Site icon ETHIO12.COM

`”የዲሞክራሲ ኤቀንቃኝ ነኝ” ባዩ ህወሃትና በለውጡ ሂደት የተመዘገቡ አንኳር ውጤቶች

በለውጡ ሂደት የተመዘገቡ አንኳር ውጤቶች

በዴሞክራሲ ስም ምሎና ተገዝቶ ወደ ስልጣን የወጣው ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ “አብዮታዊ ዴሞክራሲና ልማታዊ ዴሞክራሲ” በሚል ርእዮት ስም ለ27 ዓመታት አገሪቷንና ህዝቧን እንዳሻው ሲያደርግ ቆይቷል።

“አቀንቃኝ ነኝ” ባዩ ህወሃት ስልጣን በተቆናጠጠባቸው ዓመታት ውስጥ በስውርና በግልፅ በርካቶችን በሃሰት እየፈረጀ በመግደል፣ በማሰርና በማሰቃየት ብዙ በደል ፈፅጽሟል።

ግፉ እየበረታ ሲሄድ በህዝብ ዘንድ የሚገጥሙትን ውጫዊ ችግሮች በማፈንና በጉልበት በመደፍጠጥ፤ ውስጣዊውን ደግሞ ግምገማ፣ ተሃድሶና ጥልቅ ተሃድሶ በሚሉ ‘በእሳት ማብረድ’ አካሄዶች ለመሻገር ሞክሯል።

ነገር ግን እነዚህ አካሄዶች ጠብ የሚል ለውጥ ማምጣት ተሳናቸው፤ ህዝቡም በመንግስት ተስፋ ቆረጠ።
በተለይ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሶስት ዓመታት በሀገሪቱ አብዛኛው አከባቢዎች ህዝባዊ እምቢተኝነት እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋ መጣ።

መንግስት “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ችግሩን በለመደው የአፈና አካሄድ እፈታዋለሁ” ብሎ ቢሞክርም የሚቻል ሆኖ አልተገኘም።

በኢህአዴግ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልጉ አካለት ውጭ ካለው ህዝባዊ እምቢተኝነት ጋር ተደምሮ በፈጠሩት ጫናም ኢህአዴግ እራሱን እንዲፈትሽ አስገደዱት።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከታህሳስ 4 እስከ 20 ቀን 2010 ዓ.ም የጥልቅ ተሃድሶና የሀገራችን የህልውና ስጋት በሚል ርእስ ባካሄደው ስብሰባም የሀገሪቱ ህልውና ስጋት ያላቸውን ነጥቦች በአራቱም የኢህአዴግ ድርጅት ሊቃነ መናብርት አማካኝነት አስቀመጠ።

የውስጠ ድርጅት የዴሞክራሲ ችግር፣ ሙስናና ብልሹ አሰራር፣ የፌደራል ስርዓት ተግባራዊ የአተረጓጎም ጉድለት፣ የድርጅትና የመንግስት ሚና መደበላለቅ፣ የህግ የበላይነትና የህግ ልዕልና አለማስከበር፣ የህዝቡን አንገብጋቢ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አለመፍታት የሚሉት ሃሳቦች ተጠቃሾች ናቸው።

በዚህ አልበቃ ብሎ በወርሃ የካቲት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የመፍትሄው አካል ለመሆን በሚል ምክንያት ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ይፋ አደረጉ።

ተመልሶ ወደ ስብሰባ የገባው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም ዶክተር አብይ አህመድን የድርጀቱ ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ።

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የተሰበሰበው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ዶክተር አብይ አህመድን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ በመሾም ቃለ መሃላ ፈፀሙ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በህዝብ እንደራሴዎች ፊት ለኢትዮያ ያለሙትን ሃሳብ ይፋ አደረጉ።

በንግግራቸውም በኢህአዴግ ሹማምንቶች እምብዛም ያልተለመደውን ኢትዮጵያዊ ሀገራዊ ስሜትን በማጉላት በበርካቶች ልብ ሃሴትና ተስፋን ዘሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የለውጥ እሳቤን ይዘው ሀገር መምራት ከጀመሩ እነሆ ሶስት ዓመታትን አስቆጠሩ። ኢትዮጵያም በእነዚህ ዓመታት በአዲስ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጎዳናዎች አቅንታለች፤ እያቀናችም ትገኛለች።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በኢትዮጵያ የነበሩ ቀደምት ፖለቲካዊ ስብራቶችን ለማስተካከል በርካታ ለውጦች መከናወናቸው የአደባበይ ምስጢር ነው።

