Site icon ETHIO12.COM

ደመቀ መኮንን – የድሆችን ጭፍጨፋ መኖሪያቸው ያደረጉና ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ ላይ አርምጃ ይወሰዳል

“…የድሃ ሞት እና ጭፍጨፋ እንዲሁም ያልተረጋጋች ሃገር መፍጠር የእርካታ ምንጫቸውና መኖሪያቸው ያደረጉ ኃይሎችን ያለምህረት የመታገል እንዲሁም በየደረጃው ኃላፊነታቸውን የማይወጡ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያስተላለፉት መልዕክት ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሠረት ድንጋይ ለተጣለበት 10ኛ ዓመት በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን ለማለት እወዳለሁ።

ሃገራችን የልማት እና ዕድገት ውጥኗን በፍጥነት ለማስቀጠል ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ አቅም መሰረት ከሚጥሉ የመሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል በቀዳሚነት የሚነሳው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክታችን ነው።

ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከምንም በላይ በቀዳሚነት የሚጠቀስበት ትልቁ ምክንያት ታሪካዊ ትርጉም እና ኢኮኖሚያዊ ፍቺ በመያዙ ነው።

ለዘመናት ያለአንዳች ፋይዳ ሲፈስ የነበረው ታላቁን የአባይ ወንዛችንን ለሃይል ማመንጫነት ሙሉ በሙሉ በራሳችን ሃሳብ፣ ጉልበት እና ገንዘብ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት የመሰረተ ድንጋይ አስቀምጠን አሁን የግንባታውን ሂደት ወደ ማገባደጃ ምዕራፍ መሸጋገራችን ታሪካዊ ትርጉሙን ይበልጥ ከፍ ያደርገዋል።

በተያያዥነት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የሀገራችንን የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽለው ከመሆኑ ባሻገር፤ ለታችኛው ተፋሰስ ሃገሮች እና ለቀጠናው ሃገራት በሃይል ልማት ጠንካራ ትስስር መፍጠር ማስቻሉ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ፍቺ ይይዛል።

ባሳለፍናቸው የግንባታ ዓመታት በፕሮጀክቱ አፈፃፀም ዙሪያ የተስተዋሉ ክፍተቶችን በጥናት በመለየት እና የዕርምት ዕርምጃዎችን በትኩረት በመውሰድ ግንባታው ወደ ማገባደጃ ምዕራፍ ለማሸጋገር ተችሏል።

በተመሳሳይ በእነዚህ ዓመታት ግድቡን አስመልክቶ የተለያዩ ፍላጎቶች እና ስሜቶች በስፋት ሲንፀባረቁ የከረሙ ቢሆንም፤ በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ በመርህ ላይ በተመሰረተ ድርድር ግልፅነትን ለመፍጠር እና ከስምምነት ለመድረስ አያሌ ጥረቶች ተደርገዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የመሰረተ ድንጋይ ከተጣለበት ቀን አንስቶ አሁን ለደረሰበት ደረጃ በሃገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖረው ህዝባችን ያበረከተው የፋይናንስ እና የሞራል ድጋፍ ታሪክ መቼም አይዘነጋውም። እንዲሁም በታችኛው ተፋሰስ ሃገሮች የግድቡን ግንባታ ተከትሎ የሚደመጡ ፍላጎቶች በድርድር እልባት እንዲያገኙ ፍትህ እና እውነትን በማንገብ በሀገር ቤትና በዓለም አደባባይ ድምፃችሁን በማሰማት ለሃገር ሉዓላዊነት ጥብቅና የቆማችሁ ወገኖቻችን ውለታችሁ በትውልድ መዝገብ በደማቁ ተጽፎ እስከወዲያኛው ይዘልቃል።

ባሳለፍናቸው ዓመታት በጠንካራ የሃገር ፍቅር ስሜት የታየው ህዝባዊ ተሳትፎ እና ንቅናቄ ለቀሪ የፕሮጀክቱ ስራ ስኬታማ አፈፃፀም ድጋፋችሁ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ሁላችንም እንደምንገነዘበው ለግድባችን ስኬትና ለሀገራችን ሉዓላዊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብረን የምንቀሳቀስበት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡

ሀገራችን በሁለት አቅጣጫ ፈተናዎች እየገጠሟት ነው፡፡ በአንድ በኩል የከፋ የሉዓላዊነት ጥቃት በመፈፀም ሃገራችንን ለአደጋ ተጋላጭ ከማድረግ ጀምሮ ዜጎችን በማንነታቸው መጨፍጨፍ፣ ማፈናቀል ተረጋግተው በሰላም እንዳይኖሩ በማድረግ፣ ከውጭ እየመጣ ያለውን ጫና በአንድ ልብ ሆነው እንዳይመክቱ እየተደረገ ያለ እኩይ እንቅስቃሴ ነው፡፡

በሌላ በኩል በውጭ ያሉ ሀይሎች የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የኢትዮጵያን የእውነት መንገድና የፍትህ ጥያቄ በማዛባት ያለ የሌለ ርብርብ ከማድረጋቸውም በላይ የውስጥ ብጥብጦችን ዋነኛ የውጊያ አውድ አድርገው በስፋት እየተቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት የድሃ ሞት እና ጭፍጨፋ እንዲሁም ያልተረጋጋች ሃገር መፍጠር የእርካታ ምንጫቸውና መኖሪያቸው ያደረጉ ሀይሎችን ያለምህረት የመታገል እንዲሁም በየደረጃው ኃላፊነታቸውን የማይወጡ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ሃገራችን ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ፍትሃዊ ተጠቃሚነቷን አስጠብቃ የምትዘልቅ እና በታችኛው ተፋሰስ ሃገሮች ዘንድ የሚንፀባረቁ ፍላጎቶችን በሰላም እና በድርድር የመፍታት አቋም እንደወትሮው ፀንቶ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ሃገራችን በራሷ አቅም፣ በራሷ ሉዓላዊ ግዛት፣ በራሷ ሃብት የተፈጥሮ ፀጋዋን ለህዝብ ጥቅም እንዲውል ማድረግ፣ የሌሎችንም ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ የምታደርገውን የፍትሃዊነት እንቅስቃሴ በዘለለ ያልተገባ ጫና መፍጠር እና ለዘመናት የነበረው ኢፍትሃዊ ስርት እንዲቀጥል ማድረግ ተቀባይነት የለውም፡፡

ስለሆነም ከመነሻ ጀምሮ ገንዘባችሁን፣ ጊዜያችሁን፣ ጉልበታችሁን፣ ሃሳባችሁን እና ድምፃችሁን በመስጠት ፕሮጀክቱ ወደ ማገባደጃው ምዕራፍ እንዲሸጋገር ድጋፍ ላደረጋችሁ በሃገር ቤት እና በውጭ ዓለም ለምትኖሩ ወገኖቻችን በሙሉ ያለንን ታላቅ አክብሮት እና ምስጋና በብሄራዊ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ም/ቤት እና በራሴ ስም እየገለፅኩ፤ ሁሉንም ጫናዎች በመቋቋም የምናስበው ዓላማ እንዲሳካ፤ ውስጣዊ አንደነታችን የድሎቻችን ሁሉ ምንጭ ስለሆነ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡


Exit mobile version