Site icon ETHIO12.COM

ሀሰተኛ ዶላር ሲያዘዋዉሩ የተደረሰባቸው አራት ግለሰቦች እያንዳንዳቸዉ በ10 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጡ!

አክሊሉ አሞሼ፣አጥናፉ ስላቶ፣ፀጋዬ ሀ/ማርያምና ደስታ ህዝቅኤል የተባሉ አራት ግለሰቦች ሀሰተኛ የሆነ የአሜሪካ ዶላር ሲያዘዋውሩ በክትትል የተደረሰባቸዉና የተያዙ በመሆኑ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32/1/ሀ/ እና 359ን መሰረት አድርጎ ክስ መስርቶባቸዉ ቆይቷል፡፡

ተከሳሾቹ ሀሰተኛ የሆኑ የገንዘብ ኖቶችን እንዲዘዋወሩ ለማድረግ በማሰብ በቀን 10/06/2013 ዓ.ም በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ክልል ልዩ ቦታዉ ኤክስትሪም ሆቴል ተብሎ ከሚጠራዉ አካባቢ 1ኛና 2ተኛ ተከሳሾች ሀሰተኛ ዶላር የሚገዛ ሰው በማፈላለግና ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሲጠባበቁ 3ተኛ እና 4ተኛ ተከሳሾች በበኩላቸዉ ዶላሩን በመያዝና ቦታው ላይ ይገኛሉ፡፡

ቀጥሎም 3ተኛ ተከሳሽ 45 ባለ 100 ሀሰተኛ የአሜሪካ ዶላር ለ2ተኛ ተከሳሽ ሲያቀብል 4ተኛ ተከሳሽ ደግሞ ዶላሩን ይገዛል ለተባለዉ ግለሰብ ሊያቀብል ሲል በክትትል የተያዙ በመሆኑ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ሀሰተኛ ገንዘብ ይዞ መገኘት ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ከሳሽ ዐቃቤ ህግም የሰዉ፣የሰነድና የኤግዚቪት የማስረጃ ዝርዝሮቹን አጠናቅሮ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበዉ መሰረት የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 11ኛ የወንጀል ችሎት በቀን 20/07/2013 ዓ.ም ባስቻለዉ ችሎት ተከሳሾች ጥፋተኛ ናቸዉ ሲል እያንዳንዳቸዉ በ10 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የልደታ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ጌታቸዉ ሞረዳ ህብረተሰቡ ከነዚህና መሰል ወንጀሎች ሰለባ እንዳይሆን ከብላክ ማርኬት በመጠንቀቅ የሚያደርገዉን የገንዘብ ዝውውርና የዉጭ ምንዛሬ ህጋዊ በሆነ መንገድ በባንኮች በመጠቀም በሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶች ከመታለል ራሱን መጠበቅ እንደሚገባው መልእክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡

Via federal attorney general

Exit mobile version