በውጭ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል፤ የምርጫና የሽብር አዋጁን ጨምሮ በርካታ የህግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፤ በርካታ ፖለቲከኞች ከእስር ተለቀዋል። ነገር ግን ሂደቱ አልጋ በአልጋ አልነበረም።
ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ደግፈው ለወጡት ሰልፈኞች ንግግር ካደረጉ ጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ከተደረገባቸው የግድያ ሙከራ ጀምሮ ባለፉት ሶስት ዓመታት ሀገራዊ ለውጡ እንዳይሳካ ብሎም ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ ብዙ ሴራዎች ተሸርበዋል።

በተለይ ለውጡን በመቃወም ወደ መቀሌ የሸሸው ‘ህወሃት’ በስልጣን ላይ በነበረባቸው ጊዜያት የዘረጋቸውን መዋቅሮች በመጠቀም የንጹሃን ሞትን ጨምሮ ከፍተኛ ህዝባዊ መፈናቀሎች የተከሰቱባቸውን ግጭቶች ከኋላ ሆኖ ሲያስተባብር ቆይቷል።

የህወሃት ጎምቱ ባለስልጣናት በተለይ የኢህአዴግ ፓርቲ ውህደት እውን መሆኑን ተከትሎ የፌደራሊስት ኃይሎች ሲሉ ካዋቀሯቸው ጉዳይ አስፈጻሚዎቻው ጋር በመሆን ፖለቲካዊ ለውጡን ለመቀልበስ ከፍተኛ ፈተና ሆነው ሌት ተቀን ሰርተዋል።

እለት እለት የሚፈጠሩ ሴራዎች የለውጡ ጎታች ፈተናዎች ሆነውም ቆይተዋል።

ይህ ቡድን ኢትዮጵያን ለመግዛት እንዲመቸው የፈጠረውን አደረጃጀት ተጠቅሞ በተልዕኮ ሲያከናውን የነበረው ኢትዮጵያን የማተራመስ ሴራ አልበቃ ሲለው፤ ምናልባትም በዘመናዊው የዓለም ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የሀገር ክህደት ተግባር ፈጸመ።

“እከሌ ከመጣ እንቀብረዋለን…..” በሚል በወታደራዊ ትርኢቶች የታጀበ የእብሪት ፉከራ ላይ የቆየው ቡድን፤ ከ20 ዓመታት በላይ በትግራይ ክልል የቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ አገርን ከጠላት ሲጠብቅ በነበረውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ጥቃት ፈጸመ፤ ከፍተኛ ዝርፊያም አከናወነ።

ጥቃቱ የተፈጸመበት አግባብ አረመኔያዊና አስነዋሪ ነበር፤ ይህም ኢትዮያዊያን በአንድ ልብ በጋራ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን እንዲቆሙ አድርጓል።

መንግስት በወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃም በ15 ቀናት ውስጥ ህገ-ወጥ ቡድኑን መደምሰስ ችሏል፤ በየዋሻው የተደበቁትንም በማደን ለህግ የማቅረብ ስራ እየተከናወነ ነው።

ነገር ግን የህገወጥ ቡድኑ እርዝራዦች ከደሃ ኢትዮያውያን ዘርፈው በውጭ ያሸሹትን ሃብት በመጠቀም በውጭ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመፍጠር፤ በውስጥ ደግሞ በጉዳይ አስፈጻሚዎችና ቅጥረኞቻቸው አመካኝነት የአልሞት ባይ ተጋዳይ የትርምስ ሙከራውን በተለያዩ አካባቢዎች እያከናወኑ ይገኛሉ።

በፖለቲካው መስክ የሚነሳው ሌላው አንኳር ጉዳይ 6ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ነው።

ምርጫው ጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለት በወርሃ ግንቦት መጨረሻ የሚካሄድ ሲሆን፤ በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎችም ከወዲሁ ቅስቀሳቸውን ጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ አዲስ ወግ በተሰኘው የውይይት መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “መንግስት የዘንድሮውን ምርጫ ከዚህ ቀደም ከተደረጉት የይስሙላ ምርጫዎች በተለየ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነጻ ምርጫ ለማከናወን ቁርጠኛ ነው” ብለዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍም ባለፉት ሶስት ዓመታት በተለይ በተፈጥሮ ሃብትና ታሪክ የምትታወቀውን ኢትዮጵያ በቱሪዝም መስክ የላቀ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ተከናውነዋል።

