Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ ባሉ አለመግባባቶችና የውይይት መጓተቶች ላይ ስብስባ እንዲጠራ ሃሳብ አቀረበች

 ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ላይ ባሉ አለመግባባቶችና የውይይት መጓተቶች ላይ ስብስባ እንዲጠራ በአፍሪካ ህብረት ለመሪዎች ጉባኤ ቢሮ ሃሳብ አቀረበች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ ለጻፉት ደብዳቤ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፥ ኢትዮጵያም የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበርና ለዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሺሴኬዲ ከግድቡ ጋር በተያያዘ ባሉ መጓተቶች ላይ ስብሰባ እንዲጠሪ ሃሳብ አቅርባለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እስካሁን በግድቡ ዙሪያ የተካሄደው ውይይት እንዳልተሳካ መቁጠር አግባብ አለመሆኑን ጠቅሰው፥ ለዚህም እንደ የመርሆዎች ስምምነት መፈረም እና የብሔራዊ ገለልተኛ የሳይንስ ምርምር ቡድን መመስረትን በመልካም ማሳያነት አንስተዋል፡፡

በግድቡ ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮች ህጋዊና ቴክኒካዊ ተግዳሮቶች ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርጉ ስምምነቶች ላይ ለመድረስ እንቅፋት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ለዘጠኝ ጊዜያት ያህል መስተጓጎል የገጠመውን የሦስትዮሽ ድርድር ዕውን እንዲሆን ያደረገው ጥረት አድነቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ላይ የሚካሄደው የሦስትዮሹ ድርድር አሁንም ቢሆን በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር እንዲቀጥል ጽኑ ፍላጎትት እንዳላት መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ከሁለት ቀን በፊት ኢትዮጵያ የሚከተለውን ጥሪ አስተላለፋ ነበር። ከስር የተቀመጠውን ጥሪ ከማቅረቧ በፊትም ሙሌቱ ሲካሄድ መረጃ መለዋወጥ እንዲያስችል ታዛቢያቸውን እንዲያሳውቁ ለሁለቱም አገራት ብቅ በቀደመው ውል መሰረት ግብዣ ብታቀርብም አሻፈረኝ ማለታቸው ይታወሳል።


RELATED


ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን ወደ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲመለሱ ጥሪ አቀረበች

ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን ወደ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲመለሱና በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ሂደት እንዲያከብሩ ጥሪ አቀረበች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በህዳሴ ግድብ ላይ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት እየተካሄደ ያለውን ድርድር በተመለከተ ለፀጥታው ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ የኢትዮጵያን አቋም አሳውቀዋል፡፡

በዚህም የምክር ቤቱ አባላት ሃገራቱ ወደ ሶስትዮሽ ድርድር እንዲመለሱና በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ሂደት አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በደብዳቤያቸውም በአፍሪካ ህብረት የሚመራው ሂደት የፀጥታው ምክር ቤትን መርሆዎች መሠረት ያደረገና ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎችን የሚያፈላልግ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጅ ግብጽና ሱዳን በቅን ልቦና እየተደራደሩ አለመሆኑን በመጥቀስ፥ የሚያግባባና አሸናፊ ወደ ሆነ ውጤት ለመድረስና አስፈላጊ ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አያይዘውም ሃገራቱ ድርድሩን “መበጥበጥና ማበላሸትን” ምርጫ ማድረጋቸውን እና ጉዳዩን “ዓለም አቀፋዊ ይዘት” በማላበስ ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ ለመክተት እየሞከሩ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ለሚመራው የሶስትዮሽ ድርድር እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ እና አሁን ላይ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የሚል መርህን በመከተል ጉዳዩን ዳር ለማድረስ ለሚያደርጉት ጥረት ያላትን ምስጋና እና አድናቆትም ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የግድቡ ውሃ ሙሌት ቀደም ብሎ መረጃ ለመለዋወጥ ያሳየችውን ተነሳሽነት በማስታወስ ሃገራቱ ውድቅ ያደረጉበትን መንገድም አንስተዋል፡፡

ሃገራቱ በህዳሴው ግድብ ላይ የያዙትን ፍትሃዊ አቋም ለማሳካትና በውሃ ፍሰት አጠቃቀሙ ሁሉን አቀፍ አስገዳጅ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚሄዱበት መንገድ ተቀባይነት እንደሌለውም አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያም የሶስቱ ሃገራት ለገቡት የመርህ ስምምነት ያላትን ተገዥነት በማንሳትም፥ ግብጽና ሱዳን የገቡትን የመርህ ስምምነት በመተው ማፈንገጣቸውንም ነው በደብዳቤው ያወሱት፡፡

ኢትዮጵያን ጫና ውስጥ ለመክተት የሚደረግ ሙከራም ሆነ ከአፍሪካ ህብረቱ መር ሂደት ማፈንገጥም በሃገራቱ መካከል ያለውን መተማመን የሚያፈርስና እምነት የሚያሳጣ ነው ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡


Exit mobile version