Site icon ETHIO12.COM

የምርጫ ካርድ አለመውሰድ በማይፈልጉት ፓርቲና መንግስት ለመመራት መፍቀድ ነው

የምርጫ ካርድ አለመውሰድ በማይፈልጉት ፓርቲና መንግስት ለመመራት መፍቀድ መሆኑ ተጠቆመ።ምርጫ ዜጎች ሀገራቸውን በተሻለ መልኩ የሚመራላቸውን ፣ ወደ እድገት እና ብልጽግና የሚወስዳቸውን መንግስት የሚመርጡበት መሳርያ መሆኑም ተገለጸ፡፡

አዲስ ዘመን ያነጋገረው አርቲስት ደሳለኝ ሀይሉ እንዳስታወቀው የምርጫ ካርድ አለማውጣት ማለት በማይፈልጉት ፓርቲና መንግስት ለመገዛት ራስን ማመቻቸት ነው።ሕገመንግስታዊ መብትን አለመጠቀም ጭምር ነው፡፡

የምርጫ ካርድ ባለማውጣቱ ሳይመርጥ የቀረ ሰው ለቀጣይ አምስት ዓመታት የማይፈልገውንና ተጠያቂ ለማድረግ የማይችለውን ሰው ወይም ፓርቲ መምረጥ ማለት ነው ያለው አርቲስት ደሳለኝ ፣ መራጩ ባልፈለገው ፓርቲ ለመተዳደር እድል እየሰጠው መሆኑንም ተናግሯል።

አንድ ሰው የዴሞክራሲ መብቱን እየተጠቀመ ነው የሚባለው የሚፈልገውንና የማይፈልገውን በካርዱ መወሰን ሲችል ነው ያለው አርቲስት ደሳለኝ ፣ እኔም “የምርጫ ካርዴን ወስጃለሁ ፤ የምፈልገውን ፓርቲና መንግስት እመርጣለሁ፡፡” ብሏል፡፡

ሌሎች አርቲስቶችም ጥበብንና ጥበበኞችን የሚያበረታታ፣ የሚወድና የሚያከብር እንዲሁም ለጥበብ የተለየ ስፍራ የሚሰጥ ፓርቲን እንዲመርጡ ፣ ህብረተሰቡም የመምረጥ መብቱን እንዲጠቀም እንዲያበረታቱ ጥሪ አቅርቧል ።

አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ በበኩሉ “ የምርጫ ካርዱን በጊዜ ወስዶ መምረጥ ያልቻለ ዜጋ በምርጫው ውጤት የማማረር መብት የለውም“ ብሏል።የምርጫ ካርድ ማውጣት ለራስ መብት መሟገት መሆኑንም አመልክቷል።

ማንኛውንም ምርጫን መሰረት ያደረጉ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ በቅድሚያ የምርጫ ምዝገባ ማድረግና በመምረጥ መብት መጠቀም ያስፈልጋል።

በሀገሪቱ በታዩ ተደጋጋሚ የምርጫ መጭበርበሮች ምክንያት እከሌ ነው የሚያሸንፈው ብለን ሳንመርጥ ብንቀመጥና የማንደግፈው ፓርቲ ስልጣን ላይ ቢወጣ የምንደግፈው ፓርቲ እንዳይመረጥ ራሳችን አስተዋፅኦ እያደረግን ነው ብሏል፡፡

ነገ አፋችንን ሞልተን የምንቃወመውም መምረጥ ስንችል ነው ያለው አርቲስት ቴዎድሮስ፣ ሌሎች ሰዎች በመረጡት ምርጫ ግን ማማረርም ሆነ ማመስገን ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ አይነት እንደሚሆን አመልክቷል፡፡

ሳይመርጡ መቅርት ፀፀት የሚያስከትል መሆኑን የገለፀው አርቲስት ቴዎድሮስ ፣ የምርጫ ካርድ አውጥቶ ይወክለኛል የሚለውን ፓርቲ የመምረጥ መብትን የመጠቀም ምልክት መሆኑን አስታውቋል፡፡

ትራምፕ ባሸነፉበት የአሜሪካ ምርጫ የማሸነፉቸው ሚስጥር ደጋፊዎቹ በስፋት ወጥተው በመምረጣቸው እንደሆነ የጠቆመው አርቲስት ቴዎድሮስ፣ አለመምረጥ ባልመረጡት መንግስት ለመመራት መፍረድ መሆኑንም አብራርቷል፡፡

የምርጫ ካርድ አውጥቶ መምረጥ እንደማንኛውም ሀገራዊ ግዳጅ ሊታይ ይገባል ያለው አርቲስቱ፣ የመምረጥ ጉዳይ ከመብት ጥያቄነት አልፎ የዜግነት ግዴታም ጭምር መሆኑን አስታውቋል፡፡

ዜጎች የምርጫ ካርድ በማውጣት ሊመርጡ እንደሚገባ የጠቆመው አርቲስት ቴዎድሮስ፣ ምርጫ ዜጎች ሀገራቸውን በተሻለ መልኩ የሚመራላቸውን ፣ ብልጽግና የሚወስዳቸውን መንግስት የሚመርጡበት መሳርያ መሆኑንም ገልጿል፡፡

“አንድ ልናምነውና ልንቀበለው የሚገባን እውነት አለ፤ ምርጫ ማለት የሀገራት እጣ ፈንታ የሚወሰንበት ማለት ነው። የሀገራት እጣ ፈንታን ደግሞ የሚወስነው በህዝብ ነው ተብሎ እድሉ ተሰጥቷል። እንደ አንዳንድ አምባገነን ሀገሮች አኔ ልወስንልህ አልተባለም።ካርድ እናውጣ እንምረጥ” ብሏል ፡፡

በሰዎች ላይ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ አርቲስቶችና ታዋቂ ግለሰቦችም የምርጫ ካርድ አውጥተው እንዲመርጡ ያሳሰበው አርቲስቱ፣ ከመምረጥም ባሻገር ህብረተሰቡን የምርጫ ካርድ እንዲያወጣ በማበረታታትና አለፍ ሲልም የሚደግፉትን ፓርቲ እንዲያስተዋውቁም ጥሪ አቅርቧል፡፡

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 14/2013 – በዳግማዊት ግርማ


Exit mobile version