Site icon ETHIO12.COM

“አብቁተ የአንድነታችን፣ የመተባበራችን እና የስኬታችን መገለጫ ነው” አቶ አገኘሁ ተሻገር

የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ወደ ባንክ እንዲሸጋገር ከባለአክስዮኖች ጋር በባሕር ዳር ውይይት እያደረገ ነው፡፡ በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር አብቁተ አሁን ያስመዘገበው ውጤት ከስኬቶች ሁሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አብቁተ “የአንድነታችን፣ የመተባበራችን እና የስኬታችን መገለጫ ነው” ብለዋል አቶ አገኘሁ፡፡ የአማራ ክልል ያለውን ተፈጥሮአዊ፣ ታሪካዊ እና ሰብዓዊ እምቅ አቅም የጠቀሱት አቶ አገኘሁ ይህንን እምቅ አቅም በተለያየ መልኩ መጠቀም ባለመቻሉ ሕዝቡ ለዘመናት በድህነት ውስጥ እንዲኖር መገደዱን አንስተዋል፡፡ የአማራ ክልል ሕዝብ በተለይም ደሀው እና አርሶ አደሩ ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋጥበትን እና ዋና የልማት መሳሪያ የሆነውን የፋይናስ አገልግሎት በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ለዘመናት ሳያገኝ መቆየቱን ርእሰ መሥተዳድሩ ጠቅሰዋል፡፡

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ቋሚ ንብረት እና ሀብት ያላቸው የከተማ ነዋሪዎች በባንኮች ሲቆጥቡና ሲበደሩ በርካቶች ደግሞ ገበያቸው አነስተኛ በመሆኑ እና ከከተማ ርቀው በመኖራቸው ምክንያት የብድር ዋስትና ማቅረብ ተስኖአቸው የፋይናንስ አገልግሎት እንደተነፈጋቸውና ለችግር ተዳርገው እንደኖሩም ገልጸዋል፡፡ አብቁተ ለእነዚህ ደሀ እና አምራች በቁጥር ግን ለሚበዙት የኅብረተሰብ ክፍሎች ፍትሐዊ የገንዘብ አገልግሎት በማቅረብ ከድህነት የመውጣት ዓላማ ይዞ የተቋቋመ የመጀመሪያው የማይክሮ ፋይናንስ መሆኑን አቶ አገኘሁ ተናግረዋል፡፡

ሠርተው ከድህነት ለመውጣት ለሚፈልጉ ሰዎች የፋይናንስ አገልግሎት የሚያቀርቡ ሁሉ አነስተኛ የገንዘብ እና የብድር ተቋማት በአዋጅ ቁጥር 140/1988 እና በአዋጅ ቁጥር 626/2001 በተደነገገው ሕግ መሠረት በብሔራዊ ባንክ ተመዝግበው እና ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው እንዲቋቋሙ ከተደረጉት የማይክሮ ፋይናስ ተቋማት መካከል አንዱ አብቁተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት አዋጁን መሰረት አድርገው ከብሔራዊ ባንክ በወጡ አቅጣጫዎች እና መመሪያዎች አገልግሎት እንዲሠጡ መደረጉ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉንም አንስተዋል፡፡

አብቁተ በአማራ ከክልል ውስጥ ሠፊ የብድር ሽፋን በመስጠት ረገድ ቀዳሚ መሆኑን ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል፡፡ ብዙዎችን ከድህነት አውጥቷል፤ ብዙዎችን የብልጽግና ጎዞ አረጋግጧል ብለዋል፡፡ አብቁተ በከተማ እና በገጠር ለሚገኙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቁጠባ፣ የብድር፣ የሐዋላ፣ የገንዘብ ማስተዳደር እና የአነስተኛ የገንዘብ ኢንሹራንስ በመስጠት ላይ ያለ የክልሉ አንጋፋ የፋይናስ ተቋም መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

አብቁተ በሁሉም የአማራ ክልል ወረዳዎች 471 ቅርንጫፎች እና 1 ሺህ 127 ሳተላይት ጽሕፈት ቤቶችን በመክፈት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ርእሰ መሥተዳድሩ እንዳሉት አብቁተ ማኅበራዊ ተሳትፎው እና ተቀባይነቱም አድጓል፤ ዘመናዊ የቁጠባ ባሕል እንዲያድግ አድርጓል፤ በቁጠባ የሰበሰበውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ በክልሉ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲውል አድርጓል፡፡ “አብቁተ ለመላው ኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች የሥራ ምሳሌ ነው፤ የታማኝነት ምሳሌ ነው” ብለዋል፡፡ ተቋሙ ከክልሉ ውጭ አገልግሎቱን እንዲያሰፋ ያላሰለሰ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ተቋሙ ለልማቱ ጠንካራ መሳሪያ ሆኖ እንዲያገለግል፣ በቁጠባ አቅሙ እንዲጎለብት እና የሚያሰራጨው የብድር ኢንቨስትመንት ጥራት እና ወቅቱን የጠበቀ እንዲሆን የክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንደማይለየው አቶ አገኘሁ አስታውቀዋል፡፡

የኅብረተሰቡ ባሕል ያልሆነው እና ቀስ በቀስ እየተስተዋለ የመጣውን ብድር ያለመመለስ አዝማሚያ በቁርጠኝነት በመታገል እንደሚስተካከልም ተናግረዋል፡፡ አቶ አገኘሁ የፋይናንስ ሕጎች እና አሠራሮች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ፣ ተቀባይነት እንዲኖራቸው እና በሁሉም ኅብረተሰብ ዘንድ ግንዛቤው እንዲያድግ መንግሥት እንደሚሠራም አስታውቀዋል፡፡ በአንድነት መሥራት ውጤቱ መልካም መሆኑን እና አንድ መሆን እንዲገባም መልእክት አስተላፈቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- የማነብርሃን ጌታቸው

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 25/2013 ዓ.ም (አሚኮ)


Exit mobile version