ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት መኖር እና የሚያስከትለው ውጤት

  1. ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት መኖር

ጋብቻ በተጋቢዎች (አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት) ፍላጎት የሚመሰረት ማህበራዊ ተቋም (ህብረት) ነው፡፡ በሀራችን ህግ ስርዓት ጋብቻ በሶስት መንገድ ሊመሰረት የሚችል ሲሆን እነዚህም በክብር መዝገብ ሹም ፊት፣ የሀይማኖት ጋብቻ እና የባህል ጋብቻ ናቸው፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለያዩ ምክንያቶች ከላይ በተጠቀሱት ሶስት መንገዶች መደበኛ ጋብቻ ሳይፈፀም ሰዎች እንደ ባልና ሚስት ግንኙነት ፈጥረው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ማለት የጋብቻ ሂደትን ሳይከተል በአንድ ወንድ እና አንዲት ሴት መካከል የሚፈጠር ግንኙነት ሲሆን ሁለቱ ሰዎች እንደ ባልና ሚስት በትዳር መልክ አንድ ላይ ሲኖሩ እንደሆነ የተሻሻለው የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 አንቀፅ 98 ያሳያል፡፡

ሀገራት መደበኛ ጋብቻን ለማበረታታት ለረጅም ጊዜ ጋብቻ ሳይፈጸም እንደ ባልና ሚስት መኖር እውቅና ሳይሰጡ ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን እንደዚህ አይነቱ ግንኙነት እንደ መደበኛው ጋብቻ ሁሉ ቤተሰብን የሚፈጥር (ልጆችን መውለድ፣ ንብረት ማፍራት እና የመሳሰሉት) በመሆኑ ለቤተሰቡ ጥበቃ ለማድረግ በህግ እውቅና እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡

  1. ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት መኖር በተጋቢዎች ግላዊ ግንኙነት ላይ የሚያጣው ውጤት

ጋብቻ እንደ ባልና ሚስት መኖር ከጋብቻ እኩል ጥበቃ የሚሰጠው አይደለም፡፡ ይልቁንም በሀገራችን በስፋት የሚስተዋል እና ቤተሰብም የሚፈጥር በመሆኑ እውቅና እንዲያገኝ ከማድረግ አልፎ ከጋብቻ እኩል ተቀባይነት ሰጥቶ የሚያበረታታው አይደለም፡፡ ከቤተሰብ ህጉ እንዲሁም ከሌሎች የሀገራችን ህግጋትና ሀገራችን አባል ከሆነችባቸው አለም አቀፍ ስምምነቶች መረዳት እንደሚቻለው ግን ግላዊ ግንኙነታቸው በሁለቱም ሰዎች በእኩልነት መተዳደር የሚገባው መሆኑን ያሳያል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የጋራ ኑሯቸው ወጪ ለመሸፈን ሁለቱም እንደ አቅማቸውና ችሎታቸው አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት መኖር የጋብቻ ዝምድና አይፈጥርም፡፡ በመሆኑም በሴቲቱ እና በወንድየው የሥጋ ዘመዶች መካከል እንዲሁም በወንዱ እና በሴቲቱ የስጋ ዘመዶች መካከል ዝምድና አይፈጥርም፡፡ ሆኖም የጋብቻ ዝምድና ለጋብቻ መመስረት እንደቅድመ ሁኔታ የተቀመጠው ክልከላ ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት መኖር ላይም ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

  1. ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት መኖር በንብረት ረገድ የሚያስከትለው ውጤት
See also  የስንዴ ምች ዓለምን እያሻት ነው - የዩክሬኑ ጦርነት

ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት መኖሩ በንብረት ረገድ የራሱ ውጤት የሚያስከትል መሆኑን ከቤተሰብ ህጉ መረዳት ይቻላል፡፡ ይኸውም ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት መኖር የጋራ ንብረት ውጤት የሚያስከትለው ሴቲቱና ወንድየው ከ3 (ሶስት) አመት ላላነሰ ጊዜ ጊዜ አብረው ከኖሩ ሲሆን ለተጠቀሰው ጊዜ አብረው ከኖሩ በግንኙነታቸው ውስጥ ያፈሯቸው ንብረቶች የጋራ ንብረቶቻው ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ሆኖም በንብረት ረገድ የሚኖራቸው ግንኙነት የንብረት አስተዳደርን በተመለከተ በሁለቱ መሀከል ውል የሚኖር ከሆነ የውሉ ተፈፃሚነት እንደተጠበቀ ሆኖ ነው፡፡
አብረው በመኖር ላይ እያሉ የሚኖሯቸው ንብረቶች በግንኙነቱ ውስጥ የተፈሩ ንብረቶች እንደሆኑ የህግ ግምት የሚወሰድበት ሲሆን ተቃራኒ ማስረጃ አቅርቦ ይህን ግምት ቀሪ ማድረግ እንደሚቻል በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 102 ይደነግጋል፡፡ በሌላ በኩል እንደንብረት ሁሉ እዳ ሊኖር እንደሚችል የሚገመት ሲሆን ይህ እዳ አብረው በሚኖሩበት ጊዜ ለጋራ ኑሯቸው እና በግንኙነታቸው የተወለዱ ልጆችን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት የተገባ ከሆነ ለአከፋፈሉ ሁለቱም በአንድነትና በነጠላ ሀላፊ የሚሆኑ ይሆናል፡፡
ከዚህ ጋር በተያዘ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት በመኖር ውስጥ የጋራ ሀብት ከተፈጠረ በኋላ የሚኖራቸው ግንኙነት በምን ይገዛል የሚል ነው፡፡ የቤተሰብ ህጉ ለዚህ መልስ የሰጠ ሲሆን አንድ ጊዜ የጋራ ንብረት ከተፈጠረ በኋላ በጋብቻ ውስጥ ያለውን የንብረት ግንኙነት በተመለከተ በህጉ ውስጥ የተካተቱ ድንጋዎች ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት በሚኖሩ ሰዎች ላይ ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡ ይህ ማለት በስምምነት ከአንዳቸው አንዱ እንዲያስተዳድር ካልተስማሙ ወይም አንዱ በህግ አቅም ካላጣ በስተቀር የጋራ ንብረት በጋራ የሚያስተዳድሩ ይሆናል፡፡

  1. ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት የመኖር ግንኙነት መቋረጥ

ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት መኖር ከጅምሩም በሴቲቱ እና በወንድየው ፍላጎት መደበኛ የጋብቻ መፈፀሚያ ስነ ሥርዓቶችን ሳይከተል የሚመሰረት ግንኙነት ነው፡፡ በዚህም ግንኙነቱ ህግ ፊት ቀርበው የሚመሰርቱት አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ግንኙነቱ ሲቋረጥም እንደ ጋብቻ መደበኛ ሂደቶችን ላይከተል ይችላል፡፡ በግንኙነቱ ውስጥ የሚኖሩት ሴትና ወንድ በሚፈልጉበት ጊዜ ግንኙነታቸውን ማቋረጥ እንደሚችሉ የቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 105 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህ ማለት ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደባልና ሚስት ሲኖሩ የነበሩ ሰዎች ከንብረትና ከልጅ አስተዳደግ ጋር የተያያዘ አለመስማማት ካልገጠማቸው በስተቀር ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ ብቻ ፍርድ ቤት መሄድ አይጠበቅባቸውም ማለት ነው፡፡

See also  ሚራክል መኒ በማለት የሃሰት አስተምሮት ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ታገዱ!

Via attorney general

Leave a Reply