Site icon ETHIO12.COM

“ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

አዲስ አበባ በጥናት የተዘረፉ ዜጎች ቁጥር ቀላል አይድለም። ስም መጥቀስ አያስፈልግም እንጂ ያለውን አስረክቦ በባልደረቦቹ ድጋፍ ከእብደት የዳነ ስፖርተኛ ታላቅ ምሳሌ በሆነ ነበር። አንድ በህይወት የሌሉ ታዋቂ አሰልጣኝም ያላቸውን አስረክበዋል። ስራው የሚሰራው በአስተኳሽ ነው። አስተኳሹ ዜጋችን ሲሆን ቁማሩን የሚጫወቱት ” ኢንቪስተር” የተባሉ ናቸው።

ዝርፊያው ሁለት መልክ አለው። አንደኛው ቆርቆሮ ወይም ቡና ወይም በርከት ያለ ንብረት ከመንግስት መጋዘን በድብቅ አውጥተው በርካሽ ለመሸጥ ደላሎች ብር ያላቸውን ያግባባሉ። በሚቀርቧቸው ሰዎች አማካይነት ውስወሳው ካለቀ በሁዋላ እቃው ያለበት የመንግስት መጋዘን ሄደው እንዲያዩት ይደረጋል። ይህ ሲሆን የተወሰኑ ሃላፊዎች በጨዋታው ውስጥ እንዲኖሩበት ይደረጋል።

ሃሰተኛ ደረሰኝ፣ የርክክብ ሰነድና የማውጫ ፈቃድ ይዘጋጅና በመንግስት ቢሮ ውስጥ በገሃድ ሽያጭ ይፈጸማል። ገዢ በርካሽ አገኘሁ ብሎ ህጋዊ ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ የሸመተውን ንብረት ለመጫን መኪና ደርድሮ ይመጣና ንብረቱን ሲጠይቅ ” ፌክ ዶክመንት” እንዳቀረበ ይነገረውና አጭበርባሪ ተብሎ ይታሰራል። እስር ቤት ገብቶ አርፎ መኖር እንዳለበት የኔት ዎርኩ አባላት አስጠንቀቀው፣ ዶክመንቶቹን ተረክበው ይለቁታል። በዚህ ጨዋታ በርካታ ሰዎች ተጨርግደዋል። እነማን ይህንን ሲያደርጉ እንደነበር የሚታወቅ ነው።

ሌላው አንድ አውላላ ሜዳ ላይ ወይም ትልቅ ግቢ ወይም መጋዘን ይከራዩና ለምሳሌ አንዱን ኮንቴነር ቆርቆሮ ይሞሉና ሌሎቹን ባዶ አድርገው ያደረድራሉ። አለያም ሲከፈቱ ብቻ ሙሉ እንዲመስሉ አድርገው ያስቀምጡዋቸዋል። ንብረቱ የመንግስት፣ ለፕሮጀክት የመጣና በድብቅ የሚሸጥ መሆኑንን ለማሳመን ህጋዊ ነገር ግን በስራ ላይ ሊውል የማይችል ሰነድ ይዘጋጃል። መሳሪያ የያዘና ዩኒፎርም ያደረገ ጠባቂ የመደባል። ከዛም የተመረጠውና የፈረደበት ሆዳም በርካሽ ቆርቆሮ፣ ሲሚንቶ፣ ሚስማር፣ የህንጻ መሳሪያዎች … ገዝቶ ትርፍ ሊያጋብስ አዳራሽ ተከራይቶ ያግዛል። ከዛም በየተራ ኮንቴነሮቹን ሲከፍት ባዶ እንደሆኑ ይረዳል። እንዲህ የተመነተፉ ብዙ ናቸው። ይህንንም እነማን በነማን ሽፋን ተሰጥቷቸው ሲፈጽሙት እንደነበር ግልጽ ነው።

ሌላው ” ገንዘብ እናወርዳለን” የሚሉ ናቸው። ዶላር ይዘው ለሚመጡ ሰዎች በድራማ እያምታቱ ይዘርፏቸዋል። ይህንን ጨዋታ የሚጫወቱት የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ሲሆኑ፣ በአብዛኛው የተበሉ ሰዎች ምንም ማድረግ ስለማይችሉ ብቻቸውን እያወሩ እንዲኖሩ ይገደዳሉ። ጉዳዩ ሰፊ ነው። ያልተነከሰ የለም። ጊዜው ደርሶ ወደ አደባባይ ዛሬ ብቅ አለ።

“አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜጎች ኢንቨስተር ነን በሚል ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል እንደሚፈፅሙ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ” ይላላ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ ተጠቅሶ በኢፕድ የተዘገበው ዜና። ምረመራው እንዳረጋገጠው አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜጎች ኢንቨስተር ነን በሚል ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል በመፈፀም በዜጎች ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን አመልክቷል። የኢፕድን ዜና ከታች እንዳለ ያንብቡ።

መረጃው እንደሚያመለክተው በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ አንዳንድ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ሀብትና ንብረት ያላቸውን ኢትዮጵያዊያንን ማንነት በጥናት በመለየትና ቀረቤታ በመፍጠር ከፍተኛ የሆነ የማጭበርበር ወንጀል እየፈፀሙባቸው መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል።እነዚህ የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ሀገራችን ለኢንቨስትመንት የመጡ በማስመሰል፣ አብሯዋቸው የሚሰሩ ኢትዮጵያዊያንን እንደሚፈልጉ በማግባባትና ለስራ ማስኬጃም ከ300 ሚሊየን ዶላር በላይ እንዳላቸው በመግለጽ ኢትዮጵያዊያንን ካገኙ አብሮ ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑ በማስመሰል የሚያጭበረብሩ መሆናቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ አሳውቋል፡፡

እነዚህ አጭበርባሪዎች የኛ ዜጎች አብረዋቸው ቢሰሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በማሳመን እና ከዚህ በተጨማሪም ዶላር የማባዛት ችሎታ እንዳላቸው በመግለፅ በተግባር አባዝቶ ለማሳየት መጀመሪያ የያዙትን ዶላር ሌላ ቦታ በፖስታ በመደበቅና ይባዛበታል ያሉትን ወረቀት ኬሚካል ውስጥ በመንከር ከዚያም የተነከረውን ወረቀት አውጥተው እንዲደርቅ በማድረግ በሌላ ፖስታ ውስጥ ያስቀመጡትን ትክክለኛ ዶላር በእጥፍ እንዳባዙት በማስመሰል ለሰዎቹ ያሳዩና ይበልጥ አመኔታን ለማግኘት ተባዛ ያሉትን ዶላር ባንክ ቤት ይዘው እንዲሄዱና ትክክለኛነቱን አረጋግጠው እንዲመጡ ካደረጉ በኋላ አሁን የተባዛውን ዶላር ትክክለኛ መሆኑን ስላረጋገጥን እስከ አንድ ሚሊየን ዶላር ይዛችሁ ኑና እናባዛ በማለት ወደ ማጭበርበር ተግባር እንደሚያስገቡ ታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያን የብር ኖትም በእጥፍ ማባዛት እንደሚችሉ በማስረዳትና ሃብታም እንደሚሆኑ በማሳመን ዜጎቻችን ያላቸውን ገንዘብ ይዘውላቸው ሲሄዱ ግማሾቹ ከነ ገንዘቡ ታፍነው ገሚሶቹ ደግሞ እራሳቸውን ስተው እንደተገኙና ገንዘባቸውንም እንደተቀሙ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

የዚህ የማጭበርበር ወንጀል ሰለባዎችም ቤተሰቦቻቸው መበተኑን፣ ለድህነትና ለጤና መታወክ መዳረጋቸውን ማረጋገጡን የገለፀው ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ኢንተለጀንስ ህብረተሰቡ ሁኔታውን ተገንዝቦ የማይገባ ጥቅም አገኛለሁ ብሎ ለእንደነዚህ ዓይነት አጭበርባሪዎች ሲሳይ እንዳይሆን እንዲሁም እራሱንና ቤተሰቡን መጠበቅ እንዳለበት እያሳሰበ አጠራጣሪ ነገር ሲያጋጥመው በቅርብ ላሉ የፀጥታ አካላት ወይንም በነፃ የስልክ መስመር 987 በመደወል ጥቆማ መስጠት እንደሚችል አስታውቋል።


Exit mobile version