Site icon ETHIO12.COM

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና አመሰራረታቸው

1. መግቢያዜጎች የተለያዩ መብቶችና ነፃነቶች ያሏቸው ሲሆን ከእነዚህ መብቶች መካከል ተደራጅተው መብትና ጥቅማቸውን ማስጠበቅ አንዱ ነው፡፡ ዜጎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና ባህላዊ መብታቸውን በመደራጀት መከወን ይችላሉ፡፡ በሀገራችን ህገ መንግስት አንቀጽ 31 ላይ እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማህበር የመደራጀት መብት አለው፡፡ ነገር ግን ለህገ ወጥ ዓላማ መደራጀት ወይም ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በህገወጥ መንገድ ለማፍረስ የተመሰረቱ ወይም የተጠቀሱትን ተግባራት የሚያራምዱ ድርጅቶች የተከለከሉ ይሆናሉ፡፡ እንዲሁም በመደራጀት መብት ምክንያት ሌላ ሶስተኛ ወገንን ለመጠበቅ የወጡ ህጎችን ወይም የሌላ ሰውን መብት በሚጥስ ሁኔታ መንቀሳቀስ የማይችልና የተከለከለ ነው፡፡

2. ሲቪል ማህበሰረብ ድርጅቶች ምንነት፣ አይነት እና የህግ ማዕቀፍየመደራጀት መብት ከሚገለጽባቸው መንገዶች መካከል ዜጎች በሙያና በብዙሃን ማህበራት መደራጀት አንዱ ነው፡፡ በሀገራችን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላቸው ሲሆን ለትርፍ ያልተቋቋሙ ቦጎ አድራጎት ድረጅቶች ከጥንት ጀምሮ በማህበረሰቡ ዘንድ የዳበረ የእርስ በእርስ መረዳጃ ባህላዊ የሆኑ እንደ ደቦ የመሳሰሉ አደረጃጀቶች እንዲሁም እንደ እቁብና እድር ያሉ አደረጃጀቶች ማህበረሰቡ እርስ በእርሱ የሚተጋገዝባቸውና ገንዘብ መቆጠቢያና መበደሪያ መንገዶች ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ የእርስ በእርስ መረዳጃ ማህበራት ውጭ በኢትዮጵያ መጀመሪያ የተቋቋሙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና የስዊዲሽ ሴቭ ዘ ቺልድረን ሲሆኑ በኋላም እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1990 መጀመሪያ ጀምሮ በርካታ የሲቪል ማህበራት ተመስርተዋል፡፡

በህገ መንግስቱና ሌሎች ህጎች ለመብቱ የተሰጠው ጥበቃ እንደተጠበቀ ሆኖ የመደራጀት መብት ከሚገለፅባቸው መንገዶች አንዱ የሆኑትን በሙያና ብዙሃን የሚደራጁ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚገዛ አዋጅ ቁጥር 621/2001 ወጥቶ ሲተገበር ቆይቷል፡፡ ይህ አዋጅ የመደራጀት መብትን ይበልጥ ከማስከበር አንፃር ገደቦች/ውስንነቶች የነበሩበት በመሆኑ አዋጁ ተሻሽሎ አዋጅ 1113/2011 ሆኖ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ በአዋጅ መሰረት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ቢያንስ ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች በፍቃደኝነት የሚመሰረት፣ የመንግስት አካል ያልሆነ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ ከማናቸውም የፖለቲካ ድርጅት ያልወገነ እና ህጋዊ ዓላማን ለማሳካት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ አካል ሲሆን የሞያ ማህበራትን፤ የብዙኃን ማህበራት እና የድርጅቶች ህብረቶችን ይጨምራል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሀገር በቀልና የውጭ ድርጅት በሚል በሁለት የሚከፈሉ ሲሆን ሀገር በቀል ድርጅት በኢትዮጵያ ወይም ከኢትዮጵያ ውጭ ህጋዊ ስራ ለመስራት በኢትዮጵያዊያን፤ በኢትዮጵያ ነዋሪ በሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎች ወይም በሁለቱም የሚመሰረት ድርጅት ሆኖ መስራቾቹ ሁለትና ከዚያ በላይ መሆን አለባቸው፡፡ የውጭ ድርጅት በውጭ ሀገር ህግ መሰረት የተቋቋመና በኢትዮጵያ ውስጥ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡በሌላ በኩል አገር በቀል ድረጅቶች በአምስት አይነት አደረጃጀት የሚቋቋሙ ሲሆን እነዚህም ማህበር፣ ቦርድ መር ድርጅት፣ የዘለቄታ በጎ አድራጎት ድርጅት፣ የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት እና የበጎአድራጎት ድርጅት ናቸው፡፤

3. የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምስረታ የሲቭል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመሰራረት በሚከተሉት መርሆች እንደሚመራ አዋጁ ይደነግጋል፡፡ አነዚህ መርሆችም፤-

• ድርጅቶች ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ሊቋቋሙ መቻላቸው • በድርጅቱ ውስጥ አባል ለመሆን ፍቃደኝነት የግድ ሲሆን ከድርጅቱ በፈለገው ሰአት መውጣት ይቻላል

• አግባብነት ያለውን ህግ መሰረት በማድረግ የአባላት መቀበያ ፎርም ማዘጋጀት • ማንኛውም ሰው መስፈርቱን ካሟላ የድርጅቱ አባል መሆን መብት አለው

• እያንዳንዱ አባል እኩል ድምጽ አለው• ድረጅቶች ለአባላት ትርፍ በማሰብ ሊቋቋሙ ኤችሉም • የድርጅቱ አመሰራረትና ውስጣዊ አሰራር ዴሞክራሳዊ መርሆችን የተከተለ፤ ከአድሎአዊነት የጸዳ፤ ነጻና ገለልተኛ ሊሆን ይገባል፡• ድርጅቱ የሚመራው በመተዳደሪያ ደንቡ ስልጣን በተሰጣቸው አካላት ሙሉ ተሳትፎ በተመረጡሰዎች ነው፤

• ድርጅቱ በመተዳደሪያ ደንቡ ካልሆነ በስተቀር አባላትን ሊቀበልና ሊያሰናብት አይችልም፡፤

3.1. የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምዝገባ እና መስፈርቶችማንኛውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የፌደራል መስሪያ ቤት በሆነው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ መመዝገብ እንዳለበት በህግ ተቀምጧል፡፡ ለሀገር በቀል ድርጅቶች ምዝገባ በድርጅቱ መስራቾች ሰብሳቢ የተፈረመ ማመልከቻ መቅረብ ያለበት ሲሆን ከማመልከቻው ጋር ተያይዘው መቅረብ ያለባቸው ሰነዶች፤-

• የምስረታ ቃለ-ጉባኤ የመስራቾችን ስምና አድራሻ የያዘ፤

• የመስራቾች መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ኮፒ፤

• የድርጅቱ ስም እንዲሁም አርማ፤• የድርጅቱ አርማና ሊሰራ ያሰበበት የስራ ዘርፍ፤

• የስራ ቦታ፤

• በመስራቾች የጸደቀ መተዳደሪያ ደንብ፤

• የድርጅቱ አድራሻ፡፡ በሌላ በኩል በውጭ ሀገር የተመሰረተ ድርጅት በኢትዮጵያ ለመመዝገብ ከላይ የተዘረዘሩትን ጨምሮ የሚከተሉትን ሰነዶች ማሟላት ይኖርበታል፡• ድርጅቱ መቋቋሙን የሚያሳይ ከተቋቋመበት አገር የተሰጠው በአግባቡ የተረጋገጠ ሰነድ፤

• ስልጣን ያለው የድርጅቱ አካል ድርጅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰራ ያሳለፈው በአግባቡ የተረጋገተ ውሳኔ፤

• በአገር ውስጥ ተወካዩ የተሰጠው በአግባቡ የተረጋገጠ የውክልና ስልጣን፤ ከተቋቋመበት ሀገር ስልጣን ባለው አካል የተሰጠ የድጋፍ ደብዳቤ ወይም በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠ የድጋፍ ደብዳቤ፤

