የህወሃት ግዙፍ ስህተቶች

ህወሃት የአገራችንን ጉዞ ወደኋላ የጎተቱ ግዙፍ ስህተቶች ፈጽሟል ብዬ አምናለሁ፡፡ በእኔ እምነት ከእነዚህ ስህተቶች የምንማረው ነገር አይጠፋም፤ ስለስህተቶቹ አፍታትተን ብንናገር ደግሞ ለምንመኘው ፍትሕና ዲሞክራሲ የሰፈነበት ሥርዓት ግንባታ የሚጠቅም የተወሰነ ግብዓት ልናገኝበት እንችላለን፡፡

በቅድሚያ ግን ሁለት ነጥቦችን እንድትይዙልኝ እፈልጋለሁ፡፡

  1. በፌስቡክ መሳተፍ ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ በእነዚህ ነጥቦች ላይ ፈራ ተባ እያልኩ ስጽፍ ነበር፡፡ ቀደም ያሉ ጽሑፎቼን ላያችሁ ሰዎች አሰልቺ ከሆነባችሁ አስቀድሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ምናልባት አሁን ስጋቴ ስለቀነሰ በበለጠ ግልጽነት አቋሜን አንፀባርቄ ይሆናልና አንብባችሁ አስተያየት ብትሰጡበት ደስ ይለኛል፡፡
  2. የህወሃት ስህተቶች ያልኳቸውን የማነሳው እነዚህን ስህተቶች እንዳንደግማቸው ለማሳሰብ እንጅ ክስ ለማቅረብ አይደለም፡፡

ስህተት 1:- “የደርግ ሠራዊት”

ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ከመዓዛ ብሩ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ በደርግ ዘመን ስለተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ሲያብራሩ “ጦርነቱ የተካሄደው ሕዝባዊ ግንባር ሃርነት ኤርትራና ህወሃት በአንድ ወገን፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት በሌላ ወገን ሆነው ነው፤ ‘የደርግ ሠራዊት’ የሚለውን አጠራር አልቀበለውም” (ቃል በቃል አይደለም) ብለው ነበር፡፡ የአገራችን ተቋማት ቀጣይነት የሚያሳስበው ሰው እንዲህ አይነት አቋም ማራመዱ ተፈጥሯዊ ነው፡፡

ህወሃት የተከተለው መንገድ ግን ከዚህ ፈጽሞ የተቃረነ ነበር፡፡ የእርስ በርስ ጦርነት ተካሂዶ የመንግሥት ለውጥ በተከናወነባቸው የተለያዩ አገሮች ካየነው አካሄድ ፍጹም በተለየ ሁኔታ በ1983 የተሸነፈውን ሠራዊት በጅምላ እንደጠላት ነበር የፈረጀው፡፡ የተለመደውን አሠራር ስንመለከት ጦርነቱ በመሸናነፍም ሆነ በድርድር ሲቋጭ ብሔራዊው የመከላከያ ኃይል ከመደበኛው ሠራዊትና ከአማጺው ኃይል ተቀይጦ ይደራጃል፡፡

ከሠራዊቱ አባላትና መሪዎች መካከል ወንጀል የፈጸሙት ተጨባጭ ማስረጃን መሠረት በማድረግ ተሰናብተው ወይም ተቀጥተው ሌሎቹ ግን በሥራቸው እንዲቀጥሉ ሊደረግ ይገባ ነበር፡፡ ከዚህ ይልቅ ህወሃት የመረጠው ሁሉንም መበተንን ነበር፡፡ (እዚህ ላይ ኦነግ የተለየ አቋም ሲያራምድ እንደነበር ሰምተናል፡፡ ጦሩ እንዳለ መበተኑን ተቃውሞ እንደነበረና ህወሃት በዚህ እንደማይስማማ ሲረዳ ከቀድሞው ሠራዊት አባላት መካከል የተወሰኑትን መልምሎ እንደነበር ተጽፎ አንብበናል፡፡)
የኢትዮጵያ ሠራዊት በህወሃት/ኢሕአዴግ ጦር ከተተካ በኋላ ለታይታ ብዙ ድራማ መሠራቱን እናስታውሳለን፡፡ ለምሳሌ የሠራዊቱ አመራር አባላት የፓርቲ አባልነት ካርዳቸውን የመለሱበት መድረክ ተዘጋጅቶ አይተናል፡፡ በተጨባጭ ግን የሠራዊቱ አመራር የፓርቲ መስመሩን ይዞ ነው የቀጠለው፡፡ አቶ በረከትም የሁለት ምርጫዎች ወግ በተባለው መጽሐፋቸው ሠራዊቱ የኢሕአዴግ መንትያ እንደሆነ ደረታቸውን ነፍተው ነግረውናል፡፡
…..
ሠራዊቱን የመበተኑ ውሳኔ መዘዙ ብዙ ነበር፡፡ ጥቂቶቹን እናውሳ

