ETHIO12.COM

ብርሃኑ ነጋ አቋማቸውን ቀየሩ፤ ኢዜማ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግል ሃብት ለተከራይ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ፤ የኢዜማ የ ” ፍትህ” ሩጫ

ኢዜማ አዲስ አበባ ላይ ካሸነፈ ደርግ በግፍ የዘረፈውን የግለሰብ ንብረት በሁለት ዓመት ውስጥ እንደሚሸጥ ይፋ አደረገ። የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ነጋ ለዓመታት እንደ ፖለቲከኛም ሆነ እንደ ምሁር ደርግ የዘረፈውን የግለሰቦች ንብረት እንዲመለስ ሲወተውቱ እንደነበር የሚታወስ ነው። ዛሬ በምን መነሻ ይህ አቋም እንደተቀየረ በመግለሻው ይፋ አልሆነም።

ደርግ 5 ብር የሚከርአይ የጭቃ ቤት ትርፍ ነው በሚል በአዋጅ ዘርፎ ያሰቃያቸው፣ አንድ ቤት ውስጥ እየኖሩ በግቢያቸው ውስጥ አንድ ወይም ሁለት ክፍል ቤት አከራይተው ከሚኖሩ ምስኪኖች ሳይቀር ነጥቆ ቅርስ አልባ ያደረጋቸውን ዜጎች ከመጤፍ ያልቆጠረው ኢዜማ ግድግዳው የተያያዘ ቤትና የተፋፈገውን ሰፈር እንዴት አድርጎ የተከራይ ይዞታ እንደሚያደርግ አላብራራም።

ግፈኛው ደርግ 2 ብር ከሃምሳ ሳንቲም አበል እየከፈለ የመከራ ፍዳ ሲያሳያቸው ለነበሩ ምስኪኖች ድምጽ እንደሚሆኑ ደጋገመው ሲናገሩ የነበሩት የቅንጅት፣ የግንቦት ሰባት፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት፣ የኢዜማ መሪ በዚ ጉዳይ ላይ ዝርዝር መረጃ ሊሰጡ እንደሚገባ ዜናውን የሰሙ ጠቁመዋል።

1 / 7

ስሙ ፍትህን ያካተተው ፓርቲ በገፍ ድምጽ አገኛለሁ በሚል ሂሳብ የአንድ ትውልድ እድሜ ፍትህ የተዛባባቸውን ቤተሰቦች የገፋ ፕሮግራም ይዞ መቅረቡ ከተራ የድምጽ ክጀላና የፖለቲካ ቁማር ተለይቶ እንደማይታይም የገለጹ አሉ። በሁለት ዓመት ውስጥ በአብዛኛው የአዲስ አበባን ውሽቅሽቅና መተናፈሻ የሌላቸው ሰፈሮች ወደ ግል ሃብት አዞራላሁ ከተግባራዊነቱ በላይ ሸፍጡ የጎላበት የዘመቻ እቅድ እንደሆነ እየተነገረ ነው። ከታች የኢዜአ ዘገባ እንዳለ ያንብቡ። በተከታታይ አስተያየት አሰባስበን እንመለስበታለን።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ በምርጫ አሸንፎ አዲስ አበባን የመምራት ዕድል ካገኘ የመኖሪያ ቤት ችግሩን ለማቃለል በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ የቀበሌ ቤቶችን በሽያጭ ወደ ነዋሪዎች አስተላልፋለሁ ብሏል።

ኢዜማ የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ችግር ያቃልላሉ ያላቸውን 138 ቁልፍ ግቦችን የያዘ የቃል ኪዳን ሰነድ ዛሬ ይፋ አድርጓል።ፓርቲው በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ለመዲናዋ ነዋሪዎች ሊሰሩላቸው ይገባሉ ብሎ የለያቸውን 138 ቁልፍ ግቦች አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዳሉት ‘ኢዜማ እውነተኛ ፌዴራሊዝም መሰረቱ ያልተማከለ የአስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ነው’ የሚል እምነት አለው።

አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከተማ ብትሆንም በቅድሚያ ለሚኖሩባት ዜጎች ምቹ ሆና እንድትገኝ ማድረግ ይገባናል ብለዋል። “ፓርቲው ከሕዝቡ ጋር ወርዶ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት የነዋሪዎቿ ችግር ስር የሰደደ መሆኑን ለይተናል ለዚህ የሚመጥን የአምስት ዓመት 138 ቁልፍ ግቦችን የያዘ የቃል ኪዳን ሰነድም አዘጋጅተናል” ብለዋል ፕሮፌሰሩ።

አዲስ አበባን የከተማዋ ነዋሪ የሆነ፣ የሕዝቡን ችግር የተረዳና በሕዝብ የተመረጠ ማንኛውም ግለሰብ ማስተዳደር ይችላል ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ።በቂርቆስ ከፍለ ከተማ የአዲስ አበባ ምክር ቤት የኢዜማ ዕጩ አቶ ክቡር ገና በመዲናዋ ስር የሰደደውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በአምስት ዓመት ውስጥ በአነስተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች የሚተላለፍ ከ200 ሺህ ያላነሰ የጋራ መኖሪያ ቤት እንገነባለን ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የከተማ አስተዳደሩ በሚያወጣው የጥራት ደረጃ መሰረት የቀበሌ ቤቶችን ለሚኖሩባቸው ሰዎች ቅድሚያ በመስጠት በሁለት ዓመታት ውስጥ በሽያጭ እንዲዘዋወሩ እናደርጋለን ነው ያሉት።የዜጎችን ገቢ ከፍ፤ ወጪያቸውን ዝቅ የሚያደርጉ አሰራሮች በመተግበር የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር፣ የከተማዋን ሠላምና ጸጥታ የሚያስጠብቅ ጠንካራ የደህንነት መዋቅር መዘርጋት፣ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ዘመናዊ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትና ሌሎችም ከተማዋን የሚመጥኑ አሰራሮች ይተገበራሉም ብለዋል አቶ ክቡር።

የኢዜማ የየካ ክፍለ ከተማ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ዕጩ አቶ አሮን ሰይፉ በበኩላቸው በከተማዋ ጥራቱን የጠበቀ የማኅበራዊ ዘርፍ አገልግሎት መስጠት ቀዳሚ ስራችን ይሆናል ነው ያሉት።ከእነዚህ መካከል የመምህራንን አቅም በመገንባት ብቁ ተማሪዎች ከማፍራት በተጨማሪ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግን ጠቅሰዋል።

ደረጃቸውን የጠበቁ የሕክምና ተቋማት በፍትሃዊነት ማስፋፋትና የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ማቃለልም በመጪው አምስት ዓመት ለሕዝቡ የምንገባው ቃል ነው ብለዋል።ጽዱና ውበትን የተላበሰች አረንጓዴ ከተማ መፍጠርና መዲናዋን የጥበብ ማዕከል ማድረግ ኢዜማ ከተመረጠ ገቢራዊ የሚያደርጋቸው ስራዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።



Exit mobile version