• ከሁለት አመት ላላነሰ ጊዜ የሚተገበር የስራ እቅድ ይዞ መቅረብ የግድ ይላል፡፡ከላይ የተዘረዘሩት ቅደመ ሁኔታዎች አሟልቶ ያቀረበ ሀገር በቀል ድርጅት በኤጀንሲው ማመልከቻውን ባቀረበ በ30 ቀን ውስጥ እና የውጭ ድርጅት የምዝገባ ማመልከቻውን ከስራ እቅድ ጋር ባቀረበ በ45 ቀን ውስጥ ኤጀንሲው መዝግቦ የምስክር ወረቀት መስጠት ይኖርበታል፡፡ የምዝገባ ማመልከቻ አስገብቶ በተባለው ቀን ውስጥ የምስክር ወረቀት ያልተሰጠው ድርጅት ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቦርድ በ30 ቀን ውስጥ ቅሬታውን ማቅረብ ይችላል፡፡ ቦርዱ ምዝገባው ያለአግባብ የተከለከለ መሆኑን ከተረዳ ምስክር ወረቀቱ እንዲሰጠው ያደርጋል፡፡

3.2. ምዝገባ ውድቅ የሚሆነበት ሁኔታማንኛውም ሰው በማንኛውም አላማ የመደራጀት መብት ያለው ቢሆንም ህግ በመጣስ መደራጀት ክልክል ነው፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከላይ በተቀመጠው መሰረት ምዝገባ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ሰነዶችን ይዞ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጄንሲ ካቀረቡ በኋላ ኤጀንሲው የቀረበለትን የምዝገባ ጥያቄ ከሚከተሉት ምክንያቶች አንዱ መኖሩን ካረጋገጠ ድርጅቱ ያቀረበውን ምዝገባ ውድቅ ሊያደርግ ይችላል፡-

• የቀረበው ማመልከቻ ከላይ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የማያሟላ ሆኖ ሲገኝና ይህንንም እንዲያስተካክል የአመልካቹ ተወካይ ተጠይቆ ለማስተካከል ካልቻለ፤

• የድርጅቱ ዓላማ ወይም በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የተመለከተው የሥራ ዝርዝር ለሕግ ወይም ለሕዝብ ሞራል ተቃራኒ ከሆነ፤

• ድርጅቱ የሚመዘገብበት ስም ወይም ዓርማ ከሌላ ድርጅት ወይም ከማንኛውም ሌላ ተቋም ስም ጋር የሚመሳሰል ከሆነ ወይም ሕግን ወይም የሕዝብን ሞራል የሚቃረን ከሆነ፤

• ድርጅቱ ለምዝገባ ያቀረበው ሰነድ በሐሰት የተዘጋጀ ወይም የተጭበረበረ ከሆነ ሲሆን ከነዚህ ምክንያቶች ኤጄንሲው ምዝገባ መከልከል እንደማይችል በህጉ ላይ ተቀምጧል፡፡ ምዝገባው ውድቅ የተደረገበት ድርጅት በ30 ቀን ውስጥ የጎደለውን ነገር አሟልቶ እንዲያቀርብ ኤጀንሲው ለድርጅቱ በጽሁፍ ማሳወቅ አለበት፡፡ የጎደለውን ነገር አስተካክሎ እንዲቀርብ በጽሁፍ የተሰጠው ድርጅት በተባለው ቀን ውስጥ ለኤጀንሲው ካላቀረበ ምዝገባው ውድቅ ይሆናል፡፡ ምዝገባው ውድቅ የተደረገበት ድርጅትም ቅሬታ ካለው በ30 ቀን ውስጥ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቦርድ ቅሬታውን ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ቦርዱ ቅሬታው በቀረበለት በ60 ቀናት ውስጥ ቅሬታውን መርምሮ ውሳኔ መስጠት ይኖርበታል፡፡ አንድ ድርጅት በማታለል ወይም በማጭበርበር የምዝገባ የምስክር ወረቀት አግኝቶ ከሆነ ይኸው በኤጀንሲው ሲረጋገጥ ቦርዱ ድርጅቱ እንዲፈርስ ሊወስን የሚችል ሲሆን በተሰጠ ውሳኔ ቅሬታ ያለው ድርጅት የቦርዱ ውሳኔ በደረሰው በ30 ቀናት ውስጥ ይግባኙን በመስራቾቹ አማካኝነት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል።

3.3. የድርጅቶች የምዝገባ ውጤትከላይ የተጠቀሱትን ቅድመ ሁኔታ አሟልቶ የተመሰዘገበ ድርጅት ህጋዊ ሰውነት ይኖረዋል፣ መብትና ግዴታ ይኖረዋል፡፡ በስሙ ውል መግባት፣ ክስ ማቅረብ እና መከሰስ ይችላል፡፡ እንዲሁም ለስራ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ ህጋዊ የስራ መስክ ላይ መሳተፍ ይችላል፡፡


Exit mobile version