅነት ፣ የመሰረትነውን ትዳር ፣ ያፈራነውን የጋራ ሀብትና የቀለስናትን የጋራ ጎጆ በአንዲት ምሽት በእብሪት የናዱብን ከሀዲዎች ፤ ባንታደል እንጂ ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባ ነበር ።

ለጊዜው የምናፈርሰውን መሰረተ ልማት መልሰን በሶስት ወር ውስጥ እንገነባዋለን አትጨነቁ ብለው ፤ ለሶስት ወር ያህል ጭለማ ውስጥ ያቆዩን ፤ ያለ ምግብና ውሀ በቤት ውስጥ አሽገውን የራሳቸውን ህይወት ለማትረፍ በየጢሻው የተደበቁት ከሀዲዎች ፤ ባንታደል እንጂ ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባ ነበር ።

ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ብቻ ሲባል የመከላከያ ሰራዊቱንና የኤርትራን ሰራዊት ወታደራዊ አልባሳት አምርተው በወንጀለኞች ግፍ ያስፈፀሙብን ግፈኞች ፤ ባንታደል እንጂ ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባ ነበር ።

በለኮሱት የጦርነት እሳት ማህበራዊ ቀውስ የፈጠሩብን ፤ ቀውሱን ፈጥረውብንም ሰብአዊ እርዳታው እንኳን እንዳይደርሰን እንቅፋት የሆኑን ጉዶች ፤ ባንታደል እንጂ ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባ ነበር ።

” ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ ” እንዲሉ ግን ፤ ዛሬም እንዳለመታደል ሆኖ ፤ የዚሁ ህሊና ቢስ ቡድን የውስጥና የውጪ ርዝራዦች ፤ በፕሮፓጋንዳዎቻቸው ለይቅርታ ሳይሆን ለተጨማሪ በደል ፤ ለፍቅር ሳይሆን ለተጨማሪ ጠብና ጥላቻ እያፈላለጉን ስለመሆኑ ስሰማ ፤ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የተሰዋ ልጄን አስታውሼ አልቅሻለሁ።

የእኔ ልጅ ፤ ልጄ በረሀ ወጥቶ የነበረው ለዕኩልነት መሆኑን ሳስብና ፤ ይህ ቡድን ደግሞ ዕኩልነትን እንደ ውርደት ቆጥሮ ” አለቅነት ወይም ሞት ! ” ብሎ በስተርጅናም ተራራ ለተራራ መንጠላጠልን ገንዘቡ አድርጎ ሳይ ፤ ልጄን ያጣሁት አሁን እንደሆነ ያህል ተሰማኝ ። ለካስ የተሰለፈው በአላማ ከማይመስሉት ጋር ኖሯል አልኩ ።

በእነዚህ ሰዎች ህሊና ውስጥ እውነትም ፣ እምነትም ፣ ፍቅርም ፣ ሚዛናዊነትም ፣ ግብረ ገብነትም ፣ ጥበብም ፣ ማስተዋልም የለም ።

በእነዚህ ሰዎች ህሊና ውስጥ ታጭቆ የሚገኝ ሁለት ነገር ብቻ ነው ፤ የበዛ ዘረኝነትና አለቃ ሆኖ የመኖር ፍላጎት ።

እንደልብ ሰውነቴ የሚታዘዝ ቢሆን ፤ ልጄ ያኔ የወደቀለትን አላማ ፤ ዛሬ እኔ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን ተሰልፌ ባሳካሁት ነበር ።

ነገር ግን እንደምታየኝ አቅመ ደካማ ነኝ ፤ የማውቃቸውን ወንጀለኞች ለመጠቆምና መንገድ ለማመላከቱ ግን ዛሬም ቢሆን አልሰንፍም ።

የፈረሰ ቤቴን ሲጠግን ፤ እንኳን ወዳጅ ጠላትም ቢሆን እተባበራለሁ እንጂ ፤ የሚያፈርሰው ነው የኔ ወገን ብዬ ጎጆዬን ከሚያፈርሰው ጋር ስለምን እተባበራለሁ ።

እነኚህ ሰዎች ዛሬም አሳቻ ሰአት እየጠበቁና ቤት ለቤት እየዞሩ ፤ ” ኑ ሀገር እናፍርስ ” በሚል ወጣቱን በድብቅ ለዕልቂት ለመመልመል እየሞከሩ ነው ፤ ምንም እንኳን ሰሚ ጆሮ ባያገኙም ።

እንዲያም ስል ግን ፤ አንድ ፣ አንድ አላዋቂን ወይም ደግሞ እንደነሱ በዘረኝነት የታወረና ለእኩልነት ሳይሆን ለበላይነት መታገል የሚሻ ይጠፋል ማለቴ አይደለም ።

የሆነው ሆኖ ፤ እኛ ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር ነን ። የፈረሰውን እንጠግናለን እንጂ ፤ ዳግም ለማፍረስ በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ለተጠመደው አጥፊው ሀይል ጆሮ አንሰጥም ።

ነጻነት ሸዋንግዛው – መጋቢት 17 ቀን 2013. Via – Defense FB

Exit mobile version