Site icon ETHIO12.COM

በትግራይ የኮማንድ ፖስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰዓት እላፊ ገደብ አሻሻለ፤

በትግራይ ክልል ለአራት ወር ሥራ ላይ በዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደነገገ የሰዓት እላፊ ገደብ ማሻሻያና የአዋጅ መተግበሪያ መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊ መሆን መጀመሩን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ኮማንድ ፖስት አስታወቀ፡፡

የኮማንድ ፖስቱ አባልና የጊዜያዊ አስተዳደሩ የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ንጉሴ በአዋጁ የሰዓት እላፊ ማሻሻያና አስፈላጊነት እንዲሁም በአዋጅ መተግበሪያ መመሪያ ዙሪያ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ሀላፊው በሰጡት ማብራሪያ በክልሉ ያለው ሠላም እየተሻሻለ መምጣቱን ተከትሎ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ይበልጥ እንዲነቃቃ በአዋጁ የተደነገገው የሰዓት እላፊ ገደብን ማሻሻል አስፈልጓል፡፡

በተለይም በፋብሪካዎችና በግል ተቋማት የሚሰሩ ሠራተኞቸ ከሥራ ባህሪያቸው አንጻር እስከ ምሽት የሚሰሩ ሰራተኞችን ከግንዛቤ በማስገባት እስከ ምሽቱ አንድ ሰአት የነበረው የሰአት እላፊ ገደብ ወደ ምሽት ሁለት ሰዓት እንዲራዘም መሻሻሉን አስታውቀዋል ።አዋጁ እስካሁን የመተግበሪያ መመሪያ ሳይወጣለት የቆየ በመሆኑ የወንጀል ድርጊቶች መፈጸምና ለሌሎች ጉድለቶች ምክንያት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል ።

ኮማንድ ፖስቱ ሁኔታውን ከገመገመ በኃላ የአዋጅ መተግበሪያ መመሪያ ማዘጋጀቱን የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡መመሪያው በዋነኛነት የህብረተሰቡን ዕለታዊ እንቅስቃሴ ለመግታት ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ማድረግ ፣አሉባልታ መንዛት፣ የንግድ ተቋማት መዝጋት፣ አድማ ማድረግ ያለ በቂ ምክንያት ከሥራ ቦታ የመቅረት ክልከላዎችን ያካተተ መሆኑን አብራርተዋል።

መመሪያው የተቀመጡ ክልከላዎች ተላልፈው ሲገኙና ሲፈጸሙ በገንዘብና በእስራት ለመቅጣት የሚያስችል ሆኖ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።መመሪያው ክልሉን ወደ ቀደመ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ በማድረግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን የማነቃቃት ዓላማ ያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል ።የሰዓት እላፊ ገደብ ማሻሻያና የአዋጅ መተግበሪያ መመሪያው ከትላንት በስትያ ጀምሮ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ሀላፊውን ጠቅሶ የዘገበው ኢ ፕ ድ ነው።


Exit mobile version