  1. በኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሠረተው ሠራዊት ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ሁኔታ በብሔረሰብ በተደራጀ ጦር ተተካ፡፡ ይህ ከባድ የቅቡልነት ክፍተት ፈጠረ፡፡ ሠራዊቱ የህወሃት/ኢሕአዴግ ጦር እንጅ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ነው ብሎ ለመቀበል የሚከብድ ሆነ፡፡
  2. በክህሎት በኩል ደግሞ በመደበኛ ውጊያ ልምድ ያካበተው ኃይል በሽምቅ ውጊያ ውስጥ ባደገ ሠራዊት መተካቱ ክፍተት መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ከኤርትራ ጋር በተደረገው ጦርነት ኢሕአዴግ የቀድሞውን ጦር አባላት እንደገና ለማሰለፍ የተገደደው በዚህ ምክንያት እንደሆነ እገምታለሁ፡፡
  3. የሠራዊቱ አመራር ተጠቅልሎ በአንድ ብሔረሰብ ተወላጆች እጅ ገባ፡፡ ዋናው መስፈርት ብቃት መሆኑ ቀርቶ ፖለቲካዊ ታማኝነት ሆነ፡፡ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የበታች መኮንኖች ከሌሎች ብሔረሰቦች የመጡ የበላይ መኮንኖችን የሚያንጓጥጡበት ሁኔም እንደነበር ታዝበናል፡፡
  4. ሕገመንግሥቱን በተፃረረ ሁኔታ የጦሩ አባላት የህወሃት/ኢሕአዴግ ጋሻጃግሬዎች እንዲሆኑ ተወስኖባቸው ነበር፡፡ በየጊዜው በተካሄዱ ግምገማዎች ”የቅንጅት ወይም የኦነግ አመለካከት ነው ያለህ“ እየተባሉ የተንገላቱ በርካቶች ነበሩ፡፡ በተቋም ግንባታ መነፅር ስናየው ከተሠሩት ስህተቶች ዋነኛው ይህ ይመስለኛል፡፡ መከላከያ የአገር ሰላምና ደንበር አስከባሪ እንጅ የአንድ ፓርቲ ስልጣን አስጠባቂ ሆኖ መደራጀት አልነበረበትም፡፡
  5. በሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመው የክህደት ተግባር ራሱ የዚህ አደገኛ ፖሊሲ ውጤት ነው፡፡ ራሳቸውን የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ሳይሆን የህወሃት ዓላማ አስፈጻሚ አድርገው የቆጠሩ የሠራዊቱ አባላት ናቸው ይህን ድርጊት የፈጸሙት፡፡ አብረዋቸው በአንድ የቀበሮ ጉድጓድ ከ20 ዓመት በላይ በቆዩ ጓዶቻቸው ላይ አፈሙዝ ለማዞር ያስቻላቸው ይኸው መከላከያን በተሳሳተ መሠረት ላይ ያቆመው ፖሊሲ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
  6. ህወሃት ስልጣን በያዘ በሁለተኛው ይሁን በሦስተኛው ዓመት የብሔረሰብ ተዋፅዖን ለማመጣጠን ተብሎ በሺህ የሚቆጠሩ የትግራይ ልጆች ተቀንሰዋል፡፡ በዚህ ሂደት ሁለት ጥፋቶች እንደተፈጸሙ እናስታውሳለን፡፡ የመጀመሪያው የታጋዮቹን ሞራል በሚነካ መልክ መሰናበታቸው ሲሆን (አቶ መለስ “ይህን ግፋፎ ጥረግልኝ” “ጉሓፍ ጽረግለይ” እንዳሉ ይነገራል) ሁለተኛው ደግሞ በወልቃይት አካባቢ የሕዝብ ቁጥርን ለመለወጥ ሲባል ያለበቂ ዝግጅት እንዲሰፍሩ ሲደረግ በርካታ ዜጎች ለሞትና ስቃይ መዳረጋቸው ነበር፡፡
  7. ህወሃት በመከላከያውና በደህንነት ተቋሙ ውስጥ የበላይነቱን ይዞ ለበርካታ ዓመታት መቆየቱ “ማን ይነቀንቀኛል” የሚል እብሪት ውስጥ አስገብቶ ሌሎቹን ስህተቶቹን እንዳያይ ህሊናውን ሳይጋርደው አልቀረም፡፡ በሕዝብ ግፊትና በኢሕአዴግ የውስጥ ትግል የበላይነቱን ሲያጣ አዲሱን እውነታ ለመቀበል ዳገት የሆነበትም በዚህ ምክንያት ይመስለኛል፡፡ በሁሉም ጉዳዮች ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ሰጪ ከነበረበት ቦታ ወርዶ በእኩልነት ለመታገል እንደከበደው ይታያል፡፡
See also  አብን አስር አመራሮቹን አገደ-ክርስቲያን ታደለ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው

ስናጠቃልለው…

ህወሃት መከላከያውን በሞኖፖሊ ይዞ መቆየቱ ከባድ ጉዳት አድርሷል፡፡ ይህን ጉዳት ለመጠገን የተጀመረው እንቅስቃሴ መልካም ቢሆንም ብዙ ይቀረዋል፡፡ ምናልባትም 20 ዓመታት ያህል አብሮን የሚቆይ ችግር ይመስለኛል፡፡

መልካም ቀን. By Endalamaw Aberra FB

ይቀጥላል

Leave a Reply