የአንድነት ፓርክ፣ ሸገር ፓርክና እንጦጦ ፓርክ ደግሞ ለዚህ ህያው ምስክሮች ናቸው።

ፓርኮቹ ከግንባታ ሂደት ጀምሮ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የስራ እድል ፈጥረዋል፤ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ እናቶች በእንጦጦ ፓርክ የስራ እድል አግኝተዋል።

ከሁለት አስርታት በላይ አገልግሎት ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ በመቀየርም ተጨማሪ 6 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች ወደ ባንክ ስርዓት እንዲገቡ ተደርጓል።

የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብም ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተናግረዋል።

“በገበታ ለሀገር” አማካኝነት ኮይሻ፣ ወንጪና ጎርጎራን የቱሪዝም መዳረሻ የሚያደርግ ፕሮጀክት ግንባታ ተጀምሯል።
የፕሮጀክቶቹ እውን መሆን ደግሞ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የቱሪዝም ተደራሽ ሀገሮች ተርታ በማሰለፍ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያም ከወዲሁ ከኮሮናቫይረስ በኋላ መጎብኘት ያለባት ሀገር በሚል ስሟ በዓለምአቀፍ ተቋማት እየተጠቀሰ ይገኛል።

በኢኮኖሚው መስክ የሚጠቀሰው ሌላኛው ጉዳይ የመሰረተ ልማት ግንባታ ነው።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ከፍተኛውን በጀት በመመደብ ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክቶችን እያከናወነች ትገኛለች።
ለአብነትም በ2012 ዓ.ም ብቻ ለመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ከ49 ቢሊዮን ብር በላይ መመደቡ ይታወሳል።

እነዚህ መንገዶች ሲጠናቀቁ የሀገር ውስጥ የንግድ ልውውጡን በማሳለጥ ለምጣኔ ሃብት እድገትና የስራ እድል ፈጠራ ጉልህ ፋይዳ ይዘው እንደሚመጡ ይጠበቃል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ባሳለፍነው ዓመት ነሃሴ ወር አጋማሽ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት የተከናወነ ሲሆን፤ በዘንድሮው ክረምትም ሁለተኛውን ዙር ውሃ ሙሌት ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

ባለፉት ሶስት አመታት ትኩረት ከተሰጠው የማህበራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ ደግሞ ትምህርት ነው።
በእነዚህ ዓመታት የቀዳማዊ እመቤት ጽህፈት ቤት በተለያዩ አካባቢዎች እገነባቸዋለሁ ሲል ያቀዳቸውን ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ገንብቶ አስረክቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “ከመደመር” መጽሃፍ ሽያጭ ከተገኘው ገንዝብ ውስጥ 110 ሚሊዮን ብር ለትምህርት ቤት ግንባታ ስራ እንዲውል ለቀዳማዊ እመቤት ጽህፈት ቤት መለገሳቸው ይታወሳል።

በቅርቡ የተመረቀው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር ጉዞ መጽሃፍ ሽያጭም ለዚሁ ስራ የሚውል ነው።
በጤናው ዘርፍም ዓለምን ያስጨነቀው የኮሮናቫይረስ ስርጭት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ሰብዓዊ ቀውስ እንዳያስከትል በርካታ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።

በዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያ ተሞክሮዋን ለዓለም የጤና ድርጅት እንድታቀርብ መደረጉ ይታወሳል።
የቫይረሱን ክትባት ፈጥኖ በመጀመር ረገድም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተጠቃሽ ሀገር ነች። እነዚህና ሌሎችም ባለፉት ሶሰት ዓመታት በኢትዮጵያ እውን የሆኑ አንኳር የለውጥ ስራዎች ናቸው።

በዚህ ሂደት ለውጡን የሚገዳደሩ የተለያዩ ፈተናዎች እየተስተዋሉም ይገኛሉ። በተለያዩ አከባቢዎች በሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት የሚከሰቱ የዜጎች ሞትና መፈናቀል በዋነኝነት ለውጡ ሊሻገረው የሚገባው ፈተና ነው። ሆኖም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በፅናት በመታገል በድል አድራጊነት እንደሚወጣቸው ይታመናል።
ኢዜአ

Exit mobile version