Site icon ETHIO12.COM

የማህበር ቤት ምዝገባ ከነገ ጀምሮ እንደሚካሄድ ተገለጸ

ከነገ ማክሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አስራ አምስት ቀናት የማህበር ቤት ምዝገባ እንደሚካሄድ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚታየውን የመኖርያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ በ10/90፣ 20/80 እና 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም ቤቶችን በመገንባት በዕጣ ለተጠቃሚዎች አስተላልፏል፤ በቀጣይም ለባለዕድለኞች ለማስተላለፍ ቤቶችን በመገንባት ላይ እንደሆነ ቢሮው አስታውሷል፡፡

የነዋሪችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለመመለስ ሌሎች የቤት አማራጮችን ለመተግበር በ2005 ዓ.ም በ20/80 እና የ40/60 መርሐ ግብር ከተመዘገቡት ቤት ፈላጊዎች አቅም እና ፍላጎት ያላቸው በጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤት የህብረት ሥራ ማህበር ተደራጅተው ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ጊዜያቸውን በማቀናጀት የቤት ችግሮቻቸውን በጋራ ጥረት ሊፈቱ የሚችሉበትን መንገድ በማመቻቸት ተጠቃሚ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱንም ገልጿል፡፡

በዚህም መሰረት ከነገ ማክሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም አንስቶ በማህበር ተደራጅተው ቤት ለመገንባት አቅም እና ፍላጎት ያላቸውን ነዋሪዎች ምዝገባ ማካሄድ እንደሚጀመር ቢሮው አስታውቋል፡፡በመሆኑም ቀደም ሲል የ2005 ነባር የ20/80 እና 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም ተመዝጋቢ የሆኑ፣ ቁጠባቸውን ያላቋረጡ፣ በማህበር ተደራጅተው ቤት ለመስራት ፍላጎቱ ያላቸው እና ከእያንዳንዱ አባል የሚጠበቀውን የቤቱን ወጪ የ70 በመቶ በቅድሚያ ለመክፈል ፈቃደኛ የሆኑ ተመዝጋቢዎች በማህበር ከተደራጁ በኋላ ወደ ቢሮ መምጣት ሳያስፈልጋቸው በቀጥታ (Online) በቢሮው አድራሻ www.aahdab.gov.et አማካኝነት ከነገ ማክሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 15 ተከታታይ ቀናት (ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ) ምዝገባችውን ማካሄድ እንደሚችሉ ቢሮው ገልጿል፡፡

በምዝገባ ወቅት ችግር ያጋጠማቸው ተመዝጋቢዎች ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኋላ በቢሮ ቀርበው ማመልከት የሚችሉ መሆኑን ቢሮው ጠቁሟል።ነባሩ እና መደበኛው የ20/80 እና 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም ግንባታ ስራ በተለመደው አሰራር እንደሚቀጥል ቢሮው አስታውቋል፡፡(ምንጭ፡-የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት)

Exit